የጎጃሙ አዳል ተሰማ

0
247

ደጃዝማች አዳል ተሰማ (በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የነበረችውን ኢትዮጵያን መልክ ካስያዙት እና ታሪኳን ከቀረጹት ጥቂት ስመ-ጥር መኳንንት መካከል ግንባር ቀደሙ ተጠቃሽ የታሪክ ሰው መሆናቸውን በታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የተጻፈው “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ” የተሰኘው መጽሐፍ ይገልጻል፡፡ የተወለዱት በ1840ዎቹ አጋማሽ አካባቢ በጎጃም ምድር ነው፡፡ የትውልድ ሐረጋቸው በቀጥታ የሚመዘዘው የጎጃም ገዥ ከነበሩት እና በዘመነ መሳፍንት ማጠናቀቂያ ላይ በኃይላቸው ገናና ከነበሩት ከደጃዝማች ተሰማ ጎሹ (የደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ልጅ) ነው። በአባታቸው ሞት ምክንያት ገና በልጅነታቸው ከፍተኛ የሥልጣን ፉክክር እና አደጋ የገጠማቸው ሲሆን በጎጃም የበላይነት ለመያዝ ይፋለሙ የነበሩት ተቀናቃኛቸው ራስ ደስታ ተድላ አሳስረቸው በግዞት አቆይተዋቸው ነበር። ሆኖም ግን አዳል ተሰማ በብልሃት ከእስር ቤት ካመለጡ በኋላ ለአባታቸው እና ለቤተሰባቸው ታማኝ የነበረውን የጎጃም ጦር በምስጢር በማስተባበር እና በማደራጀት ራስ ደስታ ተድላን በጦርነት ድል በማድረግ የጎጃምን አልጋ በቁጥጥራቸው ስር አዋሉ። በዚህ የድል ጉዟቸው መጀመሪያ ላይ በዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ዳግማዊ ዘመን የ”ደጃዝማች” ማዕረግ  አግኝተዋል፡፡ ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ወደ ሥልጣን ሲመጡም አዳል ተሰማ ለአዲሱ ንጉሠ ነገሥት ታማኝነታቸውን በተግባር በማሳየታቸው የ”ራስ” ማዕረግ ተሰጥቷቸው የጎጃም ሙሉ ገዥነታቸው ጸና።

የራስ አዳል ተሰማ የፖለቲካ እና የሥልጣን ማማ ላይ መውጣት ይበልጥ የተረጋገጠው ጥር 20 ቀን 1873 ዓ.ም ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ በደብረ ታቦር ከተማ ባደረጉት ታላቅ የደስታ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጎጃም እና የከፋ ንጉሥ አድርገው ቅብዐ ቅዱስ ሲቀቧቸው እና ስማቸውንም ወደ “ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት” ሲቀይሩት ነው። ይህ የንግሥና ማዕረግ ለአዳል ተሰማ ትልቅ ክብር እና ሥልጣን የሰጠ ቢሆንም ከጎረቤት የሸዋ ንጉሥ (በኋላ ንጉሠ ነገሥት) ምኒልክ ጋር ወደ ከረረ የሥልጣን እና የግዛት ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ሁለቱም ነገሥታት በሃብት የበለጸገውን እና የንግድ መሥመር መገናኛ የነበረውን የደቡብ-ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል (ከፋን) ለመቆጣጠር በነበራቸው ፍላጎት ምክንያት ሰኔ 30 ቀን 1874 ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ አካባቢ በሚገኘው በአምባቦ ሜዳ ላይ ከባድ የርስ በርስ ጦርነት አደረጉ።

ሰኔ 30 ቀን 1874 ዓ.ም የተደረገው የአምባቦ ጦርነት በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ላይ ትልቅ የኃይል ሚዛን ለውጥ ያመጣ ክስተት ነበር። ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጦርነቱን የጀመሩት ፈጣን እና አስደንጋጭ በሆነ የማጥቃት ስልት የሸዋውን ጦር ሳይዘጋጅ ለመምታት በማሰብ ነበር። የጎጃም ጦር በወቅቱ በጀግንነቱ እና በፈረሰኛ ኃይሉ የሚታወቅ በመሆኑ ንጉሡ ይህንን የፈረሰኛ ስልት በመጠቀም የሸዋን የጦር መስመር በቀጥታ ሰብሮ ለመግባት ሞክረዋል። ሆኖም የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ እና የጦር አዛዦቻቸው (በተለይም ራስ ጎበና ዳጬ) የተከተሉት የመከላከል እና የከበበ ማጥቃት ስልት የጎጃምን ጦር በበላይነት ሊቆጣጠረው ችሏል። የሸዋ ጦር በወቅቱ ከፈረንሳይና ከጣሊያን የገዛቸው ዘመናዊ ጠመንጃዎች የነበሩት ሲሆን የጎጃም ጦር ግን በአብዛኛው ባሕላዊ መሣሪያዎችን ይዞ ነበር።

በዚህ እጅግ ደም አፋሳሽ በነበረው የአምባቦ ጦርነት ላይ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጦር በሸዋው ጦር የጦር መሣሪያ የበላይነት እና ስትራቴጂ ምክንያት ተሸነፈ፤ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት እራሳቸው ቆስለው በምኒልክ ጦር ተማረኩ። ሆኖም ግን የንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እና ጠንካራ ትእዛዝ በመምጣቱ ሁለቱ መሪዎች እንዲታረቁ እና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም ምንም ሳይነኩ ክብር እና ግዛታቸው ተመልሶላቸው ወደ ጎጃም እንዲመለሱ ተደረገ።

ለንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የንግሥና ዘመን ትልቅ ፈተና ሆኖ ያለፈው ሌላው ክስተት ከሱዳን ወገን የተነሳው የደርቡሾች (ማህዲስት) አክራሪ ወረራ ነበር። የደርቡሽ ጦር ድንበር ተሻግሮ የጎጃምን እና የጎንደርን ሕዝብ ሲያሰቃይ እና አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥል ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ጦራቸውን ይዘው ገጠሙ፤ እ.አ.አ በ1887 በተደረገው የሳር ውኃ ጦርነት ላይ በደርቡሾች የሰው ኃይል ብዛት እና የጭካኔ ወረራ ምክንያት የጎጃም ጦር ከፍተኛ ኪሳራ ደረሰበት፤ ከተማቸው ደብረ ማርቆስም በከፊል ተቃጠለች። ይህ መራር ሽንፈት ለዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ወደ መተማ መዝመት እና እዚያው መውደቅ አንዱ ትልቅ ምክንያት ሆኗል። ሆኖም ግን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በሽንፈት ተስፋ ሳይቆርጡ ጦራቸውን በድጋሚ በማደራጀት እና ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ዐፄ ምኒልክ መላውን የኢትዮጵያ ሥልጣን በያዙ ጊዜ አዲሱን ንጉሠ ነገሥት በሙሉ ልብ በመደገፍ ታማኝነታቸውን አሳዩ።

ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በታሪክ ማኅደር ውስጥ ስማቸው በወርቅ ቀለም እንዲጻፍ ያደረገው ትልቁ ተግባራቸው እ.አ.አ በ1896 የተካሄደው የታሪካዊው የዓድዋ ጦርነት ላይ ያሳዩት ወደር የሌለው ጀግንነት እና አርበኝነት ነው። ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ እና ጌታቸው መታፈሪያ  በዓድዋ ጦርነት ላይ ያተኮረው (The Battle of Adwa: reflections on Ethiopia’s historic victory Against European colonialism) ጥናታቸው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የመሩትን የጎጃም ጦር ስትራቴጂካዊ አሰላለፍ እና የጦር አቅም በዝርዝር ይተነትናል

የጣሊያን ወራሪ ጦር ሀገሪቱን ለመቀራመት የመጣ መሆኑን ሲረዱ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የቀድሞ የርስ በርስ ቂምና ቁርሾን ወደ ጎን በመተው በዐፄ ምኒልክ እና በጋራ የሀገር ጥሪ ሥር በመሰለፍ እጅግ ግዙፍ እና በጦርነት የተፈተነ የጎጃም እግረኛ እና ፈረሰኛ ጦር ይዘው ወደ ዓድዋ ዘመቱ። በማጥቃት ስትራቴጂው ላይ የጦር ግንባር መሪ ከነበሩት እንደ ራስ መኮንን እና ራስ መንገሻ ጋር በመሆን የቀኝ ክንፍ የጦር አዝማች በመሆን የጣሊያንን ወታደራዊ ምሽግ ሰብረው በመግባት እና እስከ መጨረሻው በፅናት በመዋጋት ለዓድዋ ታላቅ ድል የላቀ እና የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በአብዛኛው በታማኝነት እና በወታደራዊ ጥምረት ላይ የተመሠረተ ነበር። ዐፄ ዮሐንስ የንጉሠ ነገሥትነቱን መንበር በያዙበት ወቅት አዳል ተሰማ በጎጃም ያለውን ተቀናቃኛቸውን ራስ ደስታን ድል አድርገው ለዮሐንስ ታማኝነታቸውን በመግለጻቸው መጀመሪያ የ”ራስ” ማዕረግ ተሰጣቸው።

የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ይበልጥ የጠነከረው ጥር 20 ቀን 1873 ዓ.ም ዐፄ ዮሐንስ ራስ አዳልን “የጎጃም እና የከፋ ንጉሥ” አድርገው በደብረ ታቦር ከተማ ሲቀቧቸውና “ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት” የሚለውን የዙፋን ስም ሲሰጧቸው ነው። ይህ ዐፄ ዮሐንስ የወሰዱት ስልታዊ እርምጃ በወቅቱ እያደገ የመጣውን የሸዋውን ንጉሥ ምኒልክን ኃይል ለማመጣጠን እና ለመግታት የታለመ ነበር።

ዐፄ ዮሐንስ በመተማ ጦርነት ላይ ከወደቁ በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የዐፄ ምኒልክን የንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን በሙሉ ልብ ከተቀበሉ የመጀመሪያዎቹ የየአካባቢው መሪዎች አንዱ ነበሩ። ይህ የፖለቲካ ብልሃት እና ታማኝነት በዐፄ ምኒልክ ዘንድ ትልቅ ቦታ የተሰጠው ነበር፡፡

እኚህ ታላቅ መሪ ከብዙ የሥልጣን፣ የጦርነት እና የልማት ዘመናት በኋላ በጥር ወር 1901 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ አስከሬናቸውም በደብረ ማርቆስ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በታላቅ ክብር አርፏል። ከእሳቸው ሕልፈት በኋላም ታዋቂውና ስመ-ጥሩው ልጃቸው ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት (ራስ ኃይሉ በሉ) የጎጃም ገዥ በመሆን የአባታቸውን ሥልጣን ተረክቧል።

ሳምንቱ በታሪክ

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሻር

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአፍሪካ ሀገራትን ነፃነት፣ አንድነት እና ትብብር ለማጠናከር የተመሰረተ ታሪካዊ አህጉራዊ ተቋም ነው። ይህ ታላቅ ድርጅት የተመሰረተው ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን በወቅቱ ነፃነታቸውን አግኝተው የነበሩ የ32 ነፃ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የድርጅቱን ቻርተር በአንድነት ፈርመዋል። የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ በሐሳብ እና በቡድን ተከፋፍለው የነበሩትን የአፍሪካ መሪዎች በማስማማት እና አዲስ አበባ ላይ ሰብስበው ድርጅቱ እንዲመሰረት በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ ታሪካዊ ባለውለታ ናቸው። በዚህም ምክንያት ከምስረታው ጀምሮ የድርጅቱ ቋሚ ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ እንድትሆን በሙሉ ድምፅ ተወስኗል።

የድርጅቱ ዋና ዓላማዎች ገና በቅኝ ግዛትና በዘረኝነት ሥርዓት ሥር የነበሩትን የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት ትግል በገንዘብ፣ በወታደራዊ ሥልጠና እና በዲፕሎማሲ መደገፍ፣ በአባል ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማሳደግ እንዲሁም የሀገራቱን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ማስጠበቅ ነበሩ። ድርጅቱ ለ40 ዓመታት ያህል አህጉሪቱን ካገለገለ በኋላ አፍሪካ ከነፃነት ትግል ወጥታ ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት እና ልማት መሸጋገር ስላለባት ሐምሌ 4 ቀን 1994 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ በተደረገው ጉባኤ በይፋ ተሽሯል። በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምትክም ይበልጥ ጠንካራ መዋቅር እና ሰፊ የልማት ዓላማ ያለው የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት በዚሁ ዕለት ተተክቶ ሥራውን ጀምሯል።

ምንጭ፡- በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ መዛግብት።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here