“የእግዜር እጅ”

0
121

ዓለም አቀፉ የስፖርት ትኩሳት ጣሪያ በነካበት በዚያ እጅግ ሞቃታማ የሰኔ እሁድ ቀትር በሜክሲኮው አዝቴካ ስታዲየም የተሰበሰቡ ከ114 ሺህ በላይ ተመልካቾች የስፖርት ታሪክን ለዘላለም የሚቀይር ክስተት እንመለከታለን ብለው አልገመቱም ነበር፡፡ በ1986 እ.አ.አ አርጀንቲና እና እንግሊዝ የፍጻሜውን ጨዋታ ከማከናወናቸው አራት ዓመታት ቀደም ብሎ ሁለቱ ሀገራት እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነት አድርገዋል፡፡

የጦርነቱ መነሻ ደግሞ ሁለቱም ሀገራት የፎክላንድ ደሴቶች የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት  እንደነበር የቢቢሲ ስፖርት  መረጃ       ያመለክታል፡፡ ግጭቱ  ሙሉ በሙሉ ወደ ጦርነት የተቀየረው አርጀንቲና ደሴቶቹን በኃይል ስትወር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በ74 ቀናቱ ጦርነትም 649 አርጀንቲናውያን እና 255 እንግሊዛውያን ወታደሮች ህይወታቸውን መጣታቸው ይነገራል፡፡

አርጀንቲና ጦርነቱን መሸነፏ በሕዝቧ ልብ ውስጥ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ታዲያ ሁለቱ ሀገራት በሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ በፍጻሜ ሲገናኙ አርጀንቲናውያን ለበቀል ጥርሳቸውን ነክሰው ወደ ሜዳ መግባታቸውን I am the Diego የተሰኘው የዲዬጎ ማራዶና የግል የህይወት ታሪክ ያስነብባል፡፡

የአርጀንቲና እና የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በወቅቱ ፍጹም የተለያየ የእግር ኳስ ፍልስፍና እና ማንነት የነበራቸው ሀገራት ነበሩ፡፡

የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በጠንካራ ስነ ስርዓት፣ በአካላዊ ብቃት፣ በረጅም ኳሶች እና በኮከቦቻቸው የተገነባ ቀጥተኛ እና አይበገሬ ስብስብ ነበር፡፡ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በላቀ የኳስ ጥበብ፣ አጭር፣ ፈጣን ቅብብል እና በማንኛውም ቅጽበት ጨዋታን መለወጥ በሚችሉ የግል ባለተሰጥኦዎች ላይ የተመሰረተ ቡድን እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የእግር ኳስ ጠበብቱ ዲያጎ ማራዶና በግል የህይወት ታሪክ መጽሀፉ “ይህ ጨዋታ ለእኛ ተራ የእግር ኳስ ግጥሚያ አልነበረም፤ ከጨዋታው በፊት ይህ ስፖርት ነው ከጦርነቱ ጋር አይገናኝም እያልን ብናወራም በውስጣችን  ግን በጦርነቱ የሞቱትን አርጀንቲናውያን ወጣቶች እንናፍቅ ነበር” ይላል፡፡ ይህ የበቀል ስሜት ታዲያ በስታዲየሙ መልበሻ ክፍል መተላለፊያ (ታናል) ላይ በነበሩት የአርጀንቲና ተጫዋቾች ዐይን ውስጥ በግልጽ ይነበብ እንደነበር ዘ ሰን ያስታውሳል፡፡

ጦርነቱም ጨዋታው ገና ሳይጀመር  በቃላት ተጀምሯል፡፡ የወቅቱ የእንግሊዙ አሰልጣኝ የነበሩት ቦቢ ሮብሰን የማይጨበጠውን ዲያጎ ማራዶናን መፈናፈኛ ለማሳጣት አለ ያሉትን ዘዴ ሁሉ አዘጋጅተው እንደነበር የቢቢሲ መረጃ አመልክቷል፡፡ ቴሪ ፌንዊክ፣ ቴሪ ቡቸር እና ፒተር ሬይድ ማራዶናን በሄደበት ሁሉ እንደ ጥላ ለመከተል ጥብቅ መመሪያ የተሰጣቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ተሳክቶላቸውም እንግሊዛውያን የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለምንም ግብ አጠናቀቁ ፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ግን የእግር ኳስን ታሪክ  ሙሉ በሙሉ የቀየረ ትልቅ ክስተት ይዞ ተጠናቀቀ፡፡

በ51ኛው ደቂቃ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ኳሷን ከመሀል ሜዳ በማንከባለል ወደ ተጋጣሚያቸው የፍጹም ቅጣት ምት ክልል ይዟት ይገሰግሷል፤ እንግሊዛዊው አማካይ ስቲቭ ሆጅ ኳሷን ለማምከን እና መከላከል ያደረገው ሙከራ ይበልጥ ለምትሀተኛው አጥቂ በአየር ላይ አመቻችቶ አቀብሎታል፡፡ ነገር ግን አርጀንቲናዊው ጥበበኛ ከእንግሊዛዊው ግብ ጠባቂ ፒተር ሺልተን ጋር በቁመት አጭር በመሆኑ በግራ እጁ ኳሷን ከግብ ጠባቂው ቀድሞ  በመምታት ከመረብ ጋር አገናኝቷታል፡፡

በወቅቱ ጨዋታውን ይመራ የነበረው ዋና ዳኛ ዓሊ ቢን ናስር በግንባር የተገጨች ግብ መሰሏቸው ግቧን አጸደቁ፡፡ ማራዶናም ከጨዋታ በኋላ “ግቧ በከፊል በማራዶና ራስ፣ በከፊል ደግሞ በአምላክ እጅ የተቆጠረች ናት” በማለት ለዘላለም የሚታወሰውን ስያሜ እንድታገኝ ሀሳብ አዋጥተዋል፡፡

ዓለም በመጀመሪያዋ ግብ ተገርሞ ሳያበቃ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ (በ55ኛው ደቂቃ) ታምረኛው የእግር ኳስ ሊቅ በትውልድ የማይደበዝዝ ሌላ ድንቅ ታሪክ ፈጠረ፡፡ ከአርጀንቲና የሜዳ ክልል ውስጥ ኳስ በመቀበል በአስገራሚ ፍጥነት እና ድንቅ ክህሎት አምስት የእንግሊዝ ተጫዋቾችን (ሆድል፣ ሪድ፣ ሳንሰም፣ ቡቸር እና ፌንዊክን) እንደ ቅጠል አራግፎ እና ግብ ጠባቂውን ሺልተንንም ጭምር በማታለል ሁለተኛዋን ግብ አስቆጠረ፡፡

ይህች ግብ ከዓመታት በኋላ በፊፋ የሕዝብ ድምፅ “የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ግብ” (Goal of the Century) ተብላ መመረጧ አይዘነጋም፡፡ ማራዶናም በአራት ደቂቃ ልዩነት እጅግ ያማረች ግብ ያስመዘገበ ብቸኛ ሰው ሆነ፡፡ ጨዋታውም በአርጀንቲና ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ከጨዋታው በኋላ  ማራዶና ማለት ለእንግሊዛውያን የእግር ኳስን ሕግ የጣሰ እና ያታለለ “ከሃዲ” ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ እንግሊዛዊው ግብ ጠባቂ ሺልተንም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድርስ ይቅር እንዳላለው ዘ ሰን አስነብቧል፡፡  በአንጻሩ ለአርጀንቲናውያን በጦርነት  ላጧቸው ክብር መለኮታዊ በቀል ተደርጎ ተወሰደ፡፡

እ.አ.አ በ2015 ማራዶና ወደ ቱኒዚያ በመጓዝ ያቺን ግብ ያጸደቁለትን ዳኛ ዓሊ ቢን ናስርን ቤታቸው ድረስ ሄዶ ጎበኛቸው፤ “ለዘላለም ጓደኛዬ ነህ” የሚል ጽሑፍ ያለበትን ማሊያም በስጦታ እንዳበረከተላቸው መረጃዎች አስነብበዋል፡፡ በ2022 እ.አ.አ ደግሞ ማራዶና በዚያ ቀን የለበሳት ሰማያዊ ማሊያ በጨረታ ቀርባ ከዘጠኝ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጠች፡፡ ይህም በወቅቱ በስፖርት ታሪክ እጅግ ውድ ዋጋ የተሸጠ ዕቃ ሆኖ ክብረ ወሰን ሰብሯል፡፡

በዚያች ግብ ምክንያት በአርጀንቲና ምድር የማራዶና ዝና ወደ እምነት ተቀይሯል፡፡ በ1998 እ.አ.አ በአርጀንቲና “የማራዶና ቤተክርስቲያን” መመስረቱን ያስነበበው ቢቢሲ ስፖርት፡፡ አማኞቹ የጊዜ አቆጣጠራቸውን ማራዶና ከተወለደበት እ.አ.አ 1960 እንደሚጀምሩ ተነግሯል፤ ሰኔ 22ን (የእግዜር እጅ ግብ የተቆጠረችበትን ቀን) እንደ ታላቅ በዓል ያከብራሉ ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏት ይህች ተቋም ማራዶና በአርጀንቲናውያን ዘንድ ከስፖርተኛነት አልፎ እንደ አምላክ መታየቱን ማረጋገጫ ናት ይላል መረጃው፡፡

ማራዶና እ.አ.አ በ2020 ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም “የእግዜር እጅ” ግብ ግን በእግር ኳስ ስፖርት ሁሌም የምትታወስ ግብ መሆኗን በመጠቆም ዘ ሰን መረጃውን ይቋጫል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 15   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here