የውኃ ወለድ በሽታዎች በተበከለ ውኃ ውስጥ በሚተላለፉ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ምክንያት የሚመጡ ናቸው፡፡ ለእነዚህ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን የምንጋለጠው የተበከለውን ውኃ ለመጠጥ፣ ለምግብ ዝግጅት እና ለሌሎች አገልግሎቶች ስናውለው ነው፡፡
በርካታ ታዳጊ ሀገራት በተለይ በገጠር አካባቢ ትክክለኛ የውኃ ማጣሪያ የላቸውም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ አቅርቦቱ በጣም አናሳ ነው፡፡ በዓለማችን ላይ 844 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መሠረታዊ የመጠጥ ውኃ አገልግሎት የላቸውም፡፡ በመሆኑም ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውኃን የመጠቀም አጋጣሚያቸው ከፍተኛ በመሆኑ ለውኃ ወለድ በሽታዎች ይዳረጋሉ፡፡
በተለይም በታዳጊ ሀገራት የውኃ ወለድ በሽታዎች አሳሳቢ አደጋ ከሚባሉት የጤና እክሎች መካከል 80 በመቶውን እንደሚሸፍኑና ከሁሉም በሽታዎች መካከል አንድ ሦስተኛውን እንደሚይዙ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና የዩኒሴፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የውኃ ወለድ በሽታዎች የሚከሰቱት በሽታ አምጪ ረቂቅ ተሕዋስያን የውኃ ምንጮችን በመበከላቸው ምክንያት ነው፡፡ ውኃ በባክቴሪያ፣ ቫይረሶች እና ጥገኛ ተህዋሲያን ሊበከል ይችላል፡፡ እነዚህ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን መርዛማ ፈሳሾቻቸው እና ሌሎች በካይ ንጥረነገሮች አንድ ላይ ሆነው እንደ ኮሌራ፣ ተቅማጥ፣ ታይፎይድ፣ አሜባ፣ ሄፓታይተስ ኤ፣ የአንጀት እና የጨጓራ ችግር፣ ጃርዲያ፣ እከክ እና የትል ኢንፌክሽኖችን የመሳሰሉ ከባድ በሽታዎችን ያስከትላሉ፡፡
ውኃ እንዴት ሊበከል ይችላል?
በሽታ አምጭ ረቂቅ ተሕዋስያን ከሰው እና ከእንስሳት ዐይነምድር ሊወጡ ይችላል፡፡ በቂ ያልሆነ የንፅህና አጠባበቅ ለአብነትም የመጸዳጃ ቤት እጥረት እና ትክክለኛ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ዓለመኖር ውኃን ሊበክል ይችላል፡፡ ቆሻሻን በአግባቡ አለማስወገድም በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ወደ ውኃ አቅርቦት(ማጠራቀሚያ) ውስጥ እንዲገቡ ያስችላቸዋል፡፡ ያልተጣራ፣ ያልታከመ ወይም ያልፈላ ውኃ መጠጣት እና ለምግብ መሥሪያ ማዋል ደግሞ ለውኃ ወለድ በሽታ የመያዝ አጋጣሚን ይጨምራል፡፡
የመጠጥ ውኃ በሚገኝበት አካባቢ የእርሻ ማዳበሪያዎችን እና ፀረ-ተባይ መድሃኒቶችን መጠቀም ባክቴሪያን እና ኬሚካሎችን ወደ ውኃው ዘልቀው እንዲገቡ በማድረግ ብክለትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ከፋብሪካዎች የሚወጡ የኬሚካል ቅሪቶች እና መርዛማ ንጥረ ነገሮች ውኃን ሊበክሉ ይችላሉ፡፡ እንደ ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችም በሽታ አምጪ ተህዋሲያን እና ብክለትን ወደ ውኃ ምንጮች ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ ደካማ የንፅህና አጠባበቅ ስርዓቶች እና የተበላሹ መሠረተ ልማቶች በእነዚህ ክስተቶች የውኃ ወለድ በሽታዎችን አደጋ የበለጠ ያባብሳሉ፡፡
ምልክቶች
የውኃ ወለድ በሽታዎች እንደ አይነታቸው ሁሉ የተለያዬ ምልክቶች ቢኖራቸውም ሁሉም በሚባል ደረጃ ግን ትኩሳት፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ የሆድ ሕመም (ቁርጠት)፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት እና የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ትውከት፣የሰውነት ፈሳሽ እያለቀ ሲሄድ ደግሞ የቆዳ መገርጣት፣ ውኃማ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ደም የቀላቀለ ተቅማጥ የሆድ መነፋት እና መጥፎ ጠረን አላቸው፡፡
ሕክምናዎቹ
የውኃ ወለድ በሽታ ምልክቶች የታዩበት ሰው በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄድ ይመከራል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ተቅማጥ እና ትውከት ስለሚኖራቸው የሰውነት ፈሳሽ ሊሟጠጥ ይችላል፡፡ በመሆኑም የወጣውን ፈሳሽ መተካት ይገባል፡፡ በተጨማሪም አንቲባዮቲክስ ወይም ፀረ-ቫይረስ እና ባክቴሪያ መድኃኒቶች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡
እንዴት እንከላከል
የውኃ ወለድ በሽታዎች በቀላሉ ልንከላከላቸው የምንችላቸው ቢሆኑም አሁንም በዓለም ዙሪያ ሚሊዮኖችን የሚያጠቁ የጤና ችግሮች ናቸው፡፡ ንጹህ ውኃ፣ ጥሩ የአካባቢ ንጽህና እና የሕዝብን ግንዛቤ መጨመር የውኃ ወለድ በሽታዎችን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ውኃን አፍልቶ በመጠቀም ወይም በማጣራት የውኃ ወለድ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል፡፡ የውኃ ምንጮች በሰው እና በእንስሳት ንክኪ እንዳይበከሉ ለመከላከል የንፅህና አጠባበቅ የሚሠጡ ተቋማትን ማሻሻል፤ በተለይም ምግብን ከመመገብ በፊት እና ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅን በሳሙና እና ንጹህ ውኃ መታጠብ ተገቢ ነው፡፡ እንደ ሄፓታይተስ ኤ ላሉ በሽታዎች ደግሞ ክትባቶችን መውሰድ በበሽታው የመያዝ አደጋን ይቀንሳል፡፡
የውኃ ወለድ በሽታ መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና የመከላከያ ስልቶችን በተመለከተ ግንዛቤን ማሳደግ፣ እንዲሁም የንፁህ ውኃ፣ የአካባቢ እና የግል ንፅህና አጠባበቅ ልማዶችን በተመለከተ ሕዝብን ማስተማር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ጠቁሟል፡፡ ምግብን በደንብ አብስሎ መመገብ፣ አስተማማኝ ማከማቻ ማዘጋጀት እና ጥሬ ወይም ያልበሰለ ምግብን ከመመገብ መቆጠብን ጨምሮ ተገቢውን የምግብ ደኅንነትን መጠበቅ ከበሽታው ለመጠበቅ ይረዳሉ፡፡ ሰዎች የውኃ ወለድ በሽታዎች በብዛት በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ሲጓዙ ጥንቃቄ ማድረግን መዘንጋት እንደሌለባቸውም መረጃው ያስገነዝባል፡፡
በተጨማሪም ፍትሐዊ የንፁህ ውኃ አቅርቦትን ማረጋገጥ፣ የንፅህና አጠባበቅ አሠራሮችን ማስተዋወቅ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የምግብ አያያዝ ዘዴዎችን በመከተል እና ስለበሽታዎች ግንዛቤን በማሳደግ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ለመፍጠር የሚያስችል ውጤታማ የመከላከያ ርምጃዎችን በመተግበር የውኃ ወለድ በሽታዎችን መከላከል እንደ ሚቻል መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
ጤና አዳም
- በዓለም አቀፍ ደረጃ በውኃ ወለድ የሚተላለፉ በሽታዎች በዋነኛነት በልጆች ላይ የሚከሰቱት በንጽህና ጉድለት እና በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ በመሆኑ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ በሽታዎችም ለሕይወት አስጊ ናቸው፡፡
- ከውኃ ወለድ በሽታዎች መካከል 88 በመቶው በንፅህና አጠባበቅ፣ በቂ ያልሆነ የንፅህና መጠበቂያ ተቋማት እና ንፁህ ባልሆኑ የውኃ አቅርቦቶች ምክንያት ሊከሰቱ እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡
- የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)እና የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል (CDC)እንዳወጡት መረጃ በየዓመቱ አንድ ነጠብ አራት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በውኃ እጥረት እና ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ ሕይዎታቸውን ያጣሉ፡፡
ምንጮች፡-https://www.news-medical.net/፣ WHO
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


