የምድር እስትንፋስ

0
135

በቀደሙት ዓመታት ኢትዮጵያ ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደ ነበራት የግብርና ሚኒሥቴር መረጃ ያመላክታል፡፡ ይሁንና ዘላቂ ባልሆነ የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት አጠቃቀም   የደን ሽፋኗ ተመናምኖ  ወደ ሦስት በመቶ ወርዶ  ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም የብዝኃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት ለምነት መሟጠጥ  እና የምርታማነት መቀነስ፣ የውኃ አካላት በደለል መሞላትና የመጠን መቀነስ እንዲሁም መጥፋት ሀገሪቱን  ለከፋ ድርቅ እና  ጎርፍ ሕዝቡን ደግሞ  ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት ቆይቷል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ዓሉታዊ ተፅዕኖ በመከላከል የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብሎም ዘላቂነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲቻል የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅና በዘላቂነት መንከባብ  ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ይህንንም ችግር ለማስወገድ በኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም  የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ጀምራለች፡፡

በመርኃ ግብሩም  በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የዝናብ ወቅትን ጠብቆ የመትከልና የመንከባከብ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በመጀመሪያው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር  አራት  ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ አራት ነጥብ ሰባት  ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል፡፡

መርኃ ግብሩ በመላው የሀገሪቱ ክፍል ቀጥሎ በ2012 ዓ.ም  አምስት  ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን፣ በ2013 ዓ.ም ስድስት  ነጥብ ስምንት  ቢሊዮን፣ በ2014 ዓ.ም ሰባት  ነጥብ ሁለት ቢሊዮን፣ በ2015 ዓ.ም ሰባት  ነጥብ አምስት ቢሊዮን፣ 2016 ዓ.ም ሰባት ነጥብ አምስት እንዲሁም በ2017 ዓ.ም ስምንት ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል፡፡

በተያዘው ዓመትም(በ2018 ዓ.ም) ስምንት  ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል፡፡ የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ለመገንባት እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር  በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች መርኃ ግብሩ በየዓመቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ዘንድሮም በተመሳሳይ ሁኔታ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ሸማ ለማጎናፀፍ ሁሉም አካባቢዎች በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በአማራ ክልልም በተለያዩ አካባቢዎች ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በክልሉ በምሥራቅ ጎጃም ዞን  577 ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ  መሆኑን የዞኑ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ተጠሪ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ በዞኑ በመርኃ ግብሩ  የአረንጓዴ አሻራ እና የደን ልማት ሥራዎችን ለማሳካት ከሁለት ነጥብ ሰባት  ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ መለሰ መንግሥት አሳውቀዋል፡፡ የሚተከሉት ችግኞች ለአካባቢ ፣ ለአፈር ጥበቃ እና ለሥነ ምህዳር መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በዞኑ በቆላማና በደጋማ አካባቢዎች  የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስና የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ለማሻሻል ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማሙ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች  ይተከላሉ፡፡  በግል፣ በመንግሥት፣ በማኅበረሰብ እና በማኅበራት የሚለማው የደን ሀብት በአግባቡ እንዲጠበቅና ለልማት እንዲውል የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለአሚኮ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ  በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር   በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርጋ ግብር ከ20 ሚሊዮን በላይ የደንና የፍራፍሬ ችግኝ  መዘጋጀቱን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል አሊ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም  ከሰባት ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለጻ ከአሁን ቀደም በተከናወኑ  የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች  በተፋሰሶች ወጣቶችን በፍራፍሬ ዘርፍ በማደራጀት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

በዞኑ የደዋ ጨፋ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኑሩ መሀመድ በበኩላቸው በባለፉት ዓመታት በወረዳው የተሠሩ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች የወረዳውን የደን ሽፋን ከ13 በመቶ ወደ 15 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2018 የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ለዚህም ከ261 ሺህ  ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቷል። ከእነዚህ ውስጥ ለምግብ ዋስትና እና ለጥምር እርሻ የሚውሉ፣ ቡናን ጨምሮ የፍራፍሬ እና የደን ችግኞች ይገኙበታል፡፡ ዝግጅቱ የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ ለማልማት እና የክልሉን የደን ሽፋንን ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡ በ2017 ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 80 ነጥብ 1 በመቶ መጽደቁንም መረጃው ጠቁሟል፡፡

እንደ ሀገር የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር “ተስፋን እንትከል!” በሚል መሪ ቃል  በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ኃይቅ ዳርቻ ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)ን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል፡፡ የግብርና ሚኒሥትሩ አቶ  አዲሱ አረጋ በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር በሀገሪቱ በ2011 ዓ.ም  የተጀመረው  የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአካባቢ መራቆት ችግሮችን መፍታት ዓላማው እንደ ነበር አስታውሰዋል፡፡ በመርኃ ግብሩም  በየዓመቱ በአማካይ 25 ሚሊዮን ሕዝብ ተሳትፏል፡፡

 

በዚህም ሀገራዊ የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ በ2016 ዓ.ም ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ መርኃ ግብሩ በከፍተኛ ሁኔታ የአፈር መሸርሸር እና የደን መጨፍጨፍን በመከላከል የተፋሰሶች የውኃ መጠን በመጨመር የተስተካከለ ፍሰት እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

 

በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተከናወኑ ሥራዎችም  ኢትዮጵያ  አቮካዶን ወደ ውጪ ከሚልኩ ሀገራት ሁለተኛ እንድትሆን አስችሏታል ያሉት ሚኒሥትሩ፤ በተያዘው ዓመት ለመትከል የተቀመጠውን  ስምንት  ቢሊዮን ችግኝ ግብ ለማሳካት በትኩረት፣ በቅንጅት እና በባለቤትነት ስሜት መሥራት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

 

መርኃ ግብሩን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው  “በዚህ ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ግብ አስቀምጠን ከፍ ወዳደረግነው 65 ቢሊዮን ችግኞች ግብ የመድረስ ትልማችንን ለማሳካት በጽናት እየገሰገስን እንገኛለን” በማለት ለዕቅዱ ስኬታማነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

 

መረጃ

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ዋና ዓላማ

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም፡- የካርቦን ልቀትን በመቀነስና ከፍተኛ መጠን ያለው የካርቦን መጠን በአፈር እና በዛፎች ውስጥ በማከማቸት የአካባቢውን የሙቀት መጠን ማስተካከል።

  • የአፈር መሸርሸርን መከላከል፡- ተራራማና የተመናመኑ አካባቢዎችን በዕፅዋት መሸፈን፣ የውኃ ሀብትን መጠበቅ እንዲሁም የአፈርን እርጥበትና ለምነት ማቆየት።
  • ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ፡- ከእንጨት ምርት ባለፈ ለምግብነት የሚውሉ (እንደ ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ) የመሳሰሉ ፍሬ አፍሪ እፅዋትን በስፋት በመትከል የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ማጎልበት።
  • ብሔራዊ አንድነትን እና ግንዛቤን ማሳደግ፡- መላው የኅብረተሰብ ክፍል በጋራ በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ላይ በመሳተፍ ለአካባቢ ጥበቃ ያለው ኃላፊነት እንዲሰማው ማድረግ።

 

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የሰኔ 15  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here