ረፍት ላይ የነበረች የሥራ ባልደረባዬን ለመጠየቅ ወደ ቤቷ ጎራ ባልኩበት ጊዜ የአምስት ዓመት እድሜ ከሆናት ልጇ ጋር ስትጨቃጨቅ ደረስኩ፡፡ አላግባባ ያላቸው ጉዳይም ልጇ በግምት ከቤታቸው ሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ ካለው የመጫወቻ ሜዳ ሄጄ እጫወታለሁ ማለቷ ሲሆን እናት ደግሞ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ “አለርጂክ”ሽ ይነሳብሻል እና አትሄጅም ማለቷ ነበር፡፡ በኋላ ግን ማልቀስ ስትጀምር ፈቀደችላትና እየቦረቁ ከሚገኙት እኩዮቿ ጋር ተቀላቀለች፡፡ እኔም በዛች ቅጽበት ቀጣዩ የጤና አምዴ ስለ አለርጂ ምንነት መሆን እንዳለበት እቅድ ያዝኩ፡፡
በእቅዴ መሠረትም በጥበበ ጊዮን ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም እና የሳንባ እና የፅኑ ሕሙማን ሐኪም ዶ/ር ብሩክ ሙላት ጋር ቆይታ አደረግሁ፡፡ ሐኪሙ እንዳብራሩት አለርጂ ሰውነታችን ምንም ጉዳት የማያደርሱ እንግዳ አካላትን እንደ በሽታ አምጪ ተህዋሳት ሲረዳ የሚፈጠር የጤና እክል ነው፡፡ እነሱን ለማስወገድ በሚያደርገው ጥረትም ሰውነታችን ይቆጣል፡፡ ሰውነታችንን እንዲህ የሚያስቆጡ እንግዳ አካላት ፤ በሕክምናው አለርጂ ቀስቃሽ አካላት ተብለው ይጠራሉ፡፡
ዶ/ር ብሩክ እንዳሉት ሰዎች ለብዙ ነገሮች አለርጂክ የመሆን እድል ይኖራቸዋል፡፡ ከበርካታ አለርጅኮች መካከልም አንዱ የመተንፈሻ አካላት አለርጅክ ነው፡፡ የመተንፈሻ አካል የሚባለውም ከአፍንጫ እስከ ሳምባ የሚደርሰው የሰውነታችን ክፍል ነው፡፡ ከአፍንጫ እስከ ጉሮሮ የላይኛው የመተንፈሻ አካል ሲባል፤ ከጉሮሮ እስከ ሳምባ የሚደርሰው ደግሞ ታችኛው የመተንፈሻ አካል ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ ከጉሮሮ እስከ ሳምባ የሚደርሰው ቱቦን ሊያወኩ የሚችሉ እና ሰላማዊ የአየር ዝውውር እንዳይኖር የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ከነሱም አንዱ አለርጂ ነው፡፡
አለርጂ የተለያዬ የሰውነት ክፍሎችን የማጥቃት እና የበሽታ ምልክቶችን የማምጣት እድል ቢኖረውም የመተንፈሻ አካላት አለርጂ የምንላቸው አፍንጫን ሊያጠቁ ይችላሉ፤ እንዲሁም ወደ ታች እየወረደ ሲመጣ ደግሞ ወደ አስም ሊቀየር ይችላል፡፡ ወደታች ማለት ወደ ሳምባ እና ወደ ሳምባ መተላለፊያ ቱቦዎች ወይም ብሮንካይትስ ይባላሉ፤ እነሱን እየያዘ ሲመጣ አስም እየሆነ ይመጣል ማለት ነው፡፡
የመተንፈሻ አካላት አለርጂ በምን ሊከሰት ይችላል?
የሙቀት እና የቅዝቃዜ መቀያየር በተለይም በቅዝቃዜ ስዓት የሰውነት የበሽታ የመከላከል ሥርዓቶች ምላሽ ይሰጣሉ ይህም ሕመም ይፈጥራል፡፡ የአየር ብክለት፣ የምንጣፍ ላይ መዥገሮች፣ አቧራ፣ መጥፎም ሆነ በጣም ከባድ ጥሩ ሽታ ሲከሰት አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ይነሳባቸዋል ማለት ነው፡፡ አበባ በብዛት በሚያብብበት በጸደይ ወቅት እንዲሁም ንፋስ አብዝቶ በሚነፍስባቸው ወራት ላይ እኝህ የአበባ ብናኞች አየር ላይ ስለሚበዙ አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ይቀሰቀስባቸዋል፡፡
ሻጋታም(mold) አለርጂ ይቀሰቅሳል፡፡ በቤቶችና በሕንፃዎች ውስጥ የሚፈጠር እርጥበት አዘል ሁኔታ ፤ ሻጋታ እንዲያድግ ያደርጋል፡፡ ያደገው ሻጋታ ዘር/ብናኝ በቤቶች እና ቢሮዎች ባለ አየር ላይ ይስፋፋል፡፡ ይህም በአከባቢው ባሉ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ አለርጂ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ከአንዳንድ የቤት እንሰስሳት ሰውነት የሚረግፉ የቆዳ ቅንጣቶች፣ የጸጉር እርጋፊዎች ፣ ፈሳሾች (ምራቅ ወይም ሽንት) አለርጂን ያመጣሉ፡፡
በተለይም ከክረምት ጋራ ተያይዞ በተለይ በአየሩ መቀዝቀዝ እና በአፈር ሽታ ምክንያት የሕመም ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ይበዛሉ ማለት ነው፡፡ በተለይም አስምን፣ ሳይነስን እና አለርጂ ራይናይተስን ይቀሰቅሳሉ፡፡
ሌላው የመተንፈሻ አካላት አለርጂ አንዱ አጋላጭ ምክንያት በማለት ባለሙያው ያብራሩት በቤተሰብ ያለ የአለርጂክ ታሪክን ነው፡፡ አለርጂ ካለባቸው እናት እና አባት የተወለደ ልጅ በአለርጂ የመያዝ አጋጣሚው ከፍ ያለ ነው፡፡ አለርጂ ያለበት አንደኛው ወላጅ ብቻ ከሆነ የልጁ በአለርጂ የመጋለጥ አጋጣሚ ከ20 በመቶ በላይ ይሆናል፡፡ ሁለቱም እናት እና አባት አለርጂ ያለባቸው ከሆነ ግን አጋጣሚው ከ50 በመቶ በላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ምልክቶቹ
አለርጂ እንዳለብዎ ለማወቅ፤ የአለርጂ ምልክቶችን ለይተው መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ዶ/ር ብሩክ እንዳሉት እንደየሰዉ፤ እንደየአለርጂ አይነቱም ምልክቶቹ ቢለያዩም ፤ በይበልጥ የሚታዩት የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንድ ሰው አስቸጋሪ ሽታ ከሸተተው በኋላ ቶሎ ቶሎ ማስነጠስ ሊኖረው ይችላል፡፡ አይን ማሳከክ እና ውሃ መቋጠር፣ ንፍጥ የሚመስል ነገር ወይም ደግሞ ውሃ መሳይ ፈሳሽ ከአፍንጫ መውጣት፣ ሲተነፍሱ ሲር ሲር የሚል ድምጽ መሰማት፣ ማሳል፣ አፍንጫ መታፈን፣ አፍንጫ ማሳከክ ወደ አስም እየተቀየረ ሲመጣ ወይም ደግሞ ታችኛውን የመተንፈሻ ክፍል ሲያጠቃ ትንፋሽ የማጠር ምልክቶችን ያሳያል፡፡
ሕክምናው
ባለሙያው እንዳስረዱት አለርጂው እንደአጠቃው የመተንፈሻ አካል አይነት ሕክምና ይደረግለታል፡፡ ብዙ ጊዜ ምርመራ ሳይደረግ በምልክቶቹ ማወቅ ይቻላል፡፡ የመጀመሪው ሕክምና የሚሆነው ግን በዋናነት አለርጂውን የሚያስነሳውን ነገር በተቻለ መጠን ለይቶ ለመከላከል መሞከር ነው፡፡ ሁለተኛው ወደ ሐኪም በመሄድ በመመርመር አለርጂኩ እንዳጠቃው የመተንፈሻ አካል አይነት የተለያዩ መድኃኒቶች የሚሰጡ ይሆናሉ፡፡ መድኃኒቶቹም አንዳንዶቹ ወደ ሳምባ የሚረጩ ሲሆኑ አንዳንዶቹ በአፍንጫ የሚወሰዱ ይሆናሉ፡፡ አልፎ አልፎም የሚዋጡ መድሃኒቶች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ እንደተጠቃው የሰውነት ክፍል መድኃኒት ይታዘዝለታል ማለት ነው፡፡ ሕክምናውም ሙሉ ለሙሉ አለርጂውን ማጥፋት ሳይሆን ሰውነታችን ለእነዚህ አለርጂዎች ምላሽ እንዳይሰጥ የሚያደርግ ነው፡፡ ይሁንና አንዴ በተሰጠ መድኃኒት ሙሉ ለሙሉ አለርጂውን ማጥፋት አይቻልም፡፡
በዋነኝነት ማን ላይ ይበረታል
የመተንፈሻ አካላት አለርጂ ሁሉንም የዕድሜ ክልል እና ጾታ የሚያጠቃ ቢሆንም በአብዛኛው ልጆች እና ወጣቶች ላይ በብዛት ይከሰታል፡፡ ይሁንና ሁሉንም የዕድሜ ክልል የማጥቃት ወይም ደግሞ ምልክት የማሳየት ነገር ይኖረዋል፡፡ በአብዛኛው በልጅነት ብዙ ጊዜ ወንዶች አለርጂ የሚኖራቸው ሲሆን ትንሽ እድሜያቸው ከፍ ሲል ደግሞ ሴቶችን የበለጠ የማጥቃት ነገር እንደሚኖረው ባለሙያው አብራርተዋል፡፡
መከላከያዎቹ
ዶ/ር ብሩክ እንዳስረዱት የመተንፈሻ አካላት አለርጂን መከላከል የሚቻለው በዋናነት አለርጂ የሚያስነሳውን ነገር ፈጽሞ በማስወገድ ነው፡፡
ጤና አዳም
አለርጂ ከሚያስከትሉ ነገሮች ለመራቅ፡-
- የቤትን ንጽሕና በደንብ መጠበቅ
- ንጹህ አንሶላ እና ትራስን መጠቀም
- ብናኝ እና አቧራ የሚይዙ ምንጣፎችንና ሌሎች እቃዎችን መቀነስ
- ከእንስሳት መራቅ
- ክፍሎችን በመደበኛነት አየር እንዲያገኙ ማድረግ
- ከጭስ መራቅ
- ሻጋታ እንዳይፈጠር መከላከል
- የአበባ ብናኝ ከፍ በሚልበት ወቅት ከቤት ውጪ ያለዎትን ቆይታ መቀነስ
- ማስክ መጠቀም
ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


