የአረንጓዴ አሻራ- ዛፍ ከመትከል ባሻገር!

0
31

በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ችግኞችን በመትከል የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘመቻ ችግኞችን በመትከል፣ የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና ዘላቂ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባትን ታላሚ ያደረገ ነው። ይህ ዘመቻ ንጹህ አካባቢና  አየር እንዲፈጠር ምክንያት በመሆን ለጤናማ ትውልድ መኖርና ለኑሮ ተስማሚ የሆነ ከባቢ እንዲፈጠር ያግዛል፡፡

በዘህ ሂደት የደን ሽፋን በማሳደግ ኢትዮጵያ በታሪክ የነበራትን ከፍተኛ የደን ሽፋን ወደነበረበት መመለስ፣ ድርቅና የተፈጥሮ ሀብት መጥፋትን በመቅረፍ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ዘላቂ ልማት ለማምጣት ይጠቅማል፡፡ ይህም የአየር ንብረት ሚዛን በመጠበቅ ለብዝሃ ህይወትና ለውሃ ሀብት ጥበቃ ይጠቅማል፡፡

በተለይም በአማራ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተዘጋጁ ችግኞች ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚ የኾኑ ሀገር በቀል ችግኞች መሆናቸው አካባቢን መልሶ ለማቋቋም ብሎም ለማላመድ ትልቅ ሚና አለው፡፡

በተለይም  ፍራፍሬዎችን፣ የእንስሳት መኖ የሚሆኑ ዝርያዎችን እና ለአርሶ አደሩ ቀጥተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ተክሎችን በማካተት መሰራቱ የአረንጓዴ ዐሻራው ወደ ምግብ ዋስትና እና ወደ ገቢ ማሻሻያ እያመራ መሆኑን ያሳያል።  የተተከሉት ዛፎችም የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የከርሰ ምድር ውኃ እንዲጠናከር፣ የውኃ ምንጮች እና ወንዞች እንደገና ወደነበሩበት እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ በተጨማሪ  በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ችግኝ በማፍላትና በመሸጥ፣ የደን ዘር በመሰብሰብ፣ የተፈጥሮ ሀብት ቦታዎችን በማልማት፣ ንብ በማነብ እና የእንስሳት መኖ በማምረት በየዓመቱ ብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል እያገኙ መሆኑ መርሃ ግብሩ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም እንዳለው ያሳያል።

በእንዲህ ያሉ ሀገራዊ የዘመቻ ስራዎች የማህበረሰብ ተሳትፎ ለተግበራዊነት፣ ለውጤታማነትና በዘላቂነት እንዲጠበቅ ለማድረግ  ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በችግኝ ማብቀያዎች፣ ተከላና እንክብካቤ ላይ ለወጣቶችና ለብዙዎች የስራ ዕድል ፈጥ[ል። ከባለቤትነት ባሻገር ሰዎች ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ዕድሜ እና መሠል ጉዳይ ሳይገድባቸው ለአንድ ዓላማ በጋራ እንዲሰለፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ ማኅበራዊ ትስስር ይፈጥራል። የማህበረሰቡ አመለካከት መቀየሩም ከቁጥር በላይ የሚታይ ስኬት ነው። “አንድም ችግኝ ያለባለቤት መተከል የለበትም” የሚለው አቀራረብ ማህበረሰቡን በቀጥታ ባለቤት በማድረግ የችግኞችን ጽድቀት እና የድህረ ተከላ እንክብካቤ አጠናክሯል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የምታደርገውን ጥረት ለዓለም በማሳየት ረገድም የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ኾኗል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አርዓያ መኾን እንድትችልም አድርጓታል።

በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዛፍ የመትከል ዘመቻ ብቻ ሳይሆን የአፈር ጥበቃን፣ የምግብ ዋስትናን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የገጠር ኢኮኖሚ ማነቃቂያን እና የአካባቢ ዘላቂነትን በአንድ ላይ ያቀፈ ልማታዊ እንቅስቃሴ ነው። በተለይም በቀጣይ ዓመታት የተከላው ጥራትና የድህረ ተከላ እንክብካቤ ተጠናክሮ ከቀጠለ፣ መርሃ ግብሩ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም የአካባቢና የኢኮኖሚ ለውጥ ምሳሌ ይሆናል፡፡

በኲር የሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here