ኦል ፔጄታ ጥብቅ ክልል

0
9

ኦልፔጄታ በኬንያ ላይኪፒያ ግዛት የሚገኝ የዱር አራዊት ጥብቅ ክልል ነው፡፡ የቀጣናው ስፋት 90 ሺህ ሄክታር ተለክቷል፡፡ ቀጣናው ከ1940ዎቹ እስከ 80ዎቹ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሰፋሪዎች የከብት ርባታ (ራንች) ቦታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በከብት እና በእርሻ ቦታው ዙሪያ የዱር እንስሳትም በመጠለያነት ይጋሩ ነበር፡፡

በ1988 እ.አ.አ የከብት ርባታው ቀጣና ከዱር አራዊት የሚደርሰው ጫና በመበርታቱ ወደ ባለብዙ ሀገር በቀል የግል ኩባንያ ወይም ድርጅትነት ተቀይሯል፡፡ በመቀየሩም ከከብት ርባታው በበለጠ ከዱር እንስሳት ጥበቃ እና እንስሳቱን ከሚጐበኙ ቱሪስቶች የሚገኘው ገቢ በልጦ መገኘቱ ነው በጥብቅ ክልልነት ለመዝለቁ በምክንያትነት የተጠቀሰው፡፡

ኦልፔጄታን በ2004 እ.አ.አ “ፉና እና ፍሎራ ኢንተርናሽናል” የተሰኘ እንግሊዝ የሚገኝ ድርጅት ቀጣናውን ገዝቶ በባለቤትነት መቆጣጠር ችሏል፡፡ ድርጅቱም ከቱሪዝም እና ከበጐ አድራጐት ተቋማት የሚያገኘውን ትርፍ ለቀጣናው ልማት ፈሰስ እንደሚያደርግ ነው ድረገፆች ያስነበቡት፡፡

በባለቤትነት የተረከበው ድርጅት በበጐ ፈቃደኞች ቦርድ በመመራት የጥበቃ እና የማህበረሰብ  ልማት  የማከናወን  ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡  የድርጅቱ ገቢም ሙሉ በሙሉ ለቀጣናው ጥበቃ፣ ለኗሪዎች መሰረተ ልማት ግንባታ ብቻ ነው የሚውለው፡፡ በጥብቅ ቀጣናው ከዱር እንስሳት በስድስት መንጋ የታቀፉ 72 ኦናብስት፣ 30 አቦሽማኔ፣ 20 ነብሮች፣ ቀበሮ፣ ጅብ፣ ተኩላ /የዱር ውሻ/፣ “ዋይልድ ቢስት” መገኘታቸው ተረጋግጧል፡፡

ከእፅዋት – ቀጣናው ሳር ለበስ ሜዳ፣ ገላጣ ደን እና ረግረጋማ ስነምህዳርን  የያዘ ነው፡፡

ለጉብኝት  ተመራጩ  ከሰኔ  እስከ  ጥቅምት እንዲሁም  ጥር  እና  ታህሳስ  ወራት    ናቸው፡፡

ጥብቅ ክልሉ በሚከተለው የጥበቃ ስልት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና ሽልማት ማግኘቱን በማጠቃለያነት ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት አልፔጄታ ኮንሰርቫንሲ ኬንያ፣ ኽልፒንግ ሪሂኖስ ዶት ኦርግ እና ብሪሊያንት አፍሪካን ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር  የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here