የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሀገሪቱን የሩጫ ባህል ለማዘመን እና ስፖርቱን ወደ ክልል ከተሞች ለማስፋፋት አዲስ ስትራቴጂ ነድፏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የጎዳና ላይ ሩጫ ወደ ክልል ዋና ዋና ከተሞች ማውረድ ተችሏል፡፡ በየክልሉ ያሉ አዳዲስ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እና የስፖርቱን ተደራሽነት ለማስፋፋት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በዙር እንደገና በተከታታይ እያካሄደ ይገኛል፡፡ ውድድሩ በሀገሪቱ የአትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታላቅ ስፖርታዊ ሁነት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ይህ አዲስ ጅምር ግን “አትሌቲክስ ለሁሉም” የሚለውን መርህ በተግባር እየተረጎመ ይገኛል፡፡ በመቀሌ ተጀምሮ፣ በሐዋሳ ቀጥሎ፣ በባሕር ዳር ከሰሞኑን የተደረገው ይህ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ስፖርቱ ከውድድርነቱ ባለፈ የሕዝብ ግንኙነት እና የቱሪዝም ገጽታን የመገንባት አቅም እንዳለውም አሳይቷል፡፡
ውድድሩ መጀመሩ በአካባቢው ለሚገኙ በርካታ ወጣት አትሌቶች እና ስፖርት አፍቃሪዎች ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡
በመቀሌ የተደረገው መርሃ ግብር በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ወጣት ተተኪ አትሌቶች ተሰጥኦአቸውን እንዲያሳዩ እና አዳዲስ የውድድር ዕድሎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ረገድ ታሪካዊ ተልዕኮውን ተወጥቷል፡፡
የሐዋሳው ውድድርም በከፍተኛ ፉክክር የታየበት እንደነበር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያስነብባል፡፡
የመድረኩ ሦስተኛ ዙር ውድድር ደግሞ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡ ከጣና ሐይቅ እና ከዓባይ ወንዝ የሚነሳው ቀዝቃዛ ነፋስ አትሌቶቹን ከከፍተኛ ሙቀት የታደገ ቢሆንም የአትሌቶቹን የጽናት ብቃት ግን የፈተነ ነበር፡፡ በባሕር ዳር ከተማ የተደረገው አንደኛው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ከ11 ክለቦች የተውጣጡ 104 አትሌቶች ተሳትፏል፡፡ በውድድሩ እንደ ንግድ ባንክ፣ አማራ ማረሚያ፣ ዋሊያ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያሉ ክለቦች ተሳትፈዋል፡፡
በሴቶች ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ አትሌቶች በቡድን ታክቲክ በመምራት እና ፍጥነታቸውን በመቆጣጠር የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል፡፡ በወንዶች ደግሞ የአማራ ቤት አትሌቶች የወርቅ እና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆኑ ዳባት እንዳልክ ቀለመወርቅ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ደግሞ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ለወጡ አትሌቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡
አሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ማረሚያ ቤቶች አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ ክፍሌ ውድድሩ በክልል ከተሞች መደረጉ እድሉን ያለገኙ ባለተሰጥኦ አትሌቶችን ያነሳሳል ብለዋል፡፡ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በክልል ከተሞች መካሄዱ አዳዲስ ተሰጥኦዎችን በቀላሉ ለማግኘት፣ የስፖርት ቱሪዝምን ለማነቃቃት፣ ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት እና የስፖርት ተደራሽነትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ፍትሐዊ ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
“በተለይም በክልላችን እምቅ አቅም እያላቸው ነገር ግን የመወዳደር ዕድል አጥተው የቆዩ ወጣቶችን ወደ አደባባይ ለማውጣት ይህ ውድድር አይነተኛ ሚና ተጫውቷል” ብለዋል አሰልጣኙ፡፡ አሰልጣኙ “ባሕር ዳር ዳገት እና ቁልቁለት የሌለው ለጥ ያለ አስፋልት በመሆኑ አትሌቶች እስካሁን ድረስ ከተሮጠው ሩጫ በጣም የተሻለ ሰዓት የሮጡት እዚህ ነው” ብለዋል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ የአንጋፋው አትሌት ጀማል ይመር መሳተፍ ለውድድሩ የተለየ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡ እንደ ጀማል ያሉ በዓለም አቀፍ መድረክ ስማቸው የገነነ አትሌቶች በክልል ከተሞች በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ሲገኙ፣ ወጣት አትሌቶች “እኛም እንደነሱ መሆን እንችላለን” የሚል ተስፋ እንዲያሳድሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ የልምድ ልውውጥ በአካል መታየቱ ከማንኛውም ስልጠና በላይ ለወጣቶቹ የስነ ልቦና ጥንካሬን የሚሰጥ ነው፡፡
ውድድሩ በክልሉ የሚገኙ ወጣት አትሌቶች ብቃታቸውን እንዲያሳዩ ትልቅ በር ከፍቷል፡፡ ወደፊትም ዓለም አቀፍ ስፖርት ማኔጀሮች፣ ወኪሎች እና ታዋቂ አሰልጣኞች ወደ ክልሉ መጥተው አዳዲስ አትሌቶችን እንዲመለከቱ እና እንዲመልምሉ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ጠንካራ መሠረት ጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ የላቀ እና ማኔጀሮችን በስፋት መሳብ የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጎዳና ላይ ውድድር በዘላቂነት ለማዘጋጀት በርካታ ተግባራዊ እርምጃዎች መወሰድ ግን ይኖርባቸዋል ነው የተባለው፡፡
ውድድሩ ምንም እንኳ ስኬታማ የነበረ ቢሆንም ወደፊት መታረም ያለባቸው ክፍተቶች እንደነበሩ አሰልጣኙ አልሸሸጉም፡፡ አትሌቶች ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሲንቀሳቀሱ የሚገጥማቸው የትራንስፖርት ድካም በውጤታቸው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡
ስለሆነም ፌዴሬሽኑ ከግል ባለሀብቶችና ከትራንስፖርት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለአትሌቶች ብቻ የተለየ የጉዞ አገልግሎት ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡
በተለይም የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ችግሮችን ለመቅረፍ ራሱን የቻለ የሰርቪስ አገልግሎት መዘጋጀት እንዳለበት እና ውድድሩ ራሱን ችሎ መቆም እስኪችል ድረስ የሚመለከተው አካል ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በርካታ ብቃት ያላቸው አትሌቶች ቢኖሩም በትራንስፖርት ችግር እና በበጀት እጥረት ምክንያት ክለባቸው (አማራ ማረሚያ ቤቶች) ሁሉንም አትሌቶች ማሳተፍ ሳይችል እንደቀረ አሰልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ ነግረውናል፡፡
በአጠቃላይ በባሕር ዳር ከተማ የተደረገው ይህ ውድድር የኢትዮጵያን አትሌቲክስ አንድ ደረጃ ከፍ አድርጓል፡፡ ከተማዋ ያሳየችው የማስተናገድ አቅም ወደፊት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮችን በባሕር ዳር ለማዘጋጀት ያላትን አቅም ያሳየ ሆኖ ተጠናቋል፡፡
ከዚህ የተሻለ እና የላቀ ውድድር በዘላቂነት ለማዘጋጀት ግን ለተወዳዳሪዎች ምቹ የሆኑ መንገዶችን መምረጥ ቀጣይ የቤት ሥራ ነው፡፡
የሽልማት መጠኖችን ማሳደግ፣ የሰዓት ምዝገባን ለማዘመን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ከግል ባለሀብቶች ጋር አጋርነት መፍጠር እና ውድድሩ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል- የአስልጣኝ ኮማንደር ደጀኔ አስተያየት ነው፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


