ክረምት ለተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የክህሎት እና የተሰጥኦ ማዳበሪያ ወቅት ነው፤ የትምህርት ዘመኑ ሲጠናቀቅ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎች የክረምት ዕረፍት ይጀምራሉ። ይህ ወቅት ከአንድ ዓመት ሙሉ የትምህርት ጊዜ ረፍት ለማግኘት የሚያስችል ቢሆንም ተማሪዎች እውቀታቸውን፣ ክህሎታቸውንና ተሰጥኦዎቸውን ለማዳበር የሚያገለግል ወርቃማ ዕድልም አለው። የእረፍት ጊዜን ያለ እቅድ ከማሳለፍ ይልቅ በጥቅም ላይ ማዋል ለተማሪዎች የወደፊት ስኬት ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል የትምህርት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በክረምት ወቅት የንባብ ልምድ እና የተማሪዎች ትምህርት ውጤት ላይ የተደረጉ ጥናቶች አብዛኛውን ጊዜ የክረምት እረፍት ከመዝናናት እና ከጨዋታ ጋር ብቻ ተያይዞ ይታያል። ሆኖም የትምህርት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት የእረፍት ጊዜ ትምህርትን ፈጽሞ መርሳት ሳይሆን በተለየ መንገድ መማር፣ አዳዲስ ልምዶችን ማካበትና የግል ችሎታዎችን ማሳደግ ማለት ነው። ተማሪዎች በትምህርት ዘመን ለማንበብ ያልቻሉትን መጻሐፍት በማንበብ፣ የዓመቱን ትምህርት በመከለስ እና አዳዲስ ክህሎቶችን በመማር ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን በተሻለ ዝግጅት መመለስ ይችላሉ።
የተለያዩ ጥናቶችም በክረምት ወቅት ከትምህርት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚጠብቁ ተማሪዎች በቀጣዩ ክፍል የተሻለ የንባብ፣ የቋንቋና የመረዳት አቅም እንደሚያሳዩ ያመለክታሉ። የትምህርት ባለሙያዎች “Summer Learning Loss” ወይም “Summer Slide” በሚል እንደሚገልጹት በእረፍት ወቅት በበጋው ያካበቱት እውቀት እንዳይቀንስ ለመከላከል ተማሪዎች በቀን ቢያንስ የተወሰነ ጊዜ ለንባብና ለትምህርት መመደብ እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ።
ከትምህርት በተጨማሪ የክረምት እረፍት የሕይወት ክህሎቶችን ለመማር የሚመች ወቅት ነው። ምግብ ማብሰል፣ አትክልት መትከል፣ የኮምፒውተር እውቀት ማግኘት፣ ቋንቋ መማር፣ የእጅ ሙያዎችን መለማመድ እና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች መሳተፍ ለወደፊት ሕይወት ጠቃሚ የሆኑ ክህሎቶችን ያጎለብታሉ። እነዚህ ተግባራት ተማሪዎች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ የችግር ፈቺነት አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ለሥራ ዓለም አስፈላጊ የሆኑ ተሞክሮዎችን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።
የአካል ጤናም በዚህ ወቅት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ተማሪዎች ቀኑን ሙሉ በተንቀሳቃሽ ስልክ፣ በቴሌቪዥን ወይም በኮምፒውተር ላይ ጊዜያቸውን ማሳለፍ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል። ስለዚህ እግር ኳስ፣ ሩጫ፣ የባህል ጨዋታዎችና ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የዕለት ተዕለት ተግባራቸው አካል ሊሆኑ ይገባል። ይህም አካላዊ እና የአእምሯዊ ጤናቸውን እንዲሁም የማህበራዊ ግንኙነታቸውን ያጠናክራል።
የፈጠራ ሥራዎችም የክረምት እረፍትን ትርጉም ያለው ጊዜ ለማድረግ ከሚያስችሉ መንገዶች መካከል ናቸው። ስዕል፣ ሙዚቃ፣ ድራማ፣ ግጥም፣ ፎቶግራፊ እና ሌሎች የሥነ ጥበብ ሥራዎች የልጆችን ምናብ ያሰፋሉ፣ የችግር ፈቺነት አቅማቸውን ያሳድጋሉ፣ በራሳቸውም የመተማመን ስሜት እንዲያዳብሩ ያግዛሉ።
ይህንን እውነታ በተግባር ከሚያሳዩ ተማሪዎች መካከል በባሕር ዳር ከተማ የፈለገ ዓባይ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ መክሊት ጌታቸው እና የ12ኛ ክፍል በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የሳይንስ ቴክኖሎጅ ሂሳብ ማበልጸጊያ ማዕከል /ስቲም/ ትምህርት ቤት ተማሪ እዩኤል በየነ ይገኙበታል። ሁለቱም የክረምት እረፍታቸውን ተሰጥኦአቸውን ለማሳደግ እቅድ ይዘዋል።
መክሊት ጌታቸው ከትምህርቷ ጎን ለጎን በሚኒ ሚዲያ እያዝናኑ ቁምነገር የሚያስጨብጡ ዝግጅቶችን በማቅረብ ትታወቃለች። በክረምቱ የንግግር ችሎታዋን ለማሻሻል መጻሕፍት ለማንበብ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ለመከታተል እንዲሁም የአቀራረብ ብቃቷን የሚያጠናክሩ ልምምዶችን ለማድረግ ማቀዷን ትናገራለች። ግጥሞችንና አጫጭር ታሪኮችን በማንበብና በመጻፍ የሥነ ጽሑፍ ፍላጎቷን ለማዳበርም እንደምትፈልግ ትገልጻለች።
በተመሳሳይ እዩኤል በየነ የስዕልና የእጅ ጥበብ ሥራዎችን ይወዳል። የክረምት እረፍቱን የስዕል ችሎታውን ለማጎልበት በመጠቀም የተፈጥሮ ገጽታዎችን፣ የሰዎች ምስሎችንና የማሕበረሰብ ሕይወትን የሚያንጸባርቁ ስዕሎችን ለመሳል አቅዷል። ከካርቶን፣ ከእንጨትና ከሌሎች በቀላሉ ከሚገኙ ቁሳቁሶች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት የፈጠራ አቅሙን ለማሳደግ እንደሚፈልግም ገልጿል።
ለዚህ ተግባር የወላጆች ሚናም ከፍተኛ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በእረፍት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ነጻ ከመተው ይልቅ የቀን መርኃ ግብር እንዲያዘጋጁ፣ ለንባብ፣ ለስፖርት፣ ለፈጠራ ሥራዎችና ለቤተሰብ ጊዜ እንዲመድቡ መርዳት ይገባቸዋል። በተጨማሪም ከአደገኛ ልማዶችና ከአላስፈላጊ ቦታዎች እንዲርቁ ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በአጠቃላይ የክረምት እረፍት ለተማሪዎች ከትምህርት ርቀው የሚያገኙበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ተሰጥኦን የሚያዳብሩበት፣ ክህሎትን የሚያጎለብቱበት እና ለወደፊት ስኬታቸው መሠረት የሚጥሉበት ወሳኝ ወቅት ነው። ስለሆነም ተማሪዎች ይህንን ወርቃማ ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን ለተሻለ ነገ ማዘጋጀት ይገባቸዋል።
ተማሪዎች የክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን ከትምህርት ፈጽመው እንዳይርቁ እና ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን የተሻለ ዝግጅት አድርገው እንዲመለሱ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ የተለያዩ የክረምት ትምህርትና የመዝናኛ መርኃ ግብሮችን ማዘጋጀቱን ገልጿል። የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ትበይን ባንትይሁን ለበኵር እንደተናገሩት በክረምት ወቅት በበጎ ፈቃድ የሚያስተምሩ መምህራን፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለረፍትና ትምህርታቸውን አጠናቀው የተመለሱ ተማሪዎች እና በየአካባቢው የሚገኙ መምህራንን በማስተባበር ተማሪዎች ከትምህርት ጋር ያላቸውን ትስስር እንዳይቋረጥ ለማድረግ የሚያግዙ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል።
ተማሪዎች በየክፍል ደረጃቸው ተመድበው የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲከታተሉ እና ቀጣዩን የትምህርት ዘመን በተሻለ ዝግጅት እንዲጀምሩ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል።
ከትምህርት መርኃ ግብሮች ባሻገር ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በጤናማ መንገድ እንዲያሳልፉ የስፖርትና የመዝናኛ አማራጮችን የማስፋፋት ሥራም ተከናውኗል። በየአካባቢው የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የከተማ አስተዳደሩ ያዘጋጃቸው የስፖርት ሜዳዎች ለተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውንም ነው የተናገሩ፡፡
ወ/ሮ ትበይን አክለውም በአሁኑ ወቅት የእድሳት ሥራ እየተከናወነበት የሚገኘው የአፄ ቴዎድሮስ ስታዲዮም እስከ ሐምሌ መጀመሪያ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚውል ይጠበቃል። ስታዲዮሙ ከጭቃ የጸዳ እና ለተማሪዎች የተለያዩ የስፖርት ክህሎቶችን የሚያዳብሩበት ምቹ ስፍራ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በከተማው የሚገኙ ሌሎች የስፖርት ሜዳዎች በተማሪዎች ፍላጎትና ጥቅም መሰረት ክፍት ሆነው እንዲያገለግሉ አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል። ይህም ተማሪዎች በትምህርትና በስፖርት መካከል ሚዛናዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ የአእምሮ እረፍት እያገኙ ከትምህርት ሳይርቁ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ያግዛዋል ነው ያሉ።
ምክትል መምሪያ ኃላፊዋ የባለፈውን ዓመት ተሞክሮ በማስታወስም ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው ከመደበኛ ትምህርታቸው ባሻገር በሃይማኖት አባቶች፣ በሥነ ልቦና ባለሙያዎች፣ በሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ባለሙያዎች እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎች የተሰጡ የሥነ ምግባርና የተግባቦት ስልጠናዎችን መከታተላቸውን አስታውሰዋል፡፡
በያዝነው ዓመትም በከተማው በሚገኙ 214 ትምህርት ቤቶች ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎች በክረምት ወቅት በትምህርት፣ በስፖርት እና በተለያዩ የመዝናኛ መርኃ ግብሮች እንዲሳተፉ መታቀዱን ተናግረዋል።
የትምህርት መምሪያው ያዘጋጀው ይህ ፕሮግራም ተማሪዎች የክረምት እረፍታቸውን በጠቃሚ እንቅስቃሴዎች በማሳለፍ ከትምህርት እንዳይርቁ፣ ሥነ ምግባራቸውን እንዲያጎለብቱ እና ለአዲሱ የትምህርት ዘመን በተሻለ ዝግጁነት እንዲመለሱ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
መረጃ
ተማሪዎች በክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ ከተጠቀሙበት ለቀጣዩ የትምህርት ዘመን የተሻለ ዝግጁነት፣ ክህሎት እና ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ ያገኛሉ። ስለዚህ በክረምት፡-
ያለፈውን ትምህርት መከለስ
የንባብ ልምድ ማዳበር
ስፖርት እና የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ
በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ስራዎች መሳተፍ
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን መቆጣጠር
ቀጣዩን የትምህርት ዘመን ማቀድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
(ሰናይት በየነ)
በኲር የሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


