ውድ ልጆች፣ እንኳን ለክረምት ወራት ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ! ክረምት ከጓደኞቻችሁ ጋር የምትጫወቱበት፣ የምታርፉበት እና የምትደሰቱበት ልዩ ወቅት ቢሆንም ከከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ የሚመጡ እና እናንተን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮች ስላሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ።
በተለይ በሰፈራችሁ ወይም በትምህርት ቤታችሁ አቅራቢያ የሚገኙ የዝናብ ውኃ መውረጃ ቦዮች፣ ኩሬዎች፣ ወንዞች እና ክፍት የሆኑ የውኃ ጉድጓዶች በዚህ ወቅት በጣም አደገኛ ናቸው። የክረምት ጎርፍ ድንገት እና በከፍተኛ ፍጥነት ስለሚመጣ በቦዮችና በጅረቶች አካባቢ መጫወት ወይም ውኃውን ለመሻገር መሞከር በቀላሉ ጠራርጎ ሊወስድ ይችላል። የቆመ ውኃ ያለባቸው ኩሬዎች ደግሞ ጥልቀታቸው ስለማይታወቅ እና ከስራቸው ጭቃ ስለሚኖራቸው፣ ለመዋኘት ወይም ለመሻገር ስትሞክሩ አፍኖ የመያዝ እና የማጥለቅለቅ ከፍተኛ አደጋ አላቸው። ከዚህም በላይ የሚከማቸው ውሃ የበሽታ አምጪ ተህዋስያን መራቢያ በመሆን ለተለያዩ የጤና እክሎች ይዳርጋሉ።
ስለዚህ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅትም ሆነ ከዝናብ በኋላ ጨዋታችሁን ሙሉ በሙሉ ከነዚህ አደገኛ ቦታዎች ማራቅ አለባችሁ። በሚያንሸራትቱ የቦይ ዳርቻዎች ላይ ከመሮጥ መቆጠብ፣ የጎርፍ ውኃን በፍጹም አለመንካት እና ማንኛውንም አይነት ክፍት የውኃ አካል ስታዩ ራሳችሁን ማግለል ከከፋ አደጋ ይጠብቃችኋል። ሁልጊዜም ደህንነታችሁ የተጠበቀ እንዲሆን ከቤት ውጭ ስትጫወቱ ለአዋቂዎች ቅርብ መሆንና ማንኛውንም አጠራጣሪ ነገር ለወላጆቻችሁ መናገር ይኖርባችኋል።
በቤት ውስጥም ቢሆን የዝናብ ውኃ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ሊያረጥብ ስለሚችል ልጆች ማብሪያ እና ማጥፊያዎችን በእርጥብ እጅ መንካት የለባችሁም። ቅዝቃዜን ለመከላከል ማገዶ ወይም ከሰል ቤት ውስጥ በሚነድበት ጊዜ የጭስ መመረዝ እንዳይከሰት መስኮቶችን ክፍት በማድረግ በቂ አየር እንዲገባ ማድረግ ሌላው አስፈላጊ ጥንቃቄ ነው።
ዝናብ በሚበዛባቸው ቀናት ልጆች ከቤት እንዳይወጡ በቤት ውስጥ የሚሰሩ ስዕሎችን፣ ንባብን ወይም የፈጠራ ስራዎችን በማዘጋጀት ጊዜያቸውን በደስታ ማሳለፍ ይቻላል።
ተረት
ኤርሚያስ እና የሙዝ ልጣጩ
በአንድ ወቅት በአንድ ለምለም መንደር ውስጥ አልማዝ እና ኤርሚያስ የተባሉ እህትና ወንድም ይኖሩ ነበር። አልማዝ የተሰጣትን ከረሜላ በልታ ወረቀቱን ሁልጊዜ በቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ የምትጥል ንፁህ ልጅ ስትሆን፣ ኤርሚያስ ግን ሰነፍና ያገኘውን ቆሻሻ ሁሉ መሬት ላይ የሚጥል ነበር።
አንድ ቀን ኤርሚያስ ሙዝ በልቶ ልጣጩን በደጃፋቸው ላይ ወርውሮ ሲሄድ አልማዝ አየችውና “ኤርሚያስ፣ ቆሻሻ መሬት ላይ መጣል አካባቢን ያቆሽሻል፣ አደጋም ያመጣል፤ አንሳው” ስትል መከረችው። ኤርሚያስ ግን “አንድ የሙዝ ልጣጭ ምን ያመጣል!” ብሎ ሳቀባትና ጥሏት ሄደ።
ከሰዓት በኋላ ኤርሚያስ ከጓደኞቹ ጋር እየተሯሯጠ ወደ ቤት ሲመለስ፣ ጠዋት የጣለውን የሙዝ ልጣጭ ረስተውት ኖሮ በላዩ ላይ ረገጠው። ወዲያውኑ ድንገት ተንሸራቶ መሬት ላይ በጀርባው ወደቀና እግሩ በጣም ስለታመመ ማልቀስ ጀመረ። አልማዝ እየሮጠች መጥታ አነሳችውና ወደ ቤት አስገባችው።
ኤርሚያስ እግሩ አብጦ ለቀናት ቤት ውስጥ ለመቀመጥ ሲገደድ ጥፋቱ የራሱ መሆኑን ተረዳ፤ ከዚያ ቀን ጀምሮ “ከእንግዲህ መሬት ላይ ቆሻሻ በፍጹም አልጥልም” በማለት ለአልማዝ ቃል ገባ።
ምንጭ፡- የሕዝብ ተረት
ሞክሩ
- ቀን ቀን ይጠፋል፣ ማታ ማታ ይበራል። እሱ ምንድን ነው?
- ያለ ክንፍ ይበራል፣ ያለ እግር ይሄዳል። እሱ ምንድን ነው?
- በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) ላይ የሚገኙት ሶስቱ ቀለማት ምን ምን ናቸው?
- ኮከብ
- ደመና
- ቢጫ እና ቀይ
ነገር በምሳሌ
- ሰባሪው ባይኖር ጠጋኙ አይከብርም፦ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ አንዱ ለአንዱ መኖር አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነው።
- በአንድ እጅ አይጨበጨብም፦ ትልልቅ እና ስኬታማ ሥራዎችን ለመሥራት የሌሎች ሰዎች እገዛ እና ምክር ያስፈልጋል።
- እባብ ያየ በልጥ ደነገጠ፦ አንድ ጊዜ መጥፎ ነገር የገጠመው ሰው ሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


