ያልተነካው እምቅ ሀብት

0
214

ማዕድን ለአንድ ሀገር የገቢ ምንጭነት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን በማዳን ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ያገኘቻቸውን ጸጋዎች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመቀየር ረገድ ለዘመናት የነበራት ጉዞ አዝጋሚ ነበር።

በተለይም ከምድር በታች የተሸሸገው የማዕድን ሀብት የሀገሪቱን ብሎም የክልሎችን ኢኮኖሚ የመቀየር አቅም ቢኖረውም ለረጅም ዘመናት በዘርፉ ላይ የተደረገው ርብርብ አናሳ ሆኖ ቆይቷል። ይሁንና ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፉን የኢኮኖሚው ምሰሶ ለማድረግ በርካታ የመዋቅር፣ የፖሊሲ እና የኢንቨስትመንት ማሻሻያዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

እንደ ማዕድን ሚኒሥቴር መረጃ ባለፉት አምስት ዓመታት ዘርፉ ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሳቢ እንዲሆን የኮንትራት አሰጣጥ፣ የሮያሊቲ ክፍያ እና የታክስ ማበረታቻዎችን ያካተቱ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ማዕድናት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ እንዳይወጡ ለመከላከል ጥብቅ የድንበር እና የፋይናንስ ቁጥጥር ሥርዓቶችም ተዘርግተዋል።

የአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ በበኩሉ ማዕድናት ለሀገር ኢኮኖሚ ያላቸውን ከፍተኛ ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁሟል። መንግሥት ማዕድንን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ መፈረጁን ተከትሎ በአማራ ክልል ተስፋ ሰጪ መነቃቃት መታየት ጀምሯል።

ክልሉ በ25 ዓመቱ አሻጋሪ እና ዘላቂ የልማት ዕቅዱ ቁልፍ የልማት ዘርፎች ለይቶ ወደ ሥራ መግባቱም የሚታወስ ነው። ታዲያ ከነዚህ ዋና ዋና የልማት ዘርፎች ውስጥ የማዕድን ሀብት ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው።

በክልሉ በርካታ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ ማዕድናት እንዳሉ ተመላክቷል፡፡ የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ የክልሉን የማዕድን ሀብት ክምችት በጥናት በመለየት ልማት ላይ እንዲውል እያደረገም ይገኛል፡፡

በክልሉ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት 51  የማዕድን ዓይነቶች በጥናት ተለይተው የተገኙ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እነዚህን ዕምቅ የሀብት አይነቶች በኢንዱስትሪ፣ በግንባታ እና በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ በስፋት የማልማት እና ወደ ምርት የማስገባት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የቢሮው ጂኦሎጅስት እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናው አበበ ከበኵር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ዘርፉን በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት እና የክልሉን ዕምቅ ሀብት ወደ ጥቅም ለመቀየር እያደረገ ያለውን ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

አቶ ዝናው እንደሚያስረዱት ክልሉ አሁን ላይ ከባሕላዊ አሠራር ወጥቶ ዘርፉን በዘመናዊ መልክ በማደራጀት ላይ ይገኛል። የክልሉ የማዕድን ቢሮ በ2014 ዓ.ም ራሱን ችሎ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የጂኦ-ሳይንስ ጥናቶችን በማስፋፋት ላይ ይገኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደረገ ጥረትም የክልሉን 25 በመቶ የሥነ-ምድር ካርታ (Geological Map) መሥራት ተችሏል ነው ያሉት። ይህም ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት አስገንዝበዋል።

ለአብነት ያህል ለሲሚንቶ ምርት ወሳኝ የሆነው እና ከ16 በላይ አገልግሎቶች ያሉት ላይም ስቶን (Limestone) በሚሊዮን ቶን በሚቆጠር ክምችት በዓባይ ሸለቆ አካባቢ ይገኛል። በተጨማሪም ለብርጭቆ እና ጠርሙስ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆነው ሲሊካ ሳንድ፣ ለሴራሚክ የሚያገለግለው ቤንቶናይት በስፋት ይገኛሉ።

በኀይል ማዕድን ዘርፍም ቀድሞ ከሚታወቁት የጭልጋ እና የደብረ ብርሐን አካባቢዎች በተጨማሪ በዳውንት ከፍተኛ የካሎሪ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል መገኘቱ ለዘርፉ ትልቅ ብስራት ነው። በጌጣጌጥ ማዕድን በኩል ደግሞ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም ገበያ አንደኛ ደረጃን የያዘው እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ያለው የደላንታው ኦፓል (Opal) የክልሉ ልዩ መለያ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

የማዕድን ዘርፉ በአማራ ክልል እያመጣ ያለው የኢኮኖሚ መነቃቃት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ቀደም ሲል ማዕድናት ያለእሴት ጭማሪ ወደ ውጭ ይላኩ የነበረበትን አሠራር በመቀየር አሁን ላይ ማዕድናት እሴት ተጨምሮባቸው እንዲወጡ ጥብቅ መመሪያ ወጥቷል። ለዚህም ሲባል ማዕድናትን የሚጠርቡና ቅርፅ የሚያወጡ (Lapidary) ማሽኖች ተተክለው ባለሙያዎች ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል። ይህ የኢንዱስትሪ ትስስር ትልልቅ ፋብሪካዎችን ወደ ክልሉ እየሳበ ይገኛል።

በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በክልሉ መገንባቱ፣ የጂፕሰም እና የግራናይት ፋብሪካዎች በስፋት መከፈታቸው የዚሁ ማሳያ ናቸው። ከዚህም ባለፈ ክልሉ በወርቅ አቅርቦት ወደ ብሔራዊ ባንክ ምርት ማቅረብ ጀምሯል። የከበሩ ማዕድናት የገበያ ማዕከል በደሴ ከተማ መቋቋሙ ደግሞ ለኦፓል እና መሰል ማዕድናት ሕጋዊ የግብይት ስርዓት ፈጥሯል።

የማዕድን ዘርፍ ከማክሮ-ኢኮኖሚ ድጋፍ ባሻገር ለበርካታ  ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በበጀት ዓመቱ 45 ሺህ ሥራ አጥ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ለ36 ሺህ 739 ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፤ ከነዚህም መካከል 12 ሺህ 672 ሴቶች ናቸው። ይህም በገቢ ደረጃ ማዕድን የሀገር ውስጥ ምርትን ከመተካት ባለፈ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ያለውን ሚና ያጎላዋል።

አቶ ዝናው እንደሚሉት ቢሮው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በዘርፉ ሰፋፊ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ 94 የምርመራ እና 77 የምርት ፈቃዶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 171 ከፍተኛ የማዕድን ሥራ ፈቃድ መሰጠቱን ነው ያስረዱት።

የክልሉ ወጣቶች በዘርፉ ተደራጅተው የሥራ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ለሁለት ሺህ 106 በባህላዊ እና ለ309 በአነስተኛ ኮንስትራክሽን ማዕድን ለማምረት ለጠየቁ ማህበራት ፈቃድ ተሰጥቷል። እነዚህ አሃዞች የማዕድን ዘርፉ ለክልላችን ሕዝብ የኑሮ መሻሻል እያበረከተ ያለውን ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ያሳያሉ። በቀጣይም በተጨባጭ መረጃዎች እና ጥናቶች ላይ በመመርኮዝ የተረጋጋ እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ የልማት እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል እቅድ ተይዟል፡፡

ከማዕድን ልማት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ የሚነሳው የሕዝብ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው። ይህንን ለመፍታትም ቢሮው “የማህበረሰብ ልማት ፈንድ” (Community Development Fund) የተባለ አሠራር ዘርግቷል። ማንኛውም ባለሀብት ወደ ሥራ ሲገባ የሚያመነጨው ሀብት በቅድሚያ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ይሠራል። ይህም ማህበረሰቡ ፕሮጀክቶቹን የራሱ አድርጎ እንዲጠብቅ እና ከባለሀብቱ ጋር ተስማምቶ እንዲሠራ ትልቅ ድልድይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘርፉ ላይ ከሚታዩት ተግዳሮቶች ዋናው ከመሰረተ ልማት (መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ) ጋር የተያያዘ ነው። ይህንን ለመቅረፍ የማዕድን ቢሮው ከሌሎች የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት በመሥራት ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል። በተጨማሪም የማዕድን ናሙናዎች ለላቦራቶሪ ፍተሻ ወደ ውጭ ወይም ወደ አዲስ አበባ ሲላኩ የሚፈጠረውን የጊዜ መጓተት ለመፍታት ክልሉ የራሱን የጂኦ-ሳይንስ ላቦራቶሪ ለመገንባት የክልሉ መንግሥት በጀት መድቦ ወደ ሥራ ለመግባት ቃል መግባቱን ገልጸዋል።

“ማዕድን የሕዝብ እና የመንግሥት ሀብት ነው” ያሉት ኃላፊው ስለሆነም ያለሕጋዊ ፈቃድ ማዕድንን መፈለግ፣ ማውጣት (መቆፈር)፣ ማጓጓዝ እና መሸጥ በሕግ ያስቀጣል። ቢሮው ከፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-ወጥ የማዕድን ዝውውር (ኮንትሮባንድ) ላይ ጥብቅ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

በቅርቡ በተደረገ ቁጥጥርም ተሽከርካሪዎችን እና ማዕድናትን በመውረስ ከአምስት በላይ መዝገቦችን ወደ ፍርድ ቤት ልኮ ውሳኔ እንዲያገኙ አድርጓል። ይህም ሥርዓት አልበኝነትን ለማስቀረት እና ሕጋዊ አሠራርን ለማስፈን የተወሰደ ቁርጠኛ እርምጃ ነው። በአማራ ክልል የማዕድን ኢንቨስትመንት አሁንም ገና ያልተነካ ሀብት እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ ባሕላዊ፣ አነስተኛ፣ ከፍተኛ እና ልዩ ከፍተኛ (Large Scale) የሚባሉ የፈቃድ አሰጣጥ እርከኖች እንዳሉም ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ማዕድን ዘርፍ የጀመረው ጉዞ ከምድር ውስጥ የሚወጣውን ጠጠር ወደ ወርቅነት፣ ድንጋዩን ወደ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት የመቀየር ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው። ይህ ጅምር ተጠናክሮ ከቀጠለ ክልሉን አልፎ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የጀርባ አጥንት መሆኑ አይቀሬ ነው ብለዋል። ስለሆነም ሥራው በዕውቀት እና ሳይንስ ላይ የተመሠረተ ማዕድን የማምረት ሂደት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ሌላው ሕጋዊ ግብይት እና ሥርዓትን ተከትሎ መጠናከር እንዳለበት አመላክተዋል። በቀጣይም ማዕድናትን በጥሬው ከመላክ ወጥቶ ሙሉ በሙሉ እሴት ጨምሮ  በመቁረጥ እና በመቅረጽ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚሠራ ተመላክቷል።

አቶ ዝናው እንዳብራሩት”ማንኛውም ሕጋዊ አሠራርን ተከትሎ መሥራት የሚፈልግ ባለሀብት ወደ ክልሉ ቢመጣ ምቹ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ፣ በስፋት የሚገኝ አምራች የሰው ኀይል እና እጅግ ሰፊ  ዕምቅ የማዕድን ሀብት ይጠብቀዋል” በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በመሆኑም በዘርፉ ላይ ተሰማርቶ ራስንም ሆነ ሀገርን ለመጥቀም ለሚፈልጉ ባለሀብቶች፣ ግለሰቦች፣ ማህበራት እና ድርጅቶች የክልሉ መንግሥት መልካም አጋጣሚዎችን የፈጠረ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።

መረጃ

በአማራ ክልል የሚገኙት ማዕድናት በአምስት ዋና ዋና ዘርፎች የተከፈሉ ናቸው። እነሱም የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት፣ የግንባታ (የኮንስትራክሽን) ማዕድናት፣ የብረት እና ብረት ነክ ያልሆኑ ማዕድናት፣ የኀይል (Energy) ማዕድናት እና የከበሩ (የጌጣ ጌጥ) ማዕድናት ናቸው።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሰኔ 29  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here