ማዘር ቴሬዛ

0
286

ማዘር ቴሬዛ ለዓለም ሁሉ የፍቅር፣ የደግነት እና የርህራሄ ትልቅ ተምሳሌት የሆኑ ታላቅ ሴት ነበሩ። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1910 በአልባኒያ ሀገር ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው የልጅነት ስም አግነስ ጎንክሻ ቦያክሹ ይባል ነበር። አግነስ ገና በ12 ዓመቷ ላይ ሳለች በዓለም ዙሪያ ያሉ ችግረኛ ሰዎችን የመርዳት እና ሕይወቷን ለበጎ አድራጎት የመስጠት ትልቅ ምኞት እና ጥሪ በውስጧ አደረ።

ዕድሜዋ 18 ሲሆን በሰሜን አየርላንድ ወደሚገኝ የሎሬቶ እህቶች ማኅበር በመቀላቀል የመነኮስነት ስልጠናዋን ጀመረች። ከዚያም የሙያ ስሟን ማዘር ቴሬዛ በማለት ቀየረች። ብዙም ሳይቆይ ህጻናትን በነጻ ለማስተማር እና ሰዎችን ለመርዳት ወደ ሕንድ ሀገር ተጓዘች። በካልካታ ከተማ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ስታስተምር የቆየች ቢሆንም ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጭ ባሉት ጎዳናዎች ላይ የሚኖሩት እጅግ በጣም ደሃ፣ የታመሙ እና የተራቡ ሰዎች ሁኔታ ሁልጊዜ ልቧን ይሰብረው ነበር።

ማዘር ቴሬዛ መደበኛ የማስተማር ሥራዋን ትታ ሙሉ በሙሉ በጎዳና ላይ ለወደቁት ምስኪኖች ለመኖር ወሰነች። በ1950 እ.አ.አ የፍቅር ሚሲዮናውያን የተባለውን ዝነኛ የቅዱሳን ማኅበር በይፋ አቋቋመች። እሷ እና አብረዋት የነበሩት እህቶች ማንም ዞር ብሎ ያላያቸውን በበሽታ የተጠቁ ሰዎችን፣ አረጋውያንን እና መጠለያ የሌላቸውን ህጻናት ወደ ማዕከላቸው በማምጣት ፍቅርን ይመግቡ፣ ቁስላቸውን ያክሙ እና ያስተምሩ ነበር። ይህ በጎ ሥራቸው በፍጥነት እያደገ በመሄዱ በዓለም ዙሪያ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የረድኤት ጣቢያዎችን፣ ሆስፒታሎችን እና የሕጻናት ማሳደጊያዎችን ለመክፈት በቁ።

ማዘር ቴሬዛ ለዓለም ባሳዩት ወደር የሌለው ሰብአዊነት እና የሰላም ጉዞ በ1979 እ.አ.አ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አግኝተዋል። በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ “በትናንሽ ነገሮች ላይ ትልቅ ፍቅር ማሳየት” የሚለውን መርህ ተከትለው ሰርተዋል። በ1997 እ.አ.አ በ87 ዓመታቸው ካረፉ በኋላ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታላቅ የቅድስና ማዕረግ ሰጥታቸዋለች። ታሪካቸው ዛሬም ድረስ እኛ በቤታችን፣ በትምህርት ቤታችን እና በአካባቢያችን ላሉት ሰዎች ደግ መሆን እንደምንችል የሚያስተምር ትልቅ የብርሃን መንገድ ነው ይላል ብሪታኒካ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ ያገኘነው የሕይወት ታሪካቸው።

ተረት

ትንሹ ውሻ

በአንድ ወቅት በአንድ ትልቅ እርሻ ውስጥ ሚሎ የሚባል በጣም ትንሽ ቡችላ ነበረ። ሚሎ ከሌሎቹ ትልልቅ ውሾች በተለየ መልኩ ቁመቱ በጣም አጭር ነበር።

አንድ ቀን ማታ አንድ ሌባ የዶሮዎቹን እንቁላል ለመስረቅ ቀስ እያለ ወደ ዶሮዎቹ ቤት ተጠጋ። ትልልቆቹ ውሾች ሁሉ በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ስለነበሩ ምንም አላወቁም ነበር። ትንሹ ሚሎ ግን በጣም ንቁ ስለነበረ የሌባውን ኮቴ ወዲያውኑ ሰማ።

ሚሎ ምንም እንኳን ትንሽ ቢሆንም ምንም ሳይፈራ በከፍተኛ ድምፅ “ዋው! ዋው!” እያለ መጮኽ ጀመረ። በእሱ ጩኸት ምክንያት የቤቱው ባለቤት እና ትልልቆቹ ውሾች በድንገት ከእንቅልፋቸው ነቁ። ሌባውም ደንግጦ እግሬ አውጪኝ ብሎ ፈረጠጠ። ትንሹ ቡችላ በንቅናቄው እና በጉልበቱ የእርሻውን ዶሮዎች ሁሉ ከጥቃት አዳናቸው። ከዛን ቀን ጀምሮ ሁሉም ትልልቅ ውሾች ሚሎን ማክበር እና ማድነቅ ጀመሩ።

ምንጭ፡- የኤሶፕ ተረቶች

ሞክሩ

በሰውነታችን ውስጥ ደም በሁሉም ቦታ እንዲደርስ የሚረጨው አካል የትኛው ነው?

 

  1. በበላሁ ቁጥር አድጋለሁ፣ ውሃ በጠጣሁ ቁጥር ግን እሞታለሁ። እኔ ማን ነኝ?

 

  1. በምድር ላይ ካሉ አህጉራት ሁሉ በጣም ቀዝቃዛው የትኛው ነው?

መልስ

  1. ልባችን
  2. እሳት
  3. አንታርክቲካ

ነገር በምሳሌ

  • ሲቸግረው የመጣን እንግዳ አታባርር፦

ለተቸገሩ ሰዎች ሁልጊዜ ደግ እና አጋዥ መሆን ያስፈልጋል።

  • ካላወቁበት አይነኩት፦ ስለማናውቀው ነገር ወይም ዕቃ አስቀድመን መጠየቅ እና መማር አለብን።
  • ካላወቁበት አይነኩት፦ ስለማናውቀው ነገር ወይም ዕቃ አስቀድመን መጠየቅ እና መማር አለብን።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here