የሰው ጫማ

0
135

ፈተና ሲደርስ አብዛኛው ተማሪ ጅራቱን እየቆላ በአበጋዝ ዙሪያ ይሽከረከራል። ፈተና ሲያልፍ ደግሞ ሁሉም ጥግ ጥጉን ይዞ ወደማሽሟጠጡ ይመለሳል። የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች “በጭንቅላቱ የሚሮጠው አበጋዝ…” ይሉታል።

አበጋዝ ከእኔና ከሀና በቀር ሌሎች ተማሪዎችን ብዙ አይቀርባቸውም። እነሱም ቢሆኑ ፈተና ደርሶ ካልተጨነቁ በቀር አይጠጉትም፣ አያስጠጉትም።

ወደዩኒቨርሲቲ ከገባን ሦስት ዓመት ከመንፈቅ እየሆነን ነው። ልንመረቅ የቀረን ጊዜም ጥቂት ነው። አበጋዝ በዚህ ቆይታችን ቅርጽና ቀለማቸው ብቻ የሚቀየር ሁለት ሱሪዎች፣ አንድ ሸሚዝና ሁለት ሹራቦችን “እያፈራረቀ” ነው የሚለብሳቸው።

የአንደኛው ሱሪው ቀለም አረንጓዴ በመኾኑ ላይ ሁለቱ ጉልበቱና መቀመጫው ላይ በድግግሞሽ በመሰፋቱ አንበጣ የላሰው ቅጠል ነው የሚመስለው። ሸሚዙም ቢኾን ከቀበኛ የተረፈ ጨርቅ ነው የሚመስለው።

ጫማው እንደ ወሎ ላም ቀንድ ጫፉ ሽቅብ የቆመ ነው። እኔ የማውቃቸው ሦስት እንዲህ ዓይነት ቆዳ ጫማዎች አሉት። እነሱን ነው እያፈራረቀ የሚለብሳቸው።

ከ”ዶርም” ወደ “ካፌ”  አብረን ነው የምንሄደው። ከተማሪው በፊት ተነስተን “ካፌው” ሊዘጋ ሲል እንደርሳለን። አንዳንዶች “በጭንቅላቱ የሚሮጠው ልጅ ይሄ ነው…?” ሲሉ እሰማለሁ። ያልመጣልኝን ጨዋታ እያመጣሁ አበጋዝ እኔ የሰማሁትን እንዳይሰማ፤ ከሰማም ውስጡን እንዳይሰማው ለማድረግ እሞክራለሁ።

ከአበጋዝ ጋር የተቀራረብንበትና የተዋወቅንበት ቀን! ወደ ክፍል እየሄደ እያለ ዝናብ መዝነብ ይጀምራል። ቀስ ብሎ ተጉዞ፤ ዝናቡንም ጨርሶት በልብሱና በዚያ ጫማው ውሃ ተሸክሞ ወደ ክፍል ሲገባ ተማሪው በአንድ ድምጽ “እዋዋዋዋዋዋ….” ብሎ ሳቀበት።

ከአሁን አሁን ክፉ ቃል ይናገራል ወይ ደግሞ በብስጭት ከክፍል ወጥቶ ይሄዳል ብዬ ስጠብቅ በተማሪው ፊት ለፊት ቆሞ ሁላችንንም በዓይኖቹ እየቃኘ አንዴ ፈገግ ብሎ ወደመቀመጫው ሄደ።

ትምህርቱን ጨርሰን ከክፍል ስንወጣ አበጋዝ ከመቀመጫው አልተነሳም። መለስ ብዬ ሳየው ሀና ወንበር ስባ አብራው ተቀምጣለች።

ስደርስ ያ ጠንካራውና አይበገሬው አበጋዝ ዓይኖቹን ከሞላው ትኩስ እንባ ጋር እየታገለ ነው። እኔ እና ሀና የኾነውን ነገር ጠየቅነው። እኛ ብዙ ከጠየቅነው በኋላ እሱ አንድ ጥያቄ ብቻ ጠየቀን። “ሰው ግን ለምን በራሱ ላይ ይፈርዳል?” የሚል ጥያቄ።

“እንዴት?” አለች ሀና።

 

“ከመጸነስሽ በፊት ‘ሰው መኾን እፈልጋለሁ’ የሚል ጥያቄ ለፈጣሪሽም ኾነ ለወላጆችሽ አቅርበሽ ነበር?”

“በፍጹም!”

“እሽ ሌላው ሰውስ ወላጆቹን መርጦ ተወልዷል? ከእናት እና አባቴ ጋር ማደግ፣ መማር እና መኖር አልፈልግም ብሎ ለአምላኩ ደብዳቤ የሚጽፍ ሰው አለ?”

“የለም!” አለች ሀና ድምጿን ቀነስ አድርጋ።

“አያችሁ እኔም ሰው ነኝ። በመጀመሪያ እንደማንኛውም ሰው በወላጆቼ እና በፈጣሪ ፈቃድ ነው ወደዚህ ምድር የመጣሁት። ወላጆቼም ቢኾኑ ጨካኞች አልነበሩም። እንዲህ ከሰው በታች ያደረገኝ ክፉ ጊዜ ነው። ታናሽ እህቴን ጨምሮ እናትና አባቴን በመኪና አደጋ ያጣኋቸው የአሥረኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር።

በቤቱ የቀረኹት እኔና እኔ ብቻ ነኝ። ቤታችን ያላለቀ የባንክ እዳ ነበረበት፤ ባንኩ ቤቱን ሲሸጠው እኔ መንገድ ላይ ወደቅሁ። ወላጆቼ እያሉ ብዙ ዘመድ ነበረን። እነሱ ከሞቱ በኋላ ግን የዘመዱ ዝምድና አብሮ ሞተ።

የምለብሰውን ልብስና ጫማ የሚሰጠኝ ድሮ ከእኛ ቤት ተከራይቶ የነበረ አንድ መምህር ነው። አዲስ ጫማ የመግዛት ዐቅም ባይኖረውም የራሱን ጫማ ይሰጠኛል።

ሕይወት ያለ ወላጅ ከባድ ናት። አሁን አሁን ግን ከሕይወት በላይ የከበደኝ የሰው ነገር ነው። የውስጤን ሕመም የማዳምጥበትን እድል እንኳ ሊሰጠኝ አይፈልግም።

ደግፉኝ … አልብሱኝ…አጉርሱኝ አላልሁ… ይሄ ቀን ያልፍ ይኾናል ብዬ አንገቴን ደፍቸ ነው የምማረው። የማንንም ተማሪ መብት አልነካ… ሁሉም ቢረዱት እኮ እኔ ትናንት ከእነሱ በላይ እለብስ ነበር! ከእነሱ በላይ አጌጥ ነበር…”

ሀናን ቀና ብዬ አየኋት እያለቀሰች ነው። የአበጋዝን ዓይኖች ግን የማይበት ድፍረት አጣኹ። አንገቴን ወደ መሬት ሰብሬ እንባዬን አፈሰስኹት።

“ማጣት… ያውም ወላጆቹን እስከ ዘለዓለም ማጣት የሚፈልግ ሰው አለ? መቸገር የሚፈልግ ሰው አለ? ከሰው በታች መኾን የሚፈልግ ሰው አለ? እኔም ለሰው መጫዎቻና መዛበቻ መኾን’ኮ አልፈልግም። ግን ሰውና ፈጣሪ ተባብረው ከጨከኑ ምን ማድረግ ይቻላል!?

ዛሬ እናንተ በልብሴና በጫማዬ ትስቃላችሁ። አዲስ ልብስ ለብሸ እንደ እናንተ ከማሰብ ግን ይሄ አለባበሴ ይሻለኛል። የምማረውም ለዚህ አስተሳሰብ ሰለባ ላለመኾን ነው።

አውቃለሁ ስጓዝ ቀስ ብዬ ነው። የለበስኹት የሰው ጫማ ነውና። ያውም ቀለም ነክቶት የማያውቅ ቆርፋዳ ቆዳ ጫማ! ይሄንን ጊዜው ያለፈበትንና ከእግሬ መጠን በጣም የሚረዝም ሰፊ የሰው ጫማ ለብሸ ከሰው እኩል መራመድ አልቻልኹም።

 

ቀስ ብዬ መጓዙን ባልፈልገውም ቀስ ብዬ እንደምጓዝ ግን አውቃለሁ። ጫማው ከመቆርፈዱና ከመስፋቱ በላይ ሸፋፋ ነው። በአጭሩ ይሄ ጫማ እኔን ሳይኾን የሰጠኝን ሰው እግር ነው የሚመስለው።

ዛሬ እኔ የምጓዘው በሰው ጫማ ነው። የምራመደው በዚህ ጫማ አመል ነው። ብፈጥን ያደናቅፈኛል። ብሮጥ ይጥለኛል። በእያንዳንዱ እርምጃዬ እየተሳቀቅኹ ነው ያለኹት።

በሚደርስብኝ ያልተገባ የስነ ልቦና ጫና ምክንያት ትምህርቴን ማቋረጥ አልፈልግም። በዚህ ተልካሻ ምክንያትም በአለባበስ እንጂ በውጤትና በአመለካከት ከሰው በታች ለመኾን እጅ አልሰጥም።

አለባበሴ አምሮ አስተሳሰቤ እንዲጠቁር አልፈቅድም። ለፈተና እጅ አለመስጠትን በልጅነቴ አባቴ አስተምሮኛል። ደግሞ ሁሌ የሚገርመኝና የማምንበት ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን ለልጁ ኢድዋርድ በደብዳቤ የላከለት አንድ ምክር አለ።

“ልጄ! ሕይወት ልክ ሳይክል እንደማሽከርከር ናት! ወድቀህ ላለመቅረት ጉዞህን መቀጠል አለብህ…” የሚል ምክር።

“በወደቀ ሰው ላይ ምሳር ይበዛል” ከሚለው ሀገርኛ አባባል ይልቅ ለእኔ የአንስታይን ምክር ጉልበት ይሰጠኛል…” አለ አበጋዝ አሁን እንባዎቹን በመዳፎቹ ሲጠርጋቸው ቀና ብዬ አየኹት።

ከዚህ በፊት በአበጋዝ ኹኔታ ተሳልቄ አላውቅም። ቢኾንም ከክፍል ስወጣ ከጎኑ ያልቆምኹባቸው እነዚያ ዓመታት ግን ጸጸቱኝ። ከዚያ በኋላ ሀና እና እኔ ብቻ የአበጋዝ ምስጢረኞች ኾንን።

አሁን የመምረቂያ ጽሁፍ እያዘጋጀን ነው። ጽሁፉ የሚቀርብበት ጊዜም ሩቅ አይደለም። ተማራቂው ተማሪ በሙሉ ሱፍ እና ጫማ አሟልቷል። አበጋዝ ግን በእነዚያ ጨማዎችና ልብሶች የመመረቂያ ጽሁፉን ለማቅረብ በጉጉት እየጠበቀ ነው።

በእርግጥ የሰው ጫማ ተጫምቶ ማን እንደ ልቡ ይራመዳል? በሰው ሀሳብ ተነድቶስ ማን ሰው ይኾናል? ቢኾንም አበጋዝ እንደሚለው ዘመንን ሙሉ በሰው ሀሳብ ከማነከስ ለጥቂት ጊዜ በሰው ጫማ ማዝገም ሳይሻል አይቀርም።

ለዚህም በየመካከላችን ዛሬ ወድቀው ለነገ ትንሣኤ በጽናት የሚታገሉ ብዙዎች አሉ። እንደ ወርቅ የነጠረ ሀሳብ፣ እውቀትና አመለካከታቸውን አሮጌ ልብስ የሸሸገባቸውም ጥቂቶች አይደሉም። የነፍስና የመንፈስ ንጽሕናቸውን፣ ማጣት ያወየበባቸው ብዙዎች ናቸው!

“ክፉ ቀንን እና ቅዝምዝምን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ነው…” በሚል ማኅበረሰብ መካከል ዝቅ ብለው የሚረገጡ፤ ከራሳቸው አልፈው ለትውልድ የሚጨነቁ፣ ቁንጽል አስተሳሰብን ለመርታት አንጀታቸውን አጥፈው የሚተጉ አሉ።

ከእግር የሰው ጫማ በላይ ፤ በሰው የሀሳብ ጫማ ለዘለዓለም ሲዳክሩ ላለመኖር ዛሬ ላይ የሰው ጫማ ለብሰው እንደ አበጋዝ ቀስ እያሉ የሚራመዱ ግን ደግሞ በአቦ ሸማኔ ፍጥነት የሚያሰላስሉ ብዙ ሰዎች አሉ።

(አምሳሉ አሞኘ)

በኲር የሰኔ 15   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here