“ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው“ እየተባለ በተደጋጋሚ የሚነገረው የሕዝቧ ዋነኛ መተዳደሪያ ዘርፍ በመሆኑ ነው። ይሁንና “የጀርባ አጥንት” የሆነውን ይህን ዘርፍ መሬት በማረስ እና ዘር በመዝራት ብቻ የሕዝብን የምግብ ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። ይህም ሲባል ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ (የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ)፣ የፀረ-ተባይ እና ፀረ-አረም ኬሚካሎች እንዲሁም የግብርና ማሽነሪዎችን (ትራክተር እና ኮምባይነር) በበቂ ሁኔታ በአቅራቢያው እና በወቅቱ ማግኘት ይገባዋል፡፡
ግብዓት በአግባቡ መሟላት ለአንድ አርሶ አደር የመኖር እና የሞት ያህል ወሳኝነት አለው። ለምሳሌ አንድ አርሶ አደር በሽታን የሚቋቋም እና ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚ የሆነ ምርጥ ዘርን እና ተገቢውን ማዳበሪያ ቢጠቀም ግብዓት ሳይጠቀም ከሚያገኘው ምርት ከእጥፍ በላይ ብልጫ ሊያመጣ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙዎች ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን ኑሮ ሲያሻሽል በሀገር ደረጃ ደግሞ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲኖር ያደርጋል።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ደሳለኝ የኔት በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው እየጣለ ያለውን ዝናብ እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በመጭው ክረምት በሁለት ሄክታር መሬታቸው ላይ በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለመሸፈን እንዳቀዱ ነው በስልክ የነገሩን። በቆሎ፣ በርበሬ፣ ባቄላ እና ዳጉሳ ከሚያመርቷቸው ሰብሎች መካከል ይጠቀሳሉ። አሁን ላይ ማሳቸውን የክረምቱን መግቢያ ተከትለው በሚዘሩ በቆሎ እና ድንች ሸፍነዋል። ከፍተኛ ምርት ለማግኘትም የተሻሻሉ ምርጥ ዘርን ተጠቅመዋል። አርሶ አደሩ ያፈሉትን የበርበሬ ፍል እያረሙ እና የሚተከልበትን መሬት ደጋግመው እያረሱ መሆኑንም ነግረውናል።
በመኸር በዘር ለሚሸፍኑት መሬት ስምንት ኩንታል ዳፕ እና ዩሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ቀድመው ለሚዘሩት ሰብል በቂ የአፈር ማዳበሪያ አግኝተዋል። በቀጣይ ለሚዘሩት ሰብልም ማዳበሪያ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ናቸው። ባለፈው ዓመትም ሆነ በቀጣዩ የምርት ዘመን የግብዓት አቅርቦት ችግር አለመኖሩን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት ያለ እረፍት የመኸር እርሻ ሥራቸውን እየከወኑ የሚገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ፈጠነ ብርሐን ናቸው። በየዓመቱ ከአራት ሄክታር በላይ መሬታቸውን በተለያዩ የሰብል አይነቶች እንደሚሸፍኑ ነው የተናገሩት። በዋናነት ስንዴ፣ ማሾ እና ማሽላ የሚያመርቷቸው ሰብሎች ናቸው።
አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ እንደሚያመርቱ ነው በስልክ የነገሩን። በበጋ መስኖ ያለሙትን ስንዴ እና ሽንኩርት ሰብስበው አሁን ላይ ደግሞ ለመኸር እርሻ እያዘጋጁ ነው።
ምርጥ ዘር፣ ኮምፖስት እና ሰው ሠራሸ የአፈር ማዳበሪያ በስፋት እንደሚጠቀሙ የተናገሩት አርሶ አደር ፈጠነ ለዚህ የሚሆንም ከሰባት ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። በዚህ ወቅት ለሰብል ልማቱ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት እያሟሉ ነው።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ ትበልጭ አጥናፉ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት በዞኑ በመኸር ወቅት 266 ሺህ 597 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች ለመሸፈን ታቅዷል፤ 266 ሺህ 394 ሄክታር መሬት በአንደኛ ዙር መታረሱንም አስታውቀዋል። ከዚህም 56 ሺህ 677 ሄክታሩ በትራክተር የታረሰ እንደሆነም ገልጸዋል።
የእርሻ ሜካናይዜሽን በግብርና ሥራ ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለጉልበት እና ለጊዜ ቁጠባ፣ የምርት ጥራትን እና ውጤታማነትን መጨመር እንደሚያስችል ባለሙያዋ አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት 43 ሺህ ሄክታር መሬት በበቆሎ ዘር ተሸፍኗል። ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ 708 ሺህ 596 ኩንታል ዳፕ እና ዩሪያ የቀረበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 353 ሺህ 477 ኩንታሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል። ይህም ቀድመው ለተዘሩት እና ለሚዘሩት ሰብሎች እያገለገለ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም የአርሶ አደሮችን ወጭ ለመቀነስ አምስት ሚሊዮን 299 ሽህ 611 ሜትር ኪዩብ መደበኛ እና ቨርሚ ኮምፖስት ተዘጋጅቶ በ145 ሺህ 739 ሄክታር መሬት ላይ መዋሀዱን ገልጸዋል። 23 ሺህ 357 ኩንታል የተለያዩ የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን ለማሰራጨትም ታቅዶ 15 ሺህ 537 ኩንታሉ ተሰራጭቷል።
አርሶ አደሮች የመሬት ዝግጅታቸውን በወቅቱ እና በአግባቡ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል ያሉት የሰብል ልማት ባለሙያዋ፤ በተለይም በዘመናዊ የግብርና አሠራር ዙሪያ የባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደ ሚገባ አስገንዝበዋል። አርሶ አደሩ እየጣለ ያለውን ዝናብ ተጠቅሞ በወቅቱ የሚዘሩ ሰብሎችን ቀድሞ እንዲዘራም አሳስበዋል። በምርት ዘመኑ 14 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደ ሚጠበቅ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል በ2018/19 የምርት ዘመን አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን አቅዷል። በዘንድሮው የምርት ዘመን በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማውም 205 ሚሊዮን 196 ሺህ 945 ኩንታል ምርት ተጠባቂ ነው። እነዚህም ለምግብነት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለውጭ ገበያ (ለኤክስትፖርት) የሚውሉ ሰብሎች ናቸው፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለበኵር እንደተናገሩት የግብርና ሥርዓቱን ማዘመን እና ከልማዳዊ አሠራር ማውጣት ይገባል። አርሶ አደሩን ከበሬ ጫንቃ ለማላቀቅ፣ ጊዜ እና ጉልበቱን ለመቆጠብ እና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ሜካናይዜሽን አሠራር በትኩረት እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በምርት ዘመኑ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የታለመውን ዕቅድ ለማሳካት የኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት። ይህንንም ለማሳካት እርሻን በድግግሞሽ ከማረስ ጀምሮ ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር በሚፈለገው መጠን፣ በወቅቱ ከአርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ማድረግ፣ ኩታ ገጠም እርሻን ማሳደግ፣ የሜካናይዜሽንን አሠራር በሰፊው መተግበር ይገባል።
በክልሉ ለ2018/19 የምርት ዘመን ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ለማስገባት መታቀዱን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ተጓጉዞ መድረሱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለአሚኮ ተናግረዋል። እስካሁን ባለው ጊዜም አርሶ አደሮች ገዝተው የወሰዱት እና የተሠራጨው ሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሆነ ተናግረዋል። በሌላ በኩል 220 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ ታቅዷል። እስካሁን ባለው ጊዜ 208 ሺህ ኩንታል የሰብል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ድልድል ተደርጓል። 72 ሺህ ኩንታል የሚሆነው የሰብል ምርጥ ዘርም ተሠራጭቷል።
መረጃ
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት አፈጻጸም
| የምርት ዘመን በዓ/ም | ዕቅድ በኩንታል | ክንውን | በመቶኛ |
| 2011/12 | 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን | 5 ሚሊዮን | 90.9 |
| 2012/13 | 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን | 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን | 82.6 |
| 2013/14 | 7 ነጥብ 2 | 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን | 87.5 |
| 2014/15 | 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን | 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን | 54.9 |
| 2015/16 | 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን | 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን | 52.2 |
| 2016/17 | 8 ሚሊዮን | 6 ነጥብ 2 | 77.5 |
| 2017/18 | 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን | 6 ነጥብ 9 | 77.5 |
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የሰኔ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


