ሴቶች በራሳቸው ሰላምን የመገንባት አቅም አላቸው። ይህም ሲባል ሰላምን በቤታቸው፣ በአካባቢያቸው፣ በማህበረሰቡ፣ በሥራ ቦታቸው እና በአጠቃላይ ማህበረሰቡ እንዲረጋገጥ ሊኖራቸው የሚገባ ንቁ ተሳትፎ ካደረጉ ውጤቱ ከፍተኛ ስለሆነ ነው።
ሴቶች በአፍሪካ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፣ ብዙውን ጊዜ በመሠረታዊ ደረጃ፣ ማህበረሰቦችን የማቀራረብ፣ ውይይትን የማስፋፋት እና የግጭት መንስኤዎችን ለመፍታት ብቃታቸውን አሳይተዋል። የሴቶች ልዩ አመለካከቶች እና ልምዶች በግጭት መከላከል እና አፈታት ላይ ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ይሰጣሉ፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ውይይቱን ከማድረጉ ቀደም ብሎ በሚደረገው የአፍሪካ ቀዳማዊ እምቤቶች ውይይት በርካታ ጊዜ እነደተነሳው በርካታ የአፍሪካ እና ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲዎች እና ማዕቀፎች በግጭት መከላከል ፣ በመፍታት እና ከግጭት በኋላ መልሶ ግንባታ ላይ ተሳትፏቸውን ከፍ ለማድረግ የሴቶችን አቅም ማጎልበት እና ሰላም እና ደህንነት መካከል ያለውን ወሳኝ ግንኙነት አጉልተው አሳይተዋል። እውነታው ይሄ ቢሆንም፣ ሴቶች ከሰላም ተደራዳሪዎች፣ መልእክተኞች፣ አስታራቂዎች እና ሰላም አስከባሪዎች መካከል ግን ጥቂቶችን ብቻ ነው የሚወክሉት። ይህም የፓሊሲ አፈጻጸም ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ረገድ የተሻሻሉ ሥራዎች ቢኖሩም በታለመላቸው ድንጋጌዎች እና አሁን ባለው ሁኔታ መካከል ጉልህ ክፍተቶች እንዳሉ ማሳያ ነው።
ባለፉት ዓመታት በተለያየ ግጭት ውስጥ የሚገኙት ሊባኖስ፣ ሶማሊያ፣ ማይናማር…. ግጭት በነበረባቸው ከተሞች በተፈጠረው ቀውስ፣ በወደመው መሰረተ ልማት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የገቡት ሴቶች እና ህፃናት ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ሊባኖስ እና ሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ ሰላም ለማምጣት የሚንቀሳቀሱ ሴት ሸምጋዮች ግን ዛሬም ድረስ የደህንነት ስጋቶች ያጋጥሟቸዋል፡፡ በሰላም እጦት ሴቶች ከአካባቢ በመፈናቀል እንዲሁም ከባድ መሠረተ ልማት ውድመት የቤተሰብን እንክብካቤ የማድረግ ሸክሞች ሴቶች ላይ ወድቀዋል፡፡ የነዚህ ችግሮቶች በተደጋጋሚ መፈጠር ደግሞ ፣ የድካም እና ስሜቶች መዳከም የአእምሮ እና የአካል ደህንነት ችግር በየቀኑ እንዲጋፈጡ ያደርጋቸዋል፡፡
የማህበረሰብ አንድነት በሽምግልና፣ በተሸማጋዮች መካከል መተማመንን በዘላቂነት ለመገንባት ፣ግጭትን መከላከልና ሰላምን ለማምጣት የሁሉም የህብረተሰብ አባላት በተለይም የሴቶችን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው።
እውነተኛውን ሰላም ለሚሹት ሴቶች ከግጭቱ የከፋ ውጤት እና ከሚያጡት ነገሮች አንፃር አማራጭ የሌለው ምርጫ እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡት ከልባቸው እንደሚሠሩ የሚገልጠው ወርልድ ቪዝን ግጭት ያለባቸውን አካባቢ ዋቢ አድርጎ በፈረንጆቹ 2026 መጋቢት ላይ ያወጣው ጥናት ነው፡፡
የሰላም ግንባታ መርሃ ግብሮች ውጤታማ የማህበረሰብ ፍላጎቶችን ማሟላት የአካባቢ ባለቤትነት ስሜት መኖር ለሰላም ወሳኝ ነው፡፡ ከሴቶች፣ ወጣቶች እና ወንዶች እንደ አስፈላጊነቱ በውይይት ማካተት ለሚመጣው የሰላም ስኬት አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
በተለይም ግጭት በተከሰተበት ቦታ (አካባቢ) የሚጠነሰሱ የሰላም ውጥኖች የበለጠ ተቀባይነትን ለማግኘት ያላቸው ውጤታማነት በጥናቱ ታይቷል። በአጠቃላይ ለሰላሙ ዘላቂነት በየአካባቢው ያሉ የጎሳ መሪዎች እንዲሁም የሴት ቡድኖችን ማወያየት ወሳኝ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
ግጭት በተፈጠረበት አካባቢ ከሰላም ግንባታ ጎን ለጎን ግን መሰረት ያለው መልሶ የማቋቋም ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በማይናማር ያለው ተሞክሮ ከሰላም ማምጣት ድርድሩ ጎን ለጎን ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን በሚያግዝ ፕሮግራም በሴቶች የሚመራ ተቋቁሟል። በዚህም ለእፈላጊ እና አንገብጋቢ ጉዳቶቹ ቶሎ ምላሽ ለመሥጠት ይሰራል፡፡ በጠቅላላው የሰላም ድርድሮች እና መልሶ ግንባታ ከመሥራት ጎን ለጎን ከ300 በላይ ሴት መሪዎችን ማብቃት ችለዋል።
በሶማሊያ ደግሞ ሴት የአመራር እና የኮሙኒኬሽን ስልጠ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀይማኖት መሪዎች ጋር ውጤታማ በሆነ መንገድ ሴቶች መሳተፍ እንዲችሉ፣ ለአካባቢ ባለስልጣናት ችግራቸውን እንዲያቀርቡ ቦታም እንዲኖራቸው አስችሏል። የሴቶቹ በራስ መተማመንም እንዲጨምር አድርጓል፡፡
ጥናቱ ሴቶቹ በሰላም ሂደቶች ላይ ያላቸው ተጽእኖ በተግባር ሲተነተን ደግሞ ታማኝ ሸምጋዮች እና ተደራዳሪዎች መሆናቸውን ነው ያሳየው፡፡ ቀጣይ ተሳትፏቸው ደግሞ በጎሳዎች ላይ የተጠናከረ እምነት በማሳደር እና ቀጣይነት ያለው ውይይት በማድረግ ተደራዳሪ አካላት ላይ ያለውን አለመተማመን መለወጥ ይሆናል፡፡ ከቀውስ በኋላ ባለው ሂደት በፊት የነበሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስተማሪ በሆነ ቅጣት በመቅጣት የተጠያቂነት ዘዴዎችን ማጠናከር ይገባል፡፡ የሴቶችን ሚና እንደ አስታራቂ፣ ችግሮች ሳይደርሱ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተዋናዮች እና እንደ ማህበረሰብ እውቅና ሰጭ ቡድን አድርጎ በመደበኛነት ማደራጀት እንደሚገባ ነው ጥናቱ ያመለከተው፡፡
በኢትዮጵያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ማህበራዊ ትስስርን እንዳይጎለብት ከሚያደርጉ ነገሮች ውስጥ ድህነት፣ ግጭት፣ የእኩልነት አለመኖር እና የአካታች ተሳትፎ እጥረቶችን ለመቅረፍ “ሰላምን ተለማመዱ በሰላም ኑሩ” የሚል ፕሮጀክትን በፈረንጆቹ 2025 ሚያዚያ ወር ሲያጀምሩ እውነተኛ ሰላም ዘላቂ ሊሆን የሚችለው ሁሉም ድምጾች የሚሰሙበት፣ ሁሉም ተሞክሮዎች የሚከበሩበት እና ሁሉም የማህበረሰብ አካላት አስተዋፅኦ ለማድረግ ህጻናት፣ ሴቶች፡ ወጣቶች እና ተጋላጭ የማህበረስብን ክፍሎችን ያካተተ ጠንካራ ሀገራዊ ሰላምን የመገንባት ሥራ በሚሰራበት ወቅት እንደሆነ ጠቅሰው ነበር፡፡
ጥናቱ ሲያጠቃልል የሚጠቅሰውም ፓሊሲ አውጭ አካላት ልብ ሊሉት የሚገባው ጉዳይ የወደፊት ሰላምን የመገንቢያ ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ነው፡፡ እነዚህም የሴቶችን ተሳትፎ ማጠናከር ፣ ለሥራቸው ደህንነት ጥበቃ ማድረግ ፣ ችግር የተከሰተባቸውን ወደ ማገገሚያ ማዕከል ማስገባት እንዲሁም ጠንካራ የሴቶች አመራር መገንባት መቻልን ማረጋገጥ ከተቻለ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢ ጠንካራ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ሊመጣ እንደሚችል ነው፡፡
የሕግ አንቀጽ
የእኩልነት መብቶች
- ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ፣ አንቀጽ 7 ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ ያለምንም ልዩነት እኩል የሕግ ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ይህንን መግለጫ በመፃረር የሚደረግ ልዩነት እና ለልዩነት የሚያነሳሳ ተግባር እንዳይፈጸምባቸው እኩል የሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡
- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት፣ አንቀጽ 25 በዘር፣ በብሔር፣ ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲክ፣ በማኀበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው።
- በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የፆታ እኩልነት ጉዳይ አንቀጽ 35 ከሠፈሩት የሴቶች መብቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡ ሕገ መንግሥቱ የረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች ሁሉ ከወንዶች እኩል የመጠቀም፣ ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር. የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ፣ ለእኩል ሥራ እኩል የመወዳደርና እኩል ክፍያ የማግኘት፣ በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት የማግኘትና ጋብቻን በፍላጎት ብቻ የመመሥረት፣ ሴቶችን ከሚያንቋሽሽና ከሚጎዳ ኋላቀር ልማድና ድርጊቶች ነፃ የመሆን ወዘተ መብቶች፡፡
ምንጭ-wordpress.com
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


