ለድህረ ምርጫ ተግባራት ስኬት የድርሻችንን እንወጣ!

0
10

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ኹኔታ ተካሂዷል፡፡ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መካሄዱ መራጮች ወኪላቸውን  በነጻነት እንዲመርጡ አስችሏቸዋል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች  ጊዜያዊ  ውጤትም  ታውቋል፡፡ የምርጫው ውጤቶች በወቅቱ ይፋ መደረጋቸው የሕዝብ አመኔታን የሚጨምር ወሳኝ ርምጃ  ነው። የመጨረሻው ውጤትም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ይሆናል፡፡

ምርጫ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሕዝብ ፈቃድ የሚገለጽበትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንቢያ ኹነኛ መንገድ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከተገነባ ደግሞ ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ እንዲሁም ተጠቃሚነት ይረጋገጣል፡፡ ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሲረጋገጥም ሀገር በዕድገት ጎዳና የምታደርገው ጉዞ ይፋጠናል፡፡

ይሁን እንጂ፣ የምርጫ ሂደት በድምፅ መስጠት ወይም በውጤት ማስታወቂያ ብቻ አይጠናቀቅም። ከዚያ በኋላ የሚከናወኑ የውጤት ቆጠራ፣ የውጤት ማረጋገጫ፣ የቅሬታ አቀራረብና የውሳኔ ሂደቶች የምርጫው ወሳኝ ክፍሎች ናቸው። ምርጫ ቦርድ እነዚህን ሂደቶች  በነፃነት፣ በገለልተኝነትና በግልጽነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

የድህረ ምርጫ ወቅት የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ብስለት፣ የተቋማት ጥንካሬና የፖለቲካ ባህል የሚፈተንበት ወሳኝ ጊዜ ነው።      ስለሆነም ይህ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ከምርጫ ማግስትም (ድህረ ምርጫ) መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ተግባራዊነት ደግሞ  የመጨረሻ ውጤት ይፋ የማድረግ ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋ የሚያደርገውን ውጤት  በጸጋ መቀበል፣ የመራጩን ሕዝብ አደራ ተቀብሎም ከአሸናፊው ፓርቲ ጋር  ለሀገር ልማት በጋራ መሥራት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡   ማሸነፍም ኾነ መሸነፍ የሚወሰነው በዜጎች ነጻ ድምጽ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የምርጫ ውጤቱን በጸጋ መቀበል እንዳለ ኾኖ ቅሬታ ካለም ቅሬታን ሕጉን ጠብቆ ለቦርዱ በማቅረብ  እንዲፈታ በማድረግ  የዴሞክራሲ ባህልን ማሳደግና ለሀገር ልማት በጋራ መሥራት ይገባል፡፡ የሀገር ሰላምን ከፓርቲ ጥቅም በላይ ማስቀደም የሁሉም ፖለቲካዊ ተዋናዮች ቀዳሚ ኃላፊነት መሆን አለበት።

የብዙኃን መገናኛ አውታሮችም ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና የተረጋገጠ መረጃ ለሕዝብ ማድረስ አለባቸው። ከግምት፣ ከወሬና ከማይታመኑ ምንጮች የሚመነጩ መረጃዎችን ማሰራጨት የሕዝብን መረጋጋት ሊያናጋ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሕጋዊ የቅሬታ ሥርዓቶችን ለሕዝብ በማብራራት የሰላም ግንባታ ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል።

መራጩ ሕዝብና ሲቪክ ማኅበራትም  ውጤት እስኪገለጽ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅና የምርጫ ቦርድን ይፋዊ መግለጫዎች መከታተል አለባቸው፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በርካታ ተግባራትን ለማከናወንና ሕዝቡ እያጋጠሙት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ቃል ገብተዋል። ከምርጫ ማግስት ታዲያ ይህ ቃል መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ አሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ ሕዝቡ የመረጠው ችግሮችን ይፈታልኛል፤ በዕድገት ጎዳና ያራምደኛል ብሎ በማሰብ እንደኾነ ተገንዝቦ ከሕዝቡ የተጣለበትን አደራ ለመወጣት መሥራት ይገባዋል፡፡ በተለይ የኑሮ ውድነቱ መራጩን ሕዝብ በእጅጉ  እየፈተነ መሆኑን በማጤን ተመራጩ የፖለቲካ ፓርቲ በትኩረት መሥራት ይኖርበታል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥም ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሕዝብ በሰላም ወጥቶ ያለ ስጋት በሰላም እንዲገባ፣ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር ተግቶ መሥራት ከምርጫ ማግስት ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት ናቸው፡፡

በኲር የሰኔ 1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here