“አንድ የደም ጠብታ አንድ ሕይወት ያድናል”

0
8

የደም ልገሳ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለማዳን የሚያገለግል ከፍተኛ ሰብአዊ ተግባር ነው። በኢትዮጵያም በየቀኑ በአደጋ፣ በቀዶ ጥገና፣ በካንሰር ሕክምና እና በወሊድ ጊዜ ደም የሚያስፈልጋቸው በርካታ ታካሚዎች አሉ። ለእነዚህ ሰዎች ተስፋ የሚሆነው በፈቃደኝነት ደም የሚለግሱ ዜጎች ናቸው።

በዚህ መልካም ተግባር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ካሉ ሰዎች መካከል የባህርዳር የደም ልገሳ አምባሳደር አንዷ ናት። ከ45 ጊዜ በላይ ደም በመለገስ እና በርካታ ወጣቶችን ወደ ደም ልገሳ በማምጣት የሕይወት አድን ተግባር እየፈጸመች ትገኛለች። ስለ ሕይወቷ፣ ስለ ደም ልገሳ ጉዞዋ እና በማህበራዊ ተሳትፎዎቿ ዙሪያ ከወጣት ፍሬሕይወት ሙስጦፋ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲያነቡ በአክብሮት እንጋብዛለን።

 

በመጀመሪያ ለቃለመጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆንሽ እያመሰገንኩ፣ ራስሽን አስተዋውቀሽ በአጭሩም ትውልድ እና እድገትሽን ለአንባቢዎቻችን ግለጪልን?

እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ። ፍሬሕይወት ሙስጦፋ እባላለሁ፤ የተወለድሁትና ያደግሁት በባህርዳር ከተማ ነው። ከተማዋ በተፈጥሮ ውበቷ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ትስስሯ እና በሰዎቿ ደግነት የምትታወቅ ናት። በዚህ አካባቢ ማደጌ በሕይወቴ ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድሮብኛል። በዚያ ያሉ ሰዎች እርስ በርስ የሚረዳዱ፣ ያላቸውን የሚያካፍሉ እና ለጎረቤታቸው የሚቆሙ ናቸው።

ቤተሰቤም በተመሳሳይ መልኩ የሰውን ልጅ የሚያከብር ቤተሰብ ነው። እናቴና አባቴ በአካባቢያችን በደግነታቸው፣ በርህራሄያቸው እና ያላቸውን ከሌላቸው ጋር በመጋራት ባህላቸው የሚታወቁ ነበሩ። ከእነሱ የተማርኩት ትልቁ ነገር ሰውን መውደድ እና ለሌሎች መኖርን ነው። ዛሬ የምሰራው ማንኛውም የበጎ ፈቃድ ሥራ መሰረቱ ከዚያ አስተዳደግ የመጣ ነው።

በማህበራዊ ሥራዎች ውስጥ ተሳትፎሽ መቼ ተጀመረ?

በልጅነቴ ጀምሮ ነው። በሰርፀ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በምማርበት ወቅት በትምህርት ቤት በተለያዩ ክበቦች እሳተፍ ነበር። በፀረ ኤች አይቪ ቡድኖች፣ በተማሪዎች ማህበራት እና በልዩ ልዩ የትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች ተሳትፌያለሁ።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃላፊነት መውሰድን ተማርኩ። በሚኒ ሚዲያዎች ተሳትፌያለሁ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሰርቻለሁ፤ በትምህርት ቤት ውስጥም የተለያዩ ክበቦችን በማቋቋም ተሳትፌያለሁ። እነዚህ ተሞክሮዎች ማህበረሰብን የማገልገል ፍላጎቴን የበለጠ አጠናክረውታል።

 

የደም ልገሳ ጉዞሽ እንዴት ተጀመረ?

የደም ልገሳ ጉዞዬ በ2006 ዓ.ም. አካባቢ ተጀምሯል። በዚያ ወቅት ከፀረ ኤች አይቪ ቡድናች ጋር በመተባበር የታመሙ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል እየወሰድን እንረዳ ነበር። አንድ ቀን ከገጠር የመጣች እናት አስቸኳይ ደም እንደሚያስፈልጋት ተነገረን። ነገር ግን ቤተሰቦቿ ደም ለመለገስ ፈርተው ነበር።

ያኔ  “ለምን እኔ አልለግስም?” ብዬ አሰብኩ። በፈቃደኝነት ሄጄም ደም ለገስኩ። ይህ የመጀመሪያ ልገሳዬ ነበር። በኋላ ግን የሕይወቴ አካል ሆነ።

ያቺ እናት በሰላም ወለደች፤ ልጇንም አየች። ቤተሰቧ በጣም ደስተኞች ነበሩ። ያኔ አንድ ሰው በቀላሉ የሚያደርገው ተግባር የሌላን ሰው ሕይወት ሊያድን እንደሚችል በተግባር ተረዳሁ።

እውነቱን ለመናገር ያ ቀን እኔንም ቀይሮኛል። ደም መለገስ የሰው ልጅ ሕይወትን የሚያድን ቅዱስ ተግባር መሆኑን ተረዳሁ።

 

እስካሁን ያደረግሻቸው ልገሳዎች ምን ያህል ናቸው?

እስካሁን ከ45 ጊዜ በላይ ደም ለግሻለሁ። ይህ ቁጥር ለእኔ የሚያስደስት ቢሆንም እንደ መጨረሻ አላየውም። ጤንነቴ እስከፈቀደልኝ ድረስ መለገሴን እቀጥላለሁ።

ሌሎችን ለማበረታታት ምን ዓይነት ሥራ እየሰራሽ ነው በምን መልኩስ እየተንቀሳቀስሽ ነው?

መጀመሪያ ራሴ በተግባር ምሳሌ ለመሆን እሞክራለሁ። ከዚያ በኋላ ጓደኞቼን፣ ቤተሰቦቼን እና ተከታዮቼን እንዲለግሱ እጋብዛለሁ። በፌስቡክ እና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች የደም ልገሳ ፉክክር(challenges) እናዘጋጃለን።

አንድ ሰው ሌላ ሦስት ሰዎችን ሲጋብዝ፣ እነሱም ሌሎችን ሲጋብዙ ተጽእኖው በጣም ይሰፋል። የደም ልገሳ ባህል እንዲያድግ ይህ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

 

ወጣት ፍሬሕይወት እስኪ በዚህ የደም ልገሳ እና የማስተባበር ጉዞሽ የማይረሱ ትዝታዎች ካሉሽ አጫውቺን?

ከብዙ ትዝታዎች አንዱ አንድ ጓደኛዬ ደም መለገስ ከባድ ነው ብሎ ሲያስብ ነበር። አንድ ቀን አበረታታነውና ለመጀመሪያ ጊዜ ለገሰ። ከዚያ በኋላ “ለምን  ቀላል መሆኑን ቀደም ብለሽ አልነገርሽኝም?” አለኝ።

ይህ በጣም አስደስቶኛል። ምክንያቱም ሰዎች በፍርሃት የሚርቁትን ነገር በተግባር አይተው ሲቀበሉት ማየት በጣም ያስደስታል።

የሚያሳዝን ገጠመኝም አለኝ። አንድ ጊዜ የደም እጥረት በነበረበት ወቅት አንድ አባት ወደ ደም ባንክ መጥቶ “ልጄ ልትሞት ነው፤ አንድ ተጨማሪ የO ኔጌቲቭ ደም ያስፈልጋታል” ብሎ ሲማጸን አይቻለሁ።

ያን ጊዜ በጣም አዝኜ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ለመርዳት ፍላጎቱ ቢኖርህም ሁሉን ማድረግ አትችልም። እነዚህ ሁኔታዎች የደም ልገሳ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስታውሱኛል።

ደም መለገስን እንደ ሕይወት ዘይቤ እንድትቀበይው ያነሳሳሽ ምንድን ነው?

እኔ ሁልጊዜ እንደማስበው ደም መለገስ በጎ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ለሌላ ሰው ሕይወት መድኃኒት መሆን ማለት ነው። እኛ ጤናማ ሰዎች ሆስፒታል የምንሄደው ለምርመራ ወይም ለመለገስ ሊሆን ይችላል፤ በሆስፒታል ውስጥ ግን በሕይወትና በሞት መካከል ያሉ በርካታ ሰዎች አሉ። የቀዶ ጥገና ታካሚዎች፣ የካንሰር ሕመምተኞች፣ የኩላሊት ታካሚዎች፣ እንዲሁም ነፍሰ ጡር እናቶች ከእኛ የሚገኘውን ድጋፍ በተስፋ ይጠብቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር የሰጠንን ጤና ለሌሎች ሕይወት መታደግ ማዋል ይገባናል በሚል ነው።

አንዳንድ ሰዎች ደም መለገስ የጤና ችግር ያመጣል ብለው ይፈራሉ። አንቺ ምን ትያለሽ?

ይህ በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚገኝ ስጋት ነው። እኔ ግን ከራሴ ልምድ እና ከጤና ባለሙያዎች ምክር በመነሳት ደም ልገሳ የሚከናወነው በጥንቃቄ እና በሙያዊ ሂደት ነው ብዬ እናገራለሁ። ከመለገስ በፊት ሰውየው ምግብ መብላቱ፣ የጤና ሁኔታው፣ የሚወስደው መድኃኒት እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ይጣራሉ። ከዚያም የደም ግፊትና ሌሎች መለኪያዎች ይፈተሻሉ። ስለዚህ የባለሙያዎችን መመሪያ ተከትሎ የሚደረግ ደም ልገሳ ከባድ የጤና ችግር አያስከትልም።

እኔ ራሴ ከ45 ጊዜ በላይ ደም ለግሻለሁ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ በደም ልገሳ ምክንያት የደረሰብኝ የጎንዮሽ ጉዳት የለም።

 

የወጣቶች ተሳትፎ ጨምሯል ብለሽ ታስቢያለሽ?

በጣም የሚያበረታታ ሁኔታ እያየን ነው። በተለይ በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ወጣቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተሳተፉ ናቸው። ከቀድሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የግንዛቤ ደረጃው በጣም ተሻሽሏል። “ደም መለገስ አይጎዳኝም፤ ለሌላ ሰው ሕይወት ያበረክታል” የሚለው አመለካከት እየተስፋፋ ነው።  ይህ የሚያሳየው የበጎ ፈቃድ ባህል እያደገ መሆኑን ነው። ነገር ግን ብዙ ይቀራል፤ ምክንያቱ የደም ፍላጎት በየቀኑ እየጨመረ ነው። የትራፊክ አደጋዎች፣ የቀዶ ጥገና ታካሚዎች፣ የካንሰር ሕመምተኞች፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና ሌሎች በርካታ ታካሚዎች ደም ይፈልጋሉ። ስለዚህ አንድ ጊዜ መለገስ ብቻ በቂ አይደለም። ደም ልገሳ ቀጣይነት ያለው ተግባር መሆን አለበት።

 

ይህን ባህል ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት?

ትምህርት ቤቶች ቁልፍ ሚና አላቸው። የደም ለጋሾች ክበባት መቋቋም፣ የግንዛቤ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት እና ወጣቶች በተግባር እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከትምህርት ቤት ውጪም የበጎ ፈቃድ ማህበራትና የማህበረሰብ ቡድኖች ይህን ባህል ማስፋፋት ይችላሉ።

 

የባህርዳር ደም ባንክ አምባሳደር መሆን ማለት ለአንቺ ምን ማለት ነው?

ይህ ለእኔ ክብር ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ነው። ሰዎችን ስለ ደም ልገሳ ማስተማር፣ ማበረታታት እና በራሴ ተግባር ምሳሌ መሆን አለብኝ።

የደም ልገሳ ባህል እንዲስፋፋ መሥራት የእኔ ዋና ተልዕኮ ነው።

 

እንደ የደም ልገሳ አምባሳደርነትሽ ምን ዓይነት ሥራዎችን ትሰሪያለሽ?

በትምህርት ቤቶች፣ በወጣቶች መድረኮችና በማህበራዊ ሚዲያ ደም ልገሳን አስተዋውቃለሁ። የራሴን ልምድ እካፍላለሁ። ከ45 ጊዜ በላይ መለገሴ ብዙ ሰዎችን ለማነሳሳት አግዞኛል።

 

የወደፊት ዕቅድሽ ምንድን ነው?

ወደፊት ቋሚ ደም ለጋሾችን ቁጥር ማሳደግ ነው። ሆስፒታሎች እና የደም ባንኮች የደም እጥረት እንዳያጋጥማቸው እፈልጋለሁ። ማንኛውም ታካሚ ደም ሲያስፈልገው በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችል ማህበራዊ ባህል እንዲፈጠር እሠራለሁ።

በመጨረሻም ለወጣቶች ምን መልእክት ይኖርሻል?

ሁላችንም የሰው ሕይወት ለማዳን ማድረግ የምንችለው ነገር አለ። ደም መለገስ ቀላል ነው፤ ነገር ግን ውጤቱ ትልቅ ነው። አንድ የደም ጠብታ አንድ ሕይወት ሊያድን ይችላል።

ስለዚህ ወጣቶች ለማህበረሰባቸው እንዲቆሙ፣ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች እንዲሳተፉ እና የደም ልገሳን እንደ ሕይወት አዳኝ ተግባር እንዲመለከቱት እጠይቃለሁ። ሰውን መርዳት ከሁሉም በላይ የሚያስደስት ተግባር ነው። ዛሬ ለሌላ ሰው የምታደርጉት ትንሽ መልካም ነገር ነገ አንድን ቤተሰብ ከሀዘን ሊያድን ይችላል። ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው ማህበረሰባችንን የበለጠ ሰብዓዊ፣  ሰውን አፍቃሪ እና ተስፋ የሞላበት ማድረግ የምንችለው።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሰኔ  8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here