የ32ቱ ምርጥ ቡድኖች ፍልሚያ ዛሬ ይጀመራል፡፡ ፉክክሩ ከእያንዳንዱ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ፍጹም ትኩረትን የሚሻበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ፈፅሞ የማይሰራበት እና የዓለም ትኩረት ወደ ጥሎ ማለፉ የሚያዘነብልበት አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ተጨማሪ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች እና አስደናቂ የፍጹም ቅጣት ምቶች ይጠበቃሉ፡፡
የዘንድሮው ዓለም ዋንጫ ክስተት ኩራሳኡ እንደሆነች የዘ ቴሌግራፍ መረጃ ያመለክታል፡፡ በሕዝብ ቁጥር አነስተኛዋ ሀገር በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በዓለም ዋንጫው የተሳተፈችው፡፡ ከጀርመን ጋር ባደረገችው ጨዋታ ሰባት ለአንድ ብትሸነፍም ታሪክ መስራቷን ግን ያስቆማት የለም፡፡
ኩራሳኡ ምንም እንኳ ብዙ ግምት የተሰጣት ሀገር ባትሆንም በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ ግን ግብ ማስቆጠር መቻሏ ለሀገሪቱ እግር ኳስ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ኩራሳኡ ከኢኳዶር ጋር ያለምንም ግብ በተለያየችበት ጨዋታ ግብ ጠባቂው ኤሎይ ሩም 15 ኳሶችን ማዳኑ አይዘነጋም፡፡ ይህም በዓለም ዋንጫ ታሪክ ግቡን ሳያስደፍር ብዙ ኳስ ያዳነ ግብ ጠባቂ መሆን ችሏል ይላል የፊፋዶት ኮም መረጃ፡፡ በዚህ ጨዋታም ደሴቷ ሀገር የመጀመሪያውን ታሪካዊ ነጥብ ማግኘቷ የሚታወስ ነው፡፡
ኬፕ ቨርዲም አስደናቂ አፍሪካዊት ሀገር ስትሆን ከኡራጓይ ጋር ሁለት አቻ በተለያየችበት ጨዋታ የመጀመሪያ ግቦችን በማስቆጠር አዲስ ታሪክ ማስመዝገቧ አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳን ቱኒዚያን ጨምሮ የተወሰኑ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ከምድባቸው ቢሰናበቱም የአፍሪካ ሀገራት ተሳትፎ ዘንድሮ ተስፋ ሰጪ ሆኗል፡፡ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ እንደ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ኮትዲቫር፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬፕ ቨርዴ ያሉት ሀገራት የአፍሪካን ክብር ያስጠብቃሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
የፈረንሳዩ ኮከብ ኪሊያን ምባፔ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ መሆን ችሏል፡፡ ምባፔም በኦሊቨር ዠሩድ ተይዞ የነበረውን 58 ግብ ክብረወሰን ተሸግሯል፤ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 60 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ካናዳዊው አልፎንሶ ዴቪስ ከቶጎ ጋር በተደረገው ጨዋታ በዘጠነኛው ሴኮንድ ላይ ያስቆጠራት ግብ በውድድሩ ታሪክ ፈጣኗ ሆና ተመዝግባለች።
በሌላ በኩል የስፔኑ ታዳጊ ላሚን ያማል የዓለምን ትኩረት ስቧል፡፡ የ18 ዓመቱ ያማል የኮከብ ተጫዋች (Golden Ball) ሽልማትን ለማሸነፍ እየተፎካከረ ነው፡፡ የሮናልዶ ናዛሪዮን የ21 ዓመት የቆየ ታሪካዊ ክብረወሰን ለመስበር ተቃርቧል፡፡ የ18 ዓመት ታዳጊ ሽልማቱን ማሸነፍ ከቻለ የሮናልዶን የ28 ዓመታት (እ.አ.አ ከ1998 እስከ 2026) የዕድሜ ክብረወሰን በሰፊ ልዩነት በመስበር በታሪክ ትንሹ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች መሆን ይችላል፡፡ ታዳጊው ስፔን ሳውዲ አረቢያን አራት ለባዶ ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ አስደናቂ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ይህም በዓለም ዋንጫ ታሪክ ግብ ያስቆጠረ ስምንተኛው ትንሹ ተጫዋች በመሆን ህልሙን አሳክቷል፡፡
እንደ ሊዮኔል ሜሲ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ሉካ ሞድሪች እና ኔይማር ጁኒየር ላሉ የዓለማችን የክፍለ ዘመኑ ታላላቅ ከዋክብት የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ይሆናል፡፡ በዚህ ግዙፉ የዓለም ዋንጫ መድረክ አሰልጣኞችም ታሪክ ሠርተዋል፡፡ የኩራሳኡ አሰልጣኝ ዲክ አድቮካት በ78 ዓመታቸው ብሄራዊ ቡድኑን በመምራት በዓለም ዋንጫ ተሳትፈዋል፡፡ ይህም በዓለም ዋንጫ ታሪክ አንጋፋው አሰልጣኝ መሆን ችለዋል፡፡
የጋናው አሰልጣኝ ካርሎስ ኬይሮዥም ሌላ አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ በሰባ ዓመታቸው ፓናማን በማሸነፍ በዓለም ዋንጫው ድል ያደረገ በዕድሜ ትልቁ አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡ ጀርመናዊው ግብ ጠባቂው ማኑኤል ኑየር አዲስ ክብረወሰን ጨብጧል፡፡ ኑየር በ40 ዓመቱ ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን በመጫወት አንጋፋው ጀርመናዊ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘው የዘንድሮው ዳኝነት ውድድሩን ይበልጥ ፍትሃዊ እያደረገው ሲሆን በቀጣዮቹ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችም ያልተጠበቁ ክስተቶችን ያስመለክቱናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፊፋ ይፋ ባደረገው አዲስ አሰራር መሰረት የቫር ዳኞች የወሰኑትን ውሳኔ ከነ ምክንያቱ ዋናው ዳኛ በማይክሮፎን ስታዲየሙ ውስጥ ለሚገኙ ደጋፊዎች እና በቴሌቪዥን ለሚከታተሉ ተመልካቾች በግልጽ እንዲያብራራ እየተደረገ ነው፡፡
በዘንድሮው ውድድር ላይ የእግር ኳሱ ዓለም የደረሰበት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡ የተጫዋቾችን የድካም መጠን እና የልብ ትርታ የሚለኩ ሳይንሳዊ አልባሳትም (GPS Vests) ከአሰልጣኞች አግዳሚ ወንበር ጋር በኮምፒውተር የተገናኙ በመሆናቸው ተጫዋቾች ከመጎዳታቸው በፊት ለመቀየር አስችሏቸዋል፡፡
የዓለም ዋንጫ አዲሱ ኳስ (Adidas Trionda) በውስጡ የያዘው ማይክሮቺፕ ተጫዋቾች ኳሷን የነኩበትን ቅጽበት በሴኮንድ 500 ጊዜ ለቫር ዳኞች በቀጥታ ያስተላልፋል፡፡ በስታዲየሞች ውስጥ የተገጠሙት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ካሜራዎች የተጫዋቾችን የሰውነት አቀማመጥ በ29 የተለያዩ አንግሎች በመቅረጽ ከጨዋታ ውጪ (የኦፍሳይድ) ውሳኔዎችን በሴኮንዶች ውስጥ እንዲለዩ ተደርገዋል፡፡
በሰሜን አሜሪካ ያለውን ከፍተኛ ሙቀት ለመቋቋም በየጨዋታው ሁለት ጊዜ የተፈቀዱት የውሃ እረፍቶች አሰልጣኞች በጨዋታ መሃል አዳዲስ ታክቲካዊ መመሪያዎችን የሚያስተላልፉበት አነስተኛ እረፍት ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር የቢሊየነሮች ድግስ ይመስላል፡፡ የትኬት ዋጋው እጅግ ውድ መሆኑን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘግቧል፡፡ የስታዲየም የመኪና ማቆሚያ ዋጋ ብቻ እስከ 300 ዶላር እየተጠየቀበት መሆኑን መረጃው ያስነብባል፡፡
ይሁን እንጂ በፊፋ ይፋዊ መረጃ መሰረት ውድድሩ ከተጀመረበት የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ወደ ሰሜን አሜሪካ የገቡ ሲሆን ይህም በዓለም ዋንጫ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የቱሪስት ፍሰት ተመዝግቧል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


