ለደቡብ ምሥራቅ እስያ ብርቅዬ የሆነው የ “ሆሎንግ” ዛፍ ዝርያ በበጋ ወቅት የሚረግፉ ባለ ክንፍ ፍሬዎቹ በነፋስ ኃይል በዓየር ላይ እየተሽከረከሩ በስፋት ተሰራጭተው ራሱን እንደሚያበዛ (እንደሚተካ) ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በተለምዶ “ሆሎንግ” በመባል የሚታወቀው በሳይንሳዊ ስሙ “ዲኘቴሮካርፐስ ሬቱሰስ” ቁመቱ እስከ 60 ሜትር የተለካ ጠንካራ ዛፍ ነው፡፡ ለኢንድስትሪ ግብአት፣ ለግንባታ እና ቁሳቁስ መስሪያም ይውላል፡፡
የ “”ሀሎንግ ዛፍ” የዘር ማሰራጫ ወይም መበተኛ ስልቱ ከሁሉም የተለየ – ራሱን የመተኪያ ስልት ያለው ነው፡፡ ዛፉ ፍሬ አፍርቶ በሚጐመራበት የበጋ ወቅት ባለሁለት ክንፍ ፍሬዎቹ ከቅርንጫፍ ተላቀው በዓየር ላይ ተንሳፈው ይሽከረከራሉ፡፡
የፍሬዎቹ ክንፋማነት ተፈጥሮ ለዛፉ የለገሰችው ራሱን የመተካት፣ የመትረፍ ስልት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህም በሚሊዬን የሚቆጠሩ ዓመታትን መዝለቅ ችሏል፡፡
በበጋ ወራት ተፈጥሯዊ ባለ ክንፍ “ድሮኖች” ከዛፉ ተሰፍንጥረው ዙሪያውን ሲሽከረከሩ ይስተዋላሉ – መሬት እስኪይዙ ድረስ ፡፡ ስለ “ሆሎንግ” ዛፍ ራሱን የማትረፍ “የመዳን” ስልት ከመስማት ይልቅ በዓይን መመልከት በተሻለ ደረጃ ግንዛቤን እንደሚያስጨብጥ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በመጨረሻም “ሆሎንግ” የሚለው መጠሪያው መጀመሪያ የተመለከተው የእንግሊዝ አሳሽ “ሀውሎንግ” ሲል የጠየቀውን መሰረት አድርጐ መጠሪያው ሊሆን መቻሉን ድረ ገጹ በማደማደሚያነት ለንባብ አብቅቶታል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


