“ሰብስቦ የሚይዝ ጃንጥላ” አባትነት

0
69

አሜሪካዊያን በየዓመቱ በወርሐ ሰኔ ሦስተኛውን እሁድ ያከብራሉ። ይሄ ቀን የቤተሰብ አባላት ለአባቶች ያላቸውን ክብር የሚገልጹበት፣ አባቶችን በስጦታ የሚያንቆጠቁጡበት፣ ምግብ ቤቶች(ሬስቶራንቶ አባቶችን ለግብዣ ይዘው በወጡ ቤተሰቦች የሚጨናነቁበት ነው። ሂስቶሪ ዳት ካም (History.com) የተሰኘው ታሪክ መዝጋቢ አውታር የመጀመሪያው የአባቶች ቀን የተከበረው በጎርጎሮሳዊያኑ ሐምሌ 5/1908 እንደሆነ ይጠቁማል።

በወቅቱ በምዕራብ ቨርጂኒያ የሚገኝ ቤተ-ክርስቲያን በሞሞንጋ በሚባል ስፍራ ፌርሞንት የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ላይ በደረሰ ፍንደታ ሕይወታቸውን ላጡ 362 ወንዶች መታሰቢያ ሥነ-ስርዓት አዘጋጀ። ሥነ ስርዓቱ አንዴ እንዲደረግ እንጅ በየዓመቱ እንዲከናወን የታቀደ አልነበረም። መረጃው እንደሚያወሳው  በቀጣዩ ዓመት ሶኖራ ስማርት ዶድ የተባሉ እናት ከአምስት  የቤተሰብ አባላት ጋር ሚስቶቻቸውን ባጡ አባቶች ብቻ ያደጉ ሴት ልጆች የስፖኬን-ዋሺንግተን ነዋሪ በየዓመቱ የአባቶች ቀን እንዲከበር ማሕበረሰቡን ማግባባት ጀመሩ፤ ተሳካላቸው። በ1910 የዋሺንግተን ግዛት የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የአባቶች ቀን አከበረ። ይህ ሥነ-ስርዓት ቀስ በቀስ በመላ አሜሪካ መስፋፋቱን መረጃው ጠቁሟል።

በጉዳዩ ዙሪያ በኵር አባትነት እንዴት ይገለጻል? ስትል በደብረማርቆስ ዩንቨርሲቲ  በባሕል ጥናት ዘርፍ መምህር እና ተባባሪ ፕሮፌሰር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር)ን ጠይቃለች፡፡  እንደ  ፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ  በኢትዮጵያ ወግ እና ባሕል ውስጥ አባትነት ከቤተሰብ መዋቅር አልፎ ሰፊ ማህበራዊ እና ታሪካዊ አንድምታ አለው፡፡ የቃሉ አመጣጥ አባት ከሚለው የሥም ግሥ የወጣ ሲሆን በሴማዊ የቋንቋዎች ጥናት  በጥሬ ትርጉም  ወላጅነት ሲሆን፤ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ደግሞ ምንጭነት፣ አስገኝነት እና አስቀጣይነትን ያመለክታል፡፡

አባትነት በቤተሰብ ውስጥ ያለው ፋይዳ

አባትንነት ባሕላዊ እና ማህበራዊ ሚና እንዳለው የሚያነሡት ፕሮፌሰሩ፤  በተለምዶ ያለው ባሕላዊ አወቃቀር ከሦስት ቁልፍ ነገሮች ጋር ያዛምደዋል፡፡ አንደኛ የቤተሰብ መሪነት እና መጋቢነት ነው፡፡ አባት የቤተሰቡ ምሰሶ፣ አስተዳዳሪ እና ፍላጎቶችን አቅራቢ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የባሕል እና የእውቀት አስተላላፊ፣ የቤተሰብ ታሪክ፣ ባሕላዊ እሴት፣ የዘር ሃረግ፣ የአባት ሥምን፣ የአካባቢ ጥበብን ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት ያለበት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሦስተኛ  አማካሪነት እና ዳኝነት ነው፡፡ ይህም በቤተሰብ ውስጥም ይሁን  ከቤት ውጭ የሚነሱ ክርክሮች የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ፣ በልጆች በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ሥነ ምግባር እና ሕግን አክብረው እንዲያድጉ የማድረግ ሚና አለው፡፡

በተለያዩ ተረትና ምሳሌዎች እንዲሁም ጽሑፎች አባት ለልጁ ያለውን የጥበቃ፣ የደህንነት እና የልጅነት ማንነት የመቅረጽን አቅም ያሳያል፡፡ ከትውልድ ትሥሥር ውጭ አባትነት ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከተ ዜጋ የሀገር አባት፣ የጥበብ እና የሙያ አባት ደግሞ የተለየ ፈጠራ ለሠሩ የሚሠጥ ተምሳሌት እንደሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ቢቢሲ አባትነትን እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 1970ዎቹ ድረስ ከሕጻናት ጋር በተያያዘ ብቸኛው ኃላፊነታቸው ኦኮኖሚያዊ የሆኑ ችግሮችን መፍታት ብቻ እንደ ነበር ያሳያል። በአምስተርዳም ቭሪጅ ዩኒቨርሲቲ መምህር ማሪያን ቤከርማንስ በሠሩት ተከታታይ ጥናት  እንዳረጋገጡት ግን ከአባቶቻቸው ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት ኖሯቸው ልጅነታቸውን ማሳለፉቸው ብቻ ሕጻናት የተሻለ የአእምሮ እድገት እና ጥሩ ባህሪ እንዲታይባቸው፤ በሕይዎታቸውም ደስተኛ የመሆናቸው እድል ከፍ ያለ፣ ከሌሎች ሕጻናት ጋር ያላቸው ግንኙነትም ጥሩ እንደሆነ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት አባትነት  ከከተማነት መሥፋፋት እና ከዘመናዊ ትምህርት ጋር ተያይዞ  በርቀት ከሚታይ ሥልጣን እና ቁጥጥር በዘለለ ከልጆች ጋር ቀረቤታ በመፍጠር በሥሜት መደገፍ እና በልጆች እንክብካቤ መሳተፍ ነው፡፡

የዶክተር ቤከርማንስ ጥናትም ‘’ምናልባት ጥሩ አባትነት ሲባል ብዙዎች እጅግ ከባድና ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ነገር መስሎ ሊታያቸው ይችላል። ነገር ግን ልጆችን በጉልበታችን ላይ አስቀምጠን ዐይን ዐይናቸውን ማየት በራሱ በእጅጉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ያስችላል። በተለይ ደግሞ አዲስ የተወለዱ ሕጻናት ከእናትና አባታቸው ጋር የሚያሳልፏቸው ጊዜያት ወደ ፊት ማንነታቸውን ለመገንባት ትልቅ አቅም አላቸው’’ ይላሉ፡፡

በልጅ ማሳደግ ሂደት ውስጥ ትልቁ ነገር ጥሩም ይሁን መጥፎ አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ነው። አብሮ ጊዜ በማሳለፍ ውስጥ ልጆች ቤተሰቦቻቸውን የመላመድና ስሜታቸውን በቀላሉ መግለጽን ይማራሉ። ቤተሰብ በተለይ ደግሞ ብዙ ጊዜን ከልጆቻቸው ጋር ማሳለፍ የለመዱ አባቶች ልጆቻቸው ምን እንደሚያስደስታቸው እንዲሁም ምን እንደማያስደስታቸው በቀላሉ መለየት ይጀምራሉ። ከዚህም ባለፈ ጥሩና መጥፎ የሚሏቸውን ነገሮች በጨዋታዎች መሀል ለማሳየት እድሉን ይከፍትላቸዋል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር መስፍን በበኩላቸው በፎክለር ጥናት ውስጥ ሥም የሚወጣው  እና የዘር ሃረግ የሚቆጠረው በአባት በኩል ነው፡፡ ለልጁ ሥም ከማውጣጥ ባለፈ የማህበረሰቡ (ጎሳው) አካል አድርጎ ያስተዋውቃል፡፡

አባትነት በልጁ ሥነ ልቦና ውስጥ አምሳያነት፣ ጥሩ ወንድነት፣ ፅናት እና ማህበራዊ ግንኙነትን፣ ክህሎትን ማስተማሪያ ቀዳሚ ዓርአያ (ሞዴል) ነው፡፡

አባታቸውን በሞት፣ ከእናት ጋር በሚፈፀም ፍቺ.. የሚያጡ ልጆች ሁለንተናዊ ማንነት፣ በራስ መተማመን እና ማህበራዊ ሥነ ምግባር ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሰፊ እንደሆነ ያሳያል፡፡ጠንካራ እናት ብትኖርም አባትን ማጣት በልጁ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከባድ ነው፡፡

“አባትነት ሰብስቦ የሚይዝ ጃንጥላ ነው፣በተመደው አካሄድ መጋቢ ነው፣አስተዳዳሪ ነው .. ከሌሎች ጋር የሚደረገው ግንኙነት በአባት ጥላ ሥር ያልፋል”  ተብሎ ይታሰባል፡፡

ሁሉንም እናት ብትሸፍነውም እንኳን “አባት የለውም” ሲባል የመመኪያነትን ጥላ ልጆች በሥነ ልቦና ያጣሉ፤ ክፍተት ይኖረዋል፡፡

“ሞት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር ስለሆነ ከሞተ ምንም ማድረግ አይቻልም” የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር መስፍን ፈቃዴ (ዶ/ር)፤ትዳር ከተያዘ በኋላ አለመግባባትን በጠረጴዛ ዙሪያ ፈተው ለልጆቻቸው ሲሉ መግባባት ካልቻሉ የነሱም የልጆችም ሕይወት እንደ ሚበላሽ ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ ላይ በየጎዳናው የተበተኑ ልጆች መብዛት በሰው ሠራሽ ችግር ስለሆነ እንደ ቤተሰብ ኃላፊነት ሊወሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

መረጃ

ሕጉ ስለ አባትነት ምን ይላል

  • ልጆች ወላጆቻቸውን የማወቅና ፍቅርና እንክብካቤ አግኝተው የማደግ መብት እንዳላቸው በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀጽ 7 እና በሀገራችን ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 36 ላይ በግልፅ  ተደንግጎ  እናገኘዋለን፡፡

ወላጆችን በተለመከተ በእናትነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች በጣም አናሳ ቢሆኑም አባትነትን አስመልክቶ ግን ብዙ አከራካሪና እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የሚደርሱ ጉዳዮች መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አባትነት የሚረጋገጥባቸውን መንገዶች አስፍሯል፡፡

  • እናትነት በመውለድ በተፈጥሮ ስለሚታይ ሕጉ ሦስት አባትነትን የማረጋገጫ መንገዶችን ደንግጓል፡፡

እነዚህም በሕግ ግምት አባትነትን ማረጋገጥ፣ ልጅነትን በመቀበል አባትነትን ማረጋገጥ እና በፍርድ ቤት ውሳኔ  አባትነትን ማወቅ የሚሉ ናቸው፡፡

  • አባትነትን ማረጋገጥ ያልተቻለ ከሆነ በመቀበል አባትነት ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ይህም አባትየው “ልጄ ነው“ ሲል በመቀበሉ ምክንያት አባትነት ሊረጋገጥ እንደሚችል በአንቀጽ 131 ላይ ተደንግጓል፡፡
  • በሁለቱም (በእናት ወይም በልጅ) የሚሰጠው ማረጋገጫ አባትነቱን መቀበሉን ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ወስጥ ክርክር ካላነሱ አባት ነኝ ያለውን ሰው አምነው እንደተቀበሉ እንደሚቆጠር በአንቀጽ 138 ሰፍሯል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here