“የከተማዋ ባለቤት መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል!”

0
2517

ባህር ዳር በጣና ሀይቅና በአባይ ወንዝ ተከባ የምትገኝ ማራኪ ከተማ ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማዋን ገፅታ ከመሰረቱ የሚቀይር ግዙፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የዚህን ፕሮጀክት ሂደት፣ የከተማዋን ራዕይ፣ የነዋሪዎችን ተሳትፎና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡

እስኪ ራስዎን ለአንባብያን ያስተዋውቁልን?

እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ ተሻገር አዳሙ እባላለሁ፤ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በታሪክ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በአመራርና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለሁ፡፡

አጠቃላይ እስካሁን ወደ 15 ዓመት አካባቢ የስራ አገልግሎት አለኝ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንደያዝኩ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማበር ወረዳ መምህር በመሆን ስራ ጀመርኩ፡፡

በዚያው ወረዳ ላይ የሲቪል ሰርቪስ እና የትምህርት ሀላፊ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ በ2006 ዓ.ም መጨረሻ ወደ ባህር ዳር በመምጣት ከክፍለ ከተማ አስተዳዳሪነት ጀምሮ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ሀላፊ እንዲሁም የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ሆኜ አገልግያለሁ፡፡

ላለፉት ሶስት አመታት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኜ እየመራሁ እገኛለሁ፡፡

ባህር ዳር ከተማን እንዴት ይገልጿታል? ለከተማዋስ ምን አይነት ራዕይ አለዎት?

ባህር ዳር በአባይ እና በጣና ተከባ ያለች፣ በተፈጥሮ የታደለች እና በጣም የምታምር ከተማ ናት፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩ አባቶቻችን ከተማዋን በጥሩ ፕላን ነው የመሯት፡፡ እኛ አሁን እየሰራን ያለነው ያላትን ውብ ተፈጥሮ የበለጠ የማውጣት እና የማጉላት ስራ ነው፡፡

ለባህር ዳር ያለን ራዕይ በሶስት ምሰሶዎች ላይ ያረፈ ነው፡፡ አንደኛው፡- ደረጃዋን የጠበቀች፣ መላው አለምን የምትስብ የቱሪስት ከተማ ሆና ማየት ነው፡፡ ለዚህም አለም አቀፍ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሎጂዎች እና ሪዞርቶች እያስገነባን እንገኛለን፡፡

ሁለተኛው በማኑፋክቸሪንግ እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የዳበረች፣ ባለሀብቶችን የሳበች እና ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል የምትፈጥር ከተማ እንድትሆን ነው፡፡

ሦስተኛው ባህር ዳር እ.ኤ.አ በ2012 በዩኔስኮ “የትምህርት ከተማ” ተብላ የተሰየመች በመሆኗ አዲሱን ትውልድ በፈጠራ የሚያነቃቁ ተቋማት ያሏት ምርጥ የትምህርት ማዕከል ሆና እንድትቀጥል ማድረግ ነው፡፡

አሁን በከተማዋ በስፋት እየተሰራ ስላለው የኮሪደር ልማት እናውራ፡፡ የኮሪደር ልማቱ አጠቃላይ እቅድ እና አፈፃፀም ምን ይመስላል?

የኮሪደር ልማት ከተሞችን በማነቃቃት ረገድ ያለው ሚና እጅግ ትልቅ ነው፡፡ ባህር ዳር ይህንን ስራ ከጀመሩ ቀዳሚ ከተሞች አንዷ ናት፡፡

ወደ ስራ የገባነው የ31 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጥናት እና ዲዛይን በማዘጋጀት ነው፡፡ ይህን በአንዴ ማጠናቀቅ ስለማይቻል በምዕራፍ ከፋፍለን እየሰራነው ነው፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ አምና ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው 2.5 ኪ.ሜ የሚሸፍን ሲሆን ከአጅፕ እስከ ስካይ ሆቴል ያለውን ቦታ ያካትታል፡፡

እዚህ ላይ ባህር ዳርን ከጣና ጋር በማገናኘት ከስምንት በላይ ቦታዎች ላይ ሐይቁን በመክፈት ከተማዋ አየር እንድታገኝ አድርገናል፡፡ ሹምአቦ መናፈሻ፣ ርዕሰ መስተዳድር እና በአልማ መካከል ያለው መናፈሻ፣ እንዲሁም ዘንባባ ፓርክ በሚገርም ሁኔታ ተሰርተዋል፡፡

የፈጣን ምግብ መሸጫዎች፣ የሳይክልና የባስ ስቴሽኖች፣ እንዲሁም ሰፋፊ የግራናይት እግረኛ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ የህንፃ ቀለም እና የአጥር ዲዛይንም ወጥ እንዲሆን አድርገናል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ ወደ 6.2 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን በተለይ ከአልማ ዋተር ፍሮንት ያለው 800 ሜትር አካባቢ የነበረውን የተጎሳቆለ ሰፈር ከመልሶ ማልማት ጋር አያይዘን የሰራንበት ነው፡፡

ሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ በጣም ሰፊው እና ዘንድሮ እየሰራንበት ያለው ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ ከጊዮን እስከ ዘጌ መገንጠያ፣ ከአሮጌው የአባይ ድልድይ እስከ ቅዱስ ገብርኤል፣ ከጊዮርጊስ እስከ ፓፒረስ፣ እንዲሁም 3.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአባይ ማዶ (ዲያስፖራ አካባቢ) ስራዎችን ያካትታል፡፡

በአጠቃላይ በ5 እና 7 አመት ያልቃል ያልነውን የ31 ኪ.ሜ እቅድ ባለን ፈጣን የስራ እንቅስቃሴ ምናልባትም በሶስት ወይም በአራት አመት ሙሉ በሙሉ ልንጨርሰው እንችላለን፡፡

ሰፈሮችን ስታለሙ የዜጎችን የካሳ አከፋፈል ሂደት እንዴት ፈታችሁት?

የልማት ስራ ሲሰራ ለአብዛኛው የከተማ ነዋሪ ጥቅም ሲባል የጥቂቶች ይዞታ መነካቱ አይቀርም፡፡ ከአልማ ወደ ዋተር ፍሮንት በነበረው ስራ ከ250 በላይ ነዋሪዎችን አስነስተናል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ከ150 በላይ የሚሆኑት በኬንዳ እና በሳጠራ ቤት ውስጥ በ10 ወይም 20 ካሬ ላይ ይኖሩ የነበሩ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ነበሩ፡፡

እኛ ግን ለሁሉም 100 ካሬ ሜትር ቦታ (ትክ) ሰጥተናቸዋል፡፡ ህጋዊ የግል ይዞታ የነበራቸውንም ቦታ እና ተገቢውን የገንዘብ ካሳ ከፍለን አስተናግደናል፡፡

የኮሪደር ልማቱን የፋይናንስ ምንጭ (በጀት) ከየት ነው የምታገኙት? የህዝቡስ አስተዋፅኦ ምን ይመስላል?

ይህ ትልቅ ሀብት የሚጠይቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ የኮሪደር ልማት ስራን የራሳችንን የውስጥ ገቢ በማሳደግ ነው የምናከናውነው፡፡ ከሶስት አመት በፊት አመታዊ ገቢያችን 2.8 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን ዘንድሮ እስካሁን ብቻ 7.7 ቢሊየን ብር ሰብስበናል፡፡

ኮሪደር እያለማህ ስትሄድ የመሬት (የሊዝ) ዋጋ ስለሚያድግ ገቢህም ይጨምራል፡፡ ከዚህ ውስጥ በቀጥታ ለከተማዋ አገልግሎት የሚውል ወደ 2 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገቢ አለን፡፡ እንዲሁም የገንዘብን የጊዜ ዋጋ ታሳቢ በማድረግ በብድርም ጭምር እየሰራን ነው፡፡

ከገንዘቡ ባሻገር የማህበረሰቡ ተሳትፎ አስደናቂ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በቀጥታ ለኮሪደር ልማት ከ500 ሚሊየን ብር በላይ አዋጥቷል፡፡ ለምሳሌ ከጊዮርጊስ እስከ ፓፒረስ ፊት ለፊት ያሉት ነዋሪዎች የግራናይት ንጣፉን በራሳቸው ወጪ እያነጠፉ ሲሆን ከ100 ሚሊየን ብር በላይ አውጥተዋል፡፡

ወጣቶችም በራሳቸው አስተሳሰብ እና ወጪ ፓርኮችን አዘምነዋል፡፡ ነዋሪው ዛሬ የከተማዋ ባለቤት መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከገፅታ ግንባታ ባለፈ በኢኮኖሚው እና በስራ ባህል ላይ ያመጣው ለውጥ አለ?

አዎ! ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል፡፡ አንደኛው የስራ እድል ፈጠራ ነው፡፡ በዚህ አመት እና አምናን ጨምሮ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ብቻ ከ32 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

በቀን እስከ 600 ወጣት ስራ ላይ እየዋለ ነው፡፡ ሁለተኛውና ትልቁ ደግሞ የስራ ባህል መቀየሩ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በቀን 8 ሰዓት ለመስራት ይከብደው የነበረው ማህበረሰብ አሁን በሁለት እና በሶስት ፈረቃ ሌሊት ጭምር እያመሸ እየሰራ ነው፡፡ በዚህም ሶስትና አራት አመት ይፈጃሉ የተባሉ ፕሮጀክቶች በጥቂት ወራት ውስጥ ማለቅ ችለዋል፡፡

ከመሰረተ ልማት ቅንጅት እና ጥበቃ ጋር ተያይዞ ምን እየሰራችሁ ነው?

ቀደም ሲል አስፋልት ከተሰራ በኋላ ውሃ፣ ቴሌ ወይም መብራት የራሳቸውን መስመር ለመቅበር መንገዱን ይቆርጡት ነበር፡፡ የኮሪደር ልማቱ ግን ይህን አሰራር አስቀርቷል፡፡ ዲዛይኑ ሲዘጋጅ ሁሉም ተቋማት ኬብሎቻቸውን እና ቱቦዎቻቸውን በአንድ ላይ ከእግረኛ መንገዱ ስር አቀናጅተው ይቀብራሉ፡፡ በመሆኑም መንገዱ በድጋሚ አይቆፈርም፡፡

ይሁን እንጂ፣ የተቀበረን ኬብል እና ትራንስፎርመር የሚሰርቁ ግለሰቦች ያጋጥሙናል፡፡ እንዲሁም መናፈሻዎች ውስጥ ውብ አበባዎችን የሚበጣጥሱ፣ በእግረኛ መንገድ ላይ ሳይክል የሚነዱ እና በመኪና መንገድ ላይ እግረኞች የሚሄዱበት የልማድ ክፍተት አለ፡፡ ይህንን ለማረም እያንዳንዱ ሰው የተሰራለትን መሰረተ ልማት “የእኔ ነው” ብሎ እንዲጠብቅና እንዲንከባከብ ጥሪ አደርጋለሁ፡፡

ለሰጡን ሰፊ እና ግልፅ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሰኔ  22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here