“ተዋጊ በሬ ከሳር ይጥላል”

0
259

በእግር መጓዝ ችግር ሲሆንብን ሰረገላን ፈጠርን፤ ሰረገላው ሲዘገይብን መኪናን ሰራን፤ መኪናው በቂ ሆኖ ባልተገኘበት ፍጥነት ደግሞ ሰማዩን ሰንጥቆ የሚበር አውሮፕላንን ፈጠርን።

ይህ ሂደት የሰውን ልጅ የፈጠራ ታሪክ ከችግር እያሻገረ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከፍ ያደረገው ዘላለማዊ ግስጋሴ ነው። የሰው ልጅ ታሪክ የምቾት  አይደለም፤ ይልቁንም ያጋጠሙትን ማነቆዎች በፈጠራ እያለፈ ዓለምን ወደተሻለ መፍትሔ የመራበት ተከታታይ ጉዞ ነው። የሰው ልጅ ችግሮችን እፈታለሁ ሲል ነው የተሻለ ዓለምን የፈጠረው።

ለመሆኑ የሰው ልጅ አእምሮ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው በተሻለ አቅሙ የሚሠራው? በምቾት እና በድሎት ወይስ በእጥረት እና በፈተና ወቅት?

የስነ-ልቦና እና የነርቭ ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰው ልጅ አእምሮ በተፈጥሮው ኃይልና ጉልበት ለመቆጠብ ይጥራል። አእምሯችን ያለንበት ሁኔታ ምቹና አስተማማኝ በሚሆንበት ጊዜ በለመደው አሠራርና አስተሳሰብ ብቻ ተወስኖ መጓዝን ይመርጣል።

ይህ ሁኔታ በስነ-ልቦና ጥናት “የምቾት ቀጣና” ይባላል። በዚህ ቀጣና ውስጥ አዲስ ነገር የመፍጠር፣ የመጠየቅና የመመራመር ፍላጎት በእጅጉ ይቀንሳል።

በተቃራኒው ግን እጥረት ወይም ከባድ ፈተና ሲያጋጥም አእምሯችን አደጋ እንደተጋረጠበት ስለሚረዳ ካለበት የምቾት እንቅልፍ ይነቃል። የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ወይም እጥረቱን ለመሙላት አዳዲስ አማራጮችን መፈለግ ይጀምራል። ይህ የፈጠራ አስተሳሰብ  ይባላል።

የታሪክ ምሁራን እንደሚስማሙበት የሰው ልጅ ስልጣኔን የቀየሩ ታላላቅ ግኝቶች የመነጩት ከስኬት ሳይሆን ከከባድ ችግሮች ነው። ለምሳሌ የሕክምና ሳይንስን የቀየሩት በርካታ መድኃኒቶች የተገኙት ዓለምን በወረሩ አስከፊ ወረርሽኞች ወቅት ነው።

የትራንስፖርትና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች የፈነዱት በጦርነቶችና በረሃብ ወቅት የተፈጠሩትን መሰናክሎች ለማለፍ በሚደረግ ጥረት ውስጥ ነው። “አስፈላጊነት የፈጠራ እናት ናት” የሚለው የጥንት አባባል ሳይንሳዊ መሠረት ያለው እውነት ነው።

ችግርን ወደ ዕድል መቀየር የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃል። ታዋቂው ተመራማሪና ደራሲ ናሲም ታሌብ “Antifragile: Things That Gain from Disorder” በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ፣ በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን በሶስት ይመድባቸዋል።

የመጀመሪያው ምድብ ተሰባሪ የሚለው ነው። በትንሽ ግፊት ወይም ችግር የሚሰባበሩ ናቸው። (እንደ ብርጭቆ ያሉት)። ሁለተኛው ጠንካራዎች ናቸው። ችግሮችን ተቋቁመው ሳይለወጡ የሚቆዩ ናቸው። (እንደ ድንጋይ ያሉ)። ሦስተኛው ከፈተና የሚማሩ ናቸው። ከግርግር፣ ከፈተና እና ከችግር ውስጥ እየጠነከሩና እየበለጸጉ የሚሄዱት ናቸው። (እንደ ሰው ልጅ የጡንቻ ሥርዓት፤ ጡንቻ በከባድ ስፖርታዊ ግፊት ውስጥ ሲያልፍ ይበልጥ ይጠነክራል)።

ታሌብ እንደሚለው የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ አቅም “የማይሰበር- የሚማር” ነው። በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ውዝግቦችና ውድቀቶች ይበልጥ ጠንካራና ብልህ እንድንሆን ያደርጉናል።

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ካሮል ዲዌክ ሰዎች ለችግሮች የሚሰጡትን ምላሽ በጥናት ፈትሸዋል። የእድገት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ችግሮችን እንደ ግላዊ ውድቀት ወይም የአቅም ማነስ ማረጋገጫ አድርገው አይወስዱትም። ይልቁንም አእምሯቸው እንዲያድግና አዲስ ነገር እንዲማር የሚገፋፋ  አስገዳጅ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርገው ይመለከቱታል።

ዛሬ በዓለማችን ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ግዙፍ ኩባንያዎች ታሪካቸው ሲመረመር አብዛኛዎቹ የተመሠረቱት ወይም አቅጣጫቸውን የቀየሩት በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስና በውድቀት ወቅት ነው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጃፓን በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስና የግብዓት እጥረት ውስጥ ነበረች። የቶዮታ ኩባንያ እንደ አሜሪካውያኑ ተፎካካሪዎቹ በብዛት አምርቶ ማከማቸት የሚችልበት የገንዘብና የጥሬ ዕቃ አቅም አልነበረውም።

ይህንን ትልቅ ችግር ለመፍታት የኩባንያው መሃንዲሶች “Just-In-Time” (ልክ በሰዓቱ) የተባለውን አዲስ የአመራረት ዘዴ ፈጠሩ። ይህ ዘዴ የሚፈለገውን ምርት፣ በሚፈለገው መጠንና ሰዓት ብቻ በማምረት ብክነትን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድ ነበር። ይህ በችግር ምክንያት የተፈጠረ አሠራር ቶዮታን በዓለም ላይ ካሉ ቀልጣፋና ተመራጭ የመኪና አምራቾች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል።

ውድቀት ወይም ችግር የሕይወት ማቆሚያ ቀይ መብራት አይደለም። ይልቁንም አቅጣጫችንን እንድናስተካክል የሚነግረን ጠቋሚ ምልክት ነው። በእለት ተእለት ህይወታችን ውስጥ ብዙ መሰናክሎች ያጋጥሙናል። ሥራ ማጣት፣ የንግድ መክሰር፣ ወይም በግል ሕይወት ውስጥ የሚገጥሙ ስብራቶች የመጨረሻው ምዕራፍ ሊመስሉ ይችላሉ። ነገር ግን በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ነው አዳዲስ አቅሞቻችን የሚወለዱት።

ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳሳየን፣ እያንዳንዱ ችግር አዲስ ፍላጎትን ይፈጥራል፤ እያንዳንዱ ፍላጎት ደግሞ ወደ መፍትሔ ይመራል። በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች “ለምን እኔ ላይ ደረሰ?” ብለን ከማማረር ይልቅ “ይህ ሁኔታ ምን አዲስ በር ሊከፍትልኝ ይችላል?” ብለን መጠየቅ ስንጀምር፣ የለውጥ ጎዳናው መታየት ይጀምራል።

ችግርን ወደ እድል የመቀየር 4 ተግባራዊ መንገዶች

የመጀመሪያው ስሜትን መቆጣጠርና ሁኔታውን በትክክል መረዳት ነው። ችግር ሲገጥመን የመጀመሪያው ስሜታችን ፍርሃት፣ ቁጣ ወይም ተስፋ መቁረጥ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በእነዚህ ስሜቶች ተመርተን ውሳኔ መወሰን የለብንም። ሁኔታውን ከተጋነነ ስሜት ነፃ ሆነን በጥሞና መመልከት ይኖርብናል።

ሁለተኛው ችግሩን በአዲስ መነጽር ማየት። “ይህ ለምን በእኔ ላይ ደረሰ?” ከሚል የተጠቂነት አስተሳሰብ በመውጣት “ይህ ሁኔታ ምን እያስተማረኝ ነው? ከዚህ ውስጥ ምን አይነት አዲስ በር ሊከፈት ይችላል?” የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ይገባል።

ሦስተኛው ዘዴ በትናንሽ እርምጃዎች መንቀሳቀስ ይባላል። ትልቅ መፍትሄ ለማምጣት ፍጹም መሆንን አትጠብቁ። ካጋጠማችሁ ፈተና ውስጥ ዛሬ ምን ጥቃቅን ነገሮችን ማስተካከል እንደምትችሉ በመለየት በአነስተኛ አቅም መተግበር ጀምሩ።

አራተኛው ደግሞ ከልምምድ መማር ነው። የመጀመሪያው ሙከራ ላይሳካ ይችላል። ነገር ግን በእያንዳንዱ ውድቀት ውስጥ ምን ስህተት እንደተሠራ በመገምገም አሠራርን እያሻሻሉ መሄድ ለታላቅ ስኬት መሰረት ይሆናል።

ችግሮች የሕይወታችን የማይቀሩ አካላት ናቸው። በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ከፈተና ነፃ ሊሆን አይችልም። ልዩነቱ የሚፈጠረው ግን ለፈተናዎች በምንሰጠው ምላሽ ላይ ነው።

እንቅፋቶች መንገዳችንን የሚዘጉ ድንጋዮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ አለያም ደግሞ ወደ ላቀ ከፍታ ለመውጣት የምንረግጣቸው ደረጃዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ውሳኔው በእጃችን ነው፤ መሰናክሉን አይተን እንቆማለን ወይስ በእንቅፋቱ ላይ ረግጠን ወደፊት እንጓዛለን? የተሻለውን እንምረጥ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 1   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here