ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ታርሷል

0
95

በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከባሕላዊ እና ከተበታተነ የእርሻ አሠራር በመውጣት መሬትን በኩታ ገጠም በማደራጀትና በዘመናዊ ማሽነሪዎች ማረስ ይገባል፤ ይህም የጊዜ ቆጣቢነትን፣ የሥራ ውጤታማነትን፣ የምርት ጥራትንና የእርሻ ወጪን በመቀነስ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው።

ለአብነትም በህንድ አገር በፑንጃብና ሀርያና ግዛቶች አርሶ አደሮች መሬታቸውን በማሰባሰብ እና በትራክተር በመጠቀም የእርሻ ሥራቸውን በማዘመን በአንድ ሄክታር የሚገኘውን ምርት በእጅጉ ማሳደግ እንደቻሉ ዓለም አቀፉ የምግብ እና እርሻ ድርጅት ያወጣው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ በቻይና የተበታተኑ እርሻዎችን በማሰባሰብ እና የእርሻ ሜካናይዜሽንን በመጠቀም የምግብ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ተችሏል።

ተሞክሮዎቹ ትናንሽና የተበታተኑ ማሳዎችን በአንድ ላይ በማምጣት እና ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችን መጠቀም ለምርት ዕድገት ቁልፍ መሆናቸውን ያሳያሉ።

በኢትዮጵያም የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የኩታ ገጠም አሠራርና የግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት ተሰጥቶታል፤ በተለይ ማሳን በኩታ ገጠም ማደራጀት፣ የትራክተር አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የግብርና ማሽነሪ ማዕከላትን ማቋቋም እና የአርሶ አደሮችን ተሳትፎ ማሳደግ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማ። ይህም ከባሕላዊ የእርሻ አሠራር ወደ ዘመናዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን ያግዛል።

የአማራ ክልልም ለዘርፉ መዘመን በትኩረት እየሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፤ የተበታተኑ ማሳዎችን በኩታ ገጠም ማደራጀትና ለትራክተር አገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ የዘርፉን ስኬታማት ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ነው ቢሮው ያመላተው።

ይህን መነሻ በማድረግ በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮችን እና ሌሎች የዘርፉን ባለድርሻዎች የኩታ ገጠም እና ሜካናይዜን እርሻ ዝጅት ሥራዎችን በተመለከተ በኩር በስልክ አነጋግራቸዋለች፡፡

የወልቃት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ቃብትያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አማኑኤል ተስፋ ማርያም በ200 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ላይ ይገኛሉ። አርሶ አደሩ በዘንድሮው የምርት ዘመን በዋናነት ማሾ እና ሰሊጥ በሰፊው ለማምረት ዝግጅት ማድረጋቸውን ለበኩር ገልጸዋል።

አቶ አማኑኤል እንደተናገሩት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ሥራቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ (የእርሻ ሜካናይዜሽን) በመደገፍ እያከናወኑ ነው። ማሳውን በትራክተር ደጋግመው እያረሱ ነው፤ አስፈላጊ ግብዓቶችንም አሟልተዋል።

ለ2018/2019 የምርት ዘመን 150 ሄክታር መማሳቸውን በማሾ ለመሸፈን ማቀዳቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ ከዚህም አንድ ሺህ 500 ኩንታል ያህል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። ዕቅዱን ለማሳካት ደግሞ የመሬት ዝግጅትን፣ የዘር ምርጫን እና የግብዓት አቅርቦትን በተገቢው ወቅት ማከናወናቸውን አስረድተዋል።

የእርሻ ሥራቸው ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድልም እየፈጠረ ነው። በቋሚነት ከ15 በላይ ሠራተኞች እና በእርሻ ወቅቶች ደግሞ እስከ 300 ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አክለዋል።

አቶ አማኑኤል እንደሚሉት፣ በትራክተር የሚከናወን እርሻ መሬቱን በጥልቀት ስለሚያርስ የአፈር አየር ዝውውርን ያሻሽላል፣ የዝናብ ውኃ ወደ አፈር እንዲሰርግ ያግዛል፣ አፈር እርጥበት የመያዝ አቅሙንም ይጨምራል።

በተጨማሪም በኩታ ገጠም ማረሳቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል፤ ትራክተርና ሌሎች የግብርና ማሽኖችን በቀላሉ ለመጠቀም አስችሏቸዋል። ይህም የእርሻ ወጪን ከመቀነስ ባለፈ የሥራ ጊዜን ይቆጥባል፣ የመሬት ዝግጅትን በወቅቱ እንዲከናወን ያግዛል፣ ከፍተኛ ምርት ለማግኘትም ያስችላል።

በመሆኑም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች በመደራጀት የኩታ ገጠም አሰራርን እንዲተገብሩ እና የእርሻ መካናይዜሽን በስፋት እንዲጠቀሙ ተሞክሯቸውን በማንሳት ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አወቀ መብራቱ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ561 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።

በዞኑ ከአንድ ሺህ 200 በላይ ትራክተሮች እና የተለያዩ የግብርና ማሽነሪዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ለዚህ ሥራ የሚውል ነዳጅ በወቅቱ ተደራሽ መደረጉን በማንሳትም “ይህም አርሶ አደሮች እና ባለሀብቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል” ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የሰሜን ሽዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው ዞኑ በ2018/2019 የምርት ዘመን ከ563 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል፤ በዚህም 20 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለበኩር ተናግረዋል፡፡

አማካይ ምርታማነቱን በሄክታር 37 ኩንታል ምርት ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የተያዘውን ዕቅድ ውጤታማ ለማድረግ ከንቅናቄ ጀምሮ የግብአት ስርጭቶችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እስከ ማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ለማልማት ከታሰበው አጠቃላይ መሬት ውስጥ በኩታ ገጠም ለማረስ በዕቅድ የተያዘው ከ308 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ነው፡፡ ከዚህም 14 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ቡድን መሪው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይ ከአንድ መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 170 ትራክተሮችን በመጠቀም መታረሱን ተናግረዋል፡፡

አቶ አበበ አክለውም የኩታ ገጠም እና የእርሻ መካናይዜሽን የምርት ወጪን በመቀነስ፣ ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2018/2019 ምርት ዘመን 412 ሺህ 480 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የነገሩን ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ቤዛዊት ጌታሁን ናቸው፡፡

ከዚህም 17 ነጥብ 56 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፤ ለስኬቱ ደግሞ ከመሬት ዝግጅት በተጨማሪ ግብዓትን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የእርሻ ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ግንዛቤ ተፈጥሯል፤ በዚህም አርሶ አደሩን ከበሬና ከፈረስ ጫንቃ በመውጣት ጊዜ እና ወጭ ቆጣቢ ወደ ሆነ ቴክኖሎጂ በማሸጋገር ውጤት መገኘቱን ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ 30 ሺህ 270 ሄክታር መሬት በትራክተር ማረስ መቻሉንም አብነት አንስተዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ምርታማነትን ለማሳደግ በተመሳሳይ ማሳ ተመሳሳይ ሰብሎችን ማልማት በሚል አንድ መቶ ዘጠና ሺህ ሄክታር ያህል ማሳ በኩታ ገጠም ማረስ መቻሉን  እርሻን  መጠቀም  ተችሏል  ብለዋል፡፡ይህም በአርሶ አደሮቸ መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ያሰችላል፤ በእህል ስብሰባ ወቅትም ማሳው ላይ እንዳለ ከዩኒየኖች እና ከፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ይህ እያደገ የመጣና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ከ324 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እና ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለመጀመሪያ ዙር እርሻ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በአብክመ ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምሳሉ ጎባው በ2018/2019 የምርት ዘመን የሚሠሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

አቶ አምሳሉ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው፤ በዚህም በምርት ዘመኑ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

ከተያዘው አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ደግሞ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት በኩታ  ገጠም መታረሱን ነው ለበኩር የተናገሩት፡፡

ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ እና ጤፍ ትኩረት ተሰጥቶባቸው   የሚዘሩ ሰብሎች መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

በኩታ ገጠም ከማረስ ባለፈ የአርሶ አደሩን ሕይወት እና ጉልበት አቅላይ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን  መጠቀም ትኩረት ከተሰጣቸው መካል ይጠቀሳል፤ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን  ሄክታር መሬት በትራክተር ይታረሳል ተብሎ መታቀዱን በማንሳት እስካሁን ባለው ስድስት መቶ ሺህ ሄክታር መሬቱ በትራክተር መታረሱን አቶ አምሳሉ አስታውቀዋል፡፡

ዘመናዊ የኩታ ገጠም እርሻ እና የሜካናይዜሽን እርሻ የአሠራር ዘዴ የአርሶ አደሩን የትብብር እና የመደጋገፍ ሥራ የማሳደግ፣ የሰብል ልማቱን ለመንከባከብ፣ ለበሽታ አሰሳ ቅኝት፣ ለባለሙያ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የደረሰውን ምርት ለመሰብሰብ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ ስራም እስካሁን ሁለት ሺህ አራት መቶ አራት ትራክተር ለእርሻ ስራው መጠቀም ተችሏል፡፡ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በግብዓት ስርጭትም ሆነ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ላይ ጥሩ እቅስቃሴ ያለበት ዓመት መሆንኑ  ነው የተናገሩት፡፡

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሰኔ 15   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here