የክረምት የጤና ዕክሎች

0
161

በሀገራችን  የክረምት ወቅት ሞቃቱ የአየር ፀባይ በቀዝቃዛ የሚተካበት፣  የተስፋ፣ የልምላሜ፣  የአዲስ  ዓመት  ማብሰሪያ …  ነው፡፡

በሌላው ጎኑ ደግሞ የክረምቱን መግባት ተከትሎና እስኪወጣ ባሉት ስድስት ወራት  የተለያዩ የጤና እክሎች የሚከሰቱበት እንደ ሆነ ነው የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሳወቀው፡፡ ችግሩን ለመከላከልም ክልሎች የየራሳቸውን ቅድመ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ቀድሞ ለመከላከል  በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሊከሰቱ ይችላሉ ያላቸውን የሕብረተሰብ ጤና ችግሮች ለይቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

በተቋሙ  የመጀመሪያው በሕብረተሰቡ ዘንድ የጤና እክል ሊፈጥር ይችላል ተብሎ የታሰበው ወባ ነው፡፡ ወባ ዝናቡ ወጣ ገባ ከማለቱ ጋር ተያይዞ ፀሐያማ ሁኔታዎች በመኖራቸው እና ከመስከረም በኋላ የበሽታው ስርጭት ሊኖር ስለሚችል ቅድሚያ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ነው የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ያስታወቁት፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ የወባ ትንኝ ትገኝበታለች ተብሎ ከሚታሰበው ከፍታ በላይ መራባቷ፣ ማኅበረሰቡ ወባን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ማነስ እና በግጭቶች ምክንያት የሚደረገው የቁጥጥር መስተጓጎል ወባ በተደጋጋሚ የክልሉ የጤና ሥጋት ሊሆን ችሏል፡፡ ባለፉት 12 ወራትም አንድ  ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች በወባ መያዛቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ወባ በፕላዝሞዲየም ጥገኛ ተውሳኮች የሚመጣ ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ ሲሆን ጥገኛ ተውሳኩን በተሸከሙ ሴት አኖፌልስ ትንኞች ንክሻ ወደ ሰው ይተላለፋል፡፡ የወባ ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ የሚጀምሩት በተበከለ ትንኝ ከተነከሱ ከ10 እስከ 15 ቀናት ውስጥ ነው፡፡

የተለመዱት የወባ የመጀመሪያ ምልክቶችም ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና ብርድ ብርድ ማለት ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ምልክቶች የታየበት ሰው በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ግድ ይለዋል፡፡

አንዳንድ የወባ ዓይነቶች ከባድ ሕመም እና ሞት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ጨቅላ ሕፃናት፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች፣ ነፍሰጡሮች፣ ተጓዦች እና ኤችአይቪ ኤድስ ያለባቸው ሰዎች ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በወባ እንዳይያዙ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

አቶ በላይ  ወባን ለመከላከል ሁልጊዜ አርብ ጠዋት እድሜው ከሰባት  ዓመት ጀምሮ የሚገኙ ልጆችን ጨምሮ ማንኛውም ሕብረተሰብ በየአካባቢው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና ኬላዎች ካሉ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወባን የመከላከል ሥራዎችን ቢያንስ ለአንድ ሰዓት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዚህም የወባ መራቢያ ቦታዎችን የማጽዳት፣ ውኃ ያቆሮ ቦታዎችን ማፋሰስ፣ አጎበር በአግባቡ መጠቀም፣ በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ ሳያቆራርጡ መውሰድ፣ የጸረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ማካሄድ ወባን መከላከል እንደሚያስቸል ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ በክልሉ  የወባ መከላከል ሥራን ለማጠናከር  ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ የመኝታ አጎበር ለሕብረተሰቡ መከፋፈሉንና በ17 ወረዳዎችም የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በምዕራብ እና በሰሜን ጎጃም የሚገኙ 20 ወረዳዎች የክልሉን 50 በመቶ የወባ ስርጭት እንደያዙ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ በእነዚህ ወረዳዎች የሚሠራ የመከላከል ሥራም የክልሉን የወባ በሽታ በዕጅጉ እንደሚቀንስ ነው አጽንኦት የሠጡት፡፡

በክረምቱ ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከለያቸው በሽታዎች መካከልም የኮሌራ ወረርሽኝ ሌላው  ነው፡፡ ቫይብሪዮ ኮሌራ የተባለው ባክቴሪያም የኮሌራ ዋነኛ መንስኤ ነው፡፡ በአብዛኛው በተበከለ ምግብ እና ውኃ ይተላለፋል፡፡ ኮሌራ ከፍተኛ ውኃማ ተቅማጥን የሚያስከትል ተላላፊ በሽታ ሲሆን  በፍጥነት  ሕክምና ካላገኙ የሰውነት ፈሳሽን በመጨረስ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡

የኮሌራ ባክቴሪያ ብዙ ጊዜ በኮሌራ ጀርሞች በተያዙ ሰዎች አይነ ምድር በተበከለ ውኃ ወይም  በተበከሉ ምግቦች ውስጥ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ፣ ከመጻዳጃ መልስ እጅን በሳሙና እና በንጹህ ውኃ መታጠብ በበሽታው ላለመያዝ ይረዳል፡፡

ሌላው ከክረምቱ ጋር በተያያዘ የሕብረተሰቡ የጤና ስጋት ሊሆን ይችላል የተባለው የኩፍኝ ወረርሽኝ ነው፡፡ ኩፍኝ ተላላፊ በሽታ ነው፤  ሩቤላ የሚባል ቫይረስም ኩፍኝን ያስከትላል፡፡ በሽታው  በዋነኛነት የመተንፈሻ አካላትን ይጎዳል፡፡ በበሽታው የተያዘ ሰው በሚያስነጥስበት ወይም በሚያስልበት ጊዜም በሚወጡ ጠብታዎች ይተላለፋል፡፡ ቫይረሱ በአየር ውስጥ ወይም በመሬት ላይ ለብዙ ሰዓታት ንቁ ሆኖ ሊቆይ ይችላል፡፡ እቃዎችን፣ መጠጦችን መጋራት ወይም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ መሆን የበሽታውን የመተላለፍ አጋጣሚ ይጨምራል፡፡ ኩፍኝን መከላከል የሚቻለውም  ወቅታዊ ክትባት እና ወረርሽኙ በሚከሰትበት ጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እንደሆነ ዳይሬክተሩ መክረዋል፡፡

አቶ በላይ  እንዳስረዱት በተፈናቃይ ጊዚያዊ መጠለያዎች፣ በጸበል ቦታዎች እና ሌሎች ተጋላጭ ቦታዎች ላይም ውኃ ወለድ በሽታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የተለዩ ቦታዎች ላይ ሥራ ለመሥራት ታቅዷል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ከፍተኛ በርካታ ሰዎች በአንድ ላይ የሚኖሩበት አግባባ በመኖሩ ወረርሽኝ ሊከሰት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በጊዚያዊ መጠለያዎች ላይ በቂ ንጹህ ውኃ እና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ በነዚህ በመጠለያ ጣቢያዎች ወረርሽኝ እንዳይከሰት የቅኝት ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ከዛ አካባቢ የተነሳ ወረርሽኝ ወደ ሌላ  ሊዛመት ይችላልና፡፡

ሌላው በአፍሪካ በሁለት ሀገራት( በዴሞክራሲ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ) የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝን በተመለከተም ዳይሬክተሩ መረጃ ሰጥተዋል፡፡ ኢቦላ በኢትዮጵያ ባይከሰትም  አስፈላጊው የጥንቃቄ እና የመከላከል ተግባራት በአየር መንገድ መውጫ እና መግቢያ ቦታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡

ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ከመስከረም እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ የእብድ ውሻ በሽታ እና ከጎርፍ መጥለቅለቅ ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ሰፊ እቅድ መያዙን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ በዚህም  በክልሉ ውሻን የሚያሳብድ በሽታን በዘላቂነት ለመፍታት ባለቤት የሌላቸውን ውሾች መቆጣጠር የሚያስችል አዲስ ደንብ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለክልሉ ምክርቤት መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ ልብ ሊደረግ የሚገባው ጉዳይ  ውሻን የሚያሳብድ በሽታ የተነከሰ ሰው ምልክቶቹ ከታዩበት መዳን አለመቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም የውሻ ንክሻ ሲያጋጥም በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ክትባት መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሌላው ከክረምት መዘግየቱ ጋር ተያይዞ በተወሰኑ ወረዳዎች የምግብ እጥረት ቢከሰትም ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ፣ ለአረጋዊያን እና ለአካል  የአልሚ ምግቦች የሚደርሱበት ሁኔታ እንደሚኖር ነው ያሳወቁት፡፡ ሆኖም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ መጠናከር እንዳለበት እና በምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎች  ከተገኙም በፍጥነት ሪፖርት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

መረጃ

*በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ሚሊዮን ነጥብ ሦስት  እስከ አራት ሚሊዮን የሚደርሱ  ሰዎች  በኮሌራ  ይጠቃሉ፡፡

በየዓመቱም ከ21ሺህ እስከ 143ሺህ የሚገመቱ  ሰዎችን  ለሞት ይዳርጋል፡፡

*ከውኃ ወለድ በሽታዎች መካከል 88 በመቶው  በንፅህና አጠባበቅ፣ በቂ ያልሆነ የንፅህና መጠበቂያ ተቋማት ባለመኖራቸው እና ንፁህ ባልሆኑ የውኃ አቅርቦቶች ምክንያት ሊከሰቱ እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል፡፡

*የውኃ ወለድ በሽታዎች በብዛት ወደ ሚገኙባቸው ክልሎች ሲጓዙ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡ ለመጠጥ እና ለምግብ ማብሰያ የሚውለውን ውኃ አፍልቶ መጠቀም እና በአግባቡ የታከመ ውኃን መጠቀም ከውኃ ወለድ በሽታዎች ይታደጋል፡፡

*የወባ ትንኝ ንክሻን በማስወገድ፣ መድኃኒቶችን በአግባቡ በመውሰድ እና በሕብረተሰቡ ያለሰለሰ የመከላከል እና የቁጥጥር፣ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም  ወባን በከፍተኛ  ሁኔታ መከላከል ይቻላል፡፡

ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here