የማን ሀሳብ ነው?

0
248

ጠዋት ከእንቅልፍ ስንነሳ በውስጣችን የሚመላለሱት ሀሳቦች፣ የዛሬዎቹ ውሳኔዎቻችን ወይም በአንድ ሰው ላይ የሰነዘርነው ፍርድ በእርግጥ የራሳችን ናቸው? ወይስ እኛ እንደ አእምሯችን ባለቤት የምናስባቸው እነዚህ ሂደቶች ከውጭ በሚመጡ ተጽእኖዎች የሚነዱ የውክልና አስተሳሰቦች ናቸው?

ፈላስፋው ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን በታዋቂው  “ሰልፍ ሪሊያንስ” ጽሁፉ  ላይ “ሁላችንም የአባቶቻችን ጥቅሶች ነን” ብሏል።  እኛ በራሳችን ተሞክሮ ብቻ የተገነባን ሳይሆን በሺህ ዓመታት የአስተሳሰብ ድንጋዮች ላይ የምንራመድ ፍጡራን መሆናችንን ታዝቧል።  ይህ ጽሁፍ የአባቶችን ዕውቀት መቃወም አይደለም። የራስን ሐሳብ እና ማንነት ስለመፈለግ  ነው።

አንድ ሰው የራሱን ማንነት ከመገንባት ይልቅ የሌሎችን “ጥቅሶች” ወይም የውጭ ተጽእኖዎችን በመድገም ብቻ የሚኖር ከሆነ ሊገጥሙት የሚችሉ ከባድ ጉዳቶች አሉ።

የመጀመሪያው  የውስጣዊ ግጭት መፈጠር ነው። አንድ ሰው የአባቶቹን የቆዩ እሴቶች (ለምሳሌ፡ ወንድ ልጅ ሆነህ አታልቅስ የሚል ግትር ወግ) በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እውነታዎች ውስጥ ለማራመድ ሲሞክር ከፍተኛ የሆነ “የአስተሳሰብ ግጭት” ውስጥ ይገባል። ይህ ግጭት ሰውየውን በውስጥ በኩል ያደክመዋል፣ ያቀጭጨዋል፤ ምክንያቱም እየኖረ ያለው ለራሱ ሳይሆን ለሁለት የተለያዩ ዘመናት ስብዕናዎች ነው። ይህ ዘመን ተጋላጭነትን የሚያበረታታ ነው።

ሁለተኛው የአእምሮ ባርነት ነው። የራስን ማንነት አለመገንባት ማለት አእምሮን ለሌሎች አሳልፎ መስጠት ነው። ይህ ደግሞ የምንወስናቸው ውሳኔዎች (ምን እንግዛ፣ ምን እንመን፣ በማን እንፍረድ) በቴክኖሎጂ ስልተ-ቀመሮች የሚወሰኑ ከሆነ ሰው እንደ ነጻ ፍጡር ሳይሆን እንደ ፕሮግራም የተደረገ ማሽን ይሆናል።

ሦስተኛው  የህይወት ትርጉም ለማጣት ያጋጥማል። ቪክቶር ፍራንክል እንደሚለው ሰው ማንነቱን ካልገነባ የህይወቱን ዓላማ መለየት አይችልም። ስኬትን በራሱ መለኪያ ሳይሆን በህብረተሰቡ ወይም የመዝናኛ ኢንዱስትሪው በተቀረጸው ጠባብ “ቁሳዊ መለኪያ” ሲለካ በመጨረሻ የሚደርሰው “ባዶነት” ላይ ነው። ማንነቱን ያልገነባ ሰው ህይወቱ የራሱ የፈጠራ ስራ ሳይሆን የሌሎች የድራማ ስክሪፕት ቅጂ ይሆናል።

አራተኛው የማደግ አቅምን ይገድባል። ማንነትን መገንባት ማለት ካለፉት ትምህርት መቅሰም፣ ወደ ፊት ማሰብ፣ ነገር ግን ለእድገት የማይጠቅሙ ግድግዳዎችን መስበር ነው። ይህንን የማያደርግ ሰው በድሮ መዝጊያዎች  ውስጥ ይታሰራል። አዲስ ነገርን ለመቀበል ወይም አዲስ መንገድ ለመፍጠር ይፈራል። የራሱ ድምጽ የሌለው ሰው ሁሌም ሌላው በሚያዘው መንገድ ይሄዳል እንጂ አዲስ መሪ ወይም አዲስ አሳቢ ሊሆን አይችልም።

የመጨረሻው ነጻነት ማጣት ነው። በጣም አደገኛው ጉዳት የነጻነት ማጣት ነው። ነጻነት የሚጀምረው በውጫዊ ለውጥ ሳይሆን በውስጣዊ የማሰብ ነጻነት ነው። ማንነቱን ያልገነባ ሰው በስሜት፣ በወግ፣ በፖለቲካ እና በዲጂታል አልጎሪዝም (ስልተ ቀመር) “እስር ቤት” ውስጥ ያለ እስረኛ ነው።

መቼ መቆጣት እንዳለበት፣ መቼ ማመን እንዳለበት ወይም መቼ መለወጥ እንዳለበት የሚወስኑት ሌሎች (ወይም ስርዓቶች) ስለሆኑ የራሱ የሆነ የህይወት አቅጣጫ አይኖረውም።

በአጠቃላይ የራስን ማንነት አለመገንባት ማለት የራስን ህይወት በውክልና ማስተዳደር ነው። ይህ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜትን በመግደል ሰውየውን የራሱ ታሪክ ተዋናይ ሳይሆን የሌሎች ታሪክ ተመልካች እንዲሆን ያደርገዋል።

ዛሬ ከአባቶቻችን ወግ በተጨማሪ አዲስ እና ይበልጥ ተንኮለኛ የአስተሳሰብ መጋረጃ ተጋርዶብናል። ይህም የዘመኑ የዲጂታል አልጎሪዝም ነው። የሶሻል ሚዲያ መድረኮች እንደምናስበው ነፃ ምርጫ እንዲኖረን አይፈቅዱልንም፤ ይልቁንም በተደጋጋሚ የምናያቸውን ይዘቶች በመሰብሰብ የራሳችንን “የማስተጋቢያ ክፍል”  ይፈጥሩልናል።

እነዚህ ስልተ-ቀመሮች የሰውን ባህሪ በመቅረጽ አመለካከታችንን ሳናውቀው ወደተፈለገው አቅጣጫ ይገፋሉ። በእርግጥ መርጠን የምንገዛው እኛ ነን? ወይስ አልጎሪዝሙ የተመረጡ ምርጫዎችን በፊታችን ደርድሮ የፈቀደልንን ብቻ እንድንመርጥ እያደረገን ነው?

ከአልጎሪዝም ባሻገር ፖለቲካ እና መዝናኛ የውስጣችንን ሀሳብ ይቆጣጠራሉ። ፈላስፋው ሂላሪ ላውሰን  ‘ክሎዠር’ በተሰኘው ጥናታቸው እንደሚያስረዱት ሰዎች ዓለምን የሚረዱት ባላቸው የተወሰኑ ማጣሪያዎች ነው። ለምሳሌ ዛሬ የምንመለከተው የፖለቲካ ትርክት የራስ ትንተና ውጤት ሳይሆን ከሚዲያና ከፖለቲካ ቡድኖች የተቀዱ ስሜቶች ናቸው።

አንድ ሰው ተቃዋሚውን “ጠላት” ብሎ ሲፈርጅ በእርግጥ የዚያን ሰው አቋም መርምሮ አይደለም፤ ያንን የጥላቻ ቃል ከሌላ ሰው የተዋሰው ነው።

በተመሳሳይ መልኩ የፊልም ኢንዱስትሪዎች እና የመዝናኛ ዓለም “ስኬት” የሚለውን ቃል በአንድ ጠባብ ፍቺ ውስጥ ቀርፀውታል። ይህንን ተከትሎም የሰው ልጅ ሕልውናን ትርጉም በቁሳዊነት ብቻ እንዲለካ ተደርጓል። እዚህ ጋር ነው የቪክቶር ፍራንክል ‘ማንስ ሰርች ፎር ሚኒንግ’ መጽሐፍ ትልቅ ሚና የሚጫወተው። ፍራንክል እንደሚሉት ሰው በውጫዊ ሁኔታዎች (ባህል፣ ፖለቲካ፣ ወይም ዘመናዊ ግፊት) ቢታጠርም የራሱን የሕይወት ዓላማ የመምረጥ እና በውስጡ የራሱን ድምጽ የመጠበቅ የመጨረሻ ነጻነት አለው።

ከዚህ የጥቅስ አስተሳሰብ ለመውጣት እንደ አርተር ሾፐንሃወር ያሉ አሳቢዎች እንደሚመክሩት “ከመውሰድ ይልቅ ማስተዋል” ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ የሚከተሉትን ሶስት መርሆች መከተል እንችላለን።

የስነ-ልቦና መነጠል: አንድ ነገር ስናስብ ወይም ስንቆጣ “ይህ ሀሳብ ከየት መጣ? ከእኔ ንቃተ-ህሊና ወይስ ማህበራዊ ሚዲያ ከሚመግበኝ መረጃ?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። በሃሳባችን እና በድርጊታችን መካከል ክፍተት ስንፈጥር የሌሎችን ድምጽ ከራሳችን ድምጽ መለየት እንጀምራለን።

የአልጎሪዝም ተፅዕኖን መቀነስ: ተፅእኖ ፈጣሪ ከሆኑ መተግበሪያዎች አልፎ አልፎ በመራቅ የራስን የማሰብ አቅም ማደስ ያስፈልጋል። መረጃን መምረጥ እንጂ መረጃ እንዲመርጠን መፍቀድ የለብንም።

የአባቶችን እሴት ማጣራት: እንደ ታማኝነት እና ለቤተሰብ ማሰብ ያሉ መልካም የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን ይዘን ግለሰብን የሚያደቁ ወጎችን ደፍሮ መተው ተገቢ ነው።

ኤመርሰን “የአባቶቻችን ጥቅሶች ነን” ሲል የእነርሱ  ታሪክ ቀጣይ እንድንሆን እንጂ የነርሱ ቅጂ እንድንሆን አይደለም። እኛ የዘመኑን አልጎሪዝም፣ የፖለቲካ ጩኸት እና የድሮ ወግን የሚያመዛዝን ገለልተኛ አእምሮ ሊኖረን ይገባል።

ሕይወት የራስህ ናት፤ የሌሎችን ድምጽ ማስተጋባት አቁመን የራሳችንን ታሪክ መጻፍ እንጀምር። በውስጣችን ያለው ድምጽ የራሳችን መሆኑን የምታረጋግጥበት ጊዜ አሁን ነው። የቆዩትን ግድግዳዎች እንመርምር። የሚጠቅሙትን እንያዝ። የማይጠቅሙትን ሰባብረን ወደፊት እንጓዝ። ነጻነት በውጫዊ ለውጥ ሳይሆን በውስጣዊ የማሰብ ነጻነት ይጀምራል።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሰኔ 29  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here