ግብር ምን ማለት ነው?

0
66

ግብር በመዝገበ ቃላት ፍችው –  “መንግሥት በሕግና ደንብ ላይ ተመስርቶ ከሕዝብና ከድርጅቶች ገንዘብ የሚያገኝበት መሳሪያ ነው፡፡ ዜጎች በመነገድ፣ ቤትና ንብረት በማከራየት ፣ዕውቀታቸውን በመሸጥ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ከሚያገኙት ገቢ ላይ በሕግ በተቀመጠው መሰረት የመንግስትን ድርሻ (ግብር) ይከፍላሉ፡፡ስለዚህ ግብር ህብረተሰቡ ወይም ግብር ከፋዮች ለመንግሥት በግዴታ ክፍያ የሚፈጽሙበት መንገድ /ሥርአት/ ሲሆን በአንጻሩ ግን መንግሥት ለሕብረተሰቡ በለውጡ ወይም በምትኩ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ልዩነት ሳይፈጥር ለሚያቀርበው አገልግሎትና መሰረተ ልማቶች የሚያውለው ገንዘብ ነው” ይላል፡፡

የግብር/ታክስ አስፈላጊነት /ጥቅም

ግብር ከእያንዳንዱ ግለሰብ የየእለት እንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሲሆን ጠቀሜታዎቹም አያሌና ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ግብር ለኢኮኖሚ ልማት፣ ለማህበራዊ አገልግሎት መስፋፋት፣ ለባህል እድገት፣ ለሀገር ደህንነት፣ ለፍትሕና መልካም አስተዳደር መስፈን፣ ለአከባቢ ጥበቃ፣ ሀገርን ከጠላት ለመከላከል፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ሰርተውና ውለው ለመግባት፣ ደህንነታቸውና ሰላማቸውን ለመጠበቅ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣ የኀይል አቅርቦትን ለመስፋፋት ፣ኢኮኖሚን ለማነቃቃት፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ፣ ልማትን ለማፋጠን፣ የሕብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ኢኮኖሚን ለማረጋጋት፣ በዜጎች መካከል ፍትሓዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ እና የመሳሰሉት ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ገንዘብ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ግብር /ታክስ/ ዋናው የመንግሥት የገንዘብ ምንጭ በመሆን የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ልማት እና እድገት የጀርባ አጥንት ነው” በማለት የዘርፉ ባለሞያዎች የሚገልጹት፡፡

የግብር /ታክስ/ አይነቶች

የግብር ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ቀጥተኛ ታክስ እና ቀጥተኛ ያለሆነ ታክሶች በመባል ይታወቃሉ፡፡

ቀጥተኛ ታክስ

ቀጥተኛ ታክስ የሚባለው ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት በየትኛውም የሥራ መስክ ሲሰማራ ከሚያገኘው ገቢ ላይ የሚከፍለው የግብር /ታክስ/ አይነት ነው፡፡ በዚህ ስር የሚካተቱ የግብር ወይም ታክስ አይነቶችም በገቢ ግብር አዋጁ አንቀጽ 8 ላይ እንደሰፈረው ከቅጥር፣ ከኪራይ፣ ከንግድ እና ሌሎች ገቢዎች የሚገኘውን ነው፡፡  ይህ ማለትም የፈጠራ መብትን በማከራየት የሚገኝ ገቢ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚሰጥ አገልግሎት የሚገኝ ገቢ፣ በእድል ሙከራ ውድድር አሸናፊነት የሚገኝ ገቢ፣ ቋሚ ባልሆነ ሁኔታ ከንብረት ኪራይ ከሚገኝ ገቢ፣ ከወለድ ገቢ፣ ከንግድ ሥራ ጋር ካልተያያዘ የካፒታል ዋጋ እድገት የሚገኝ ገቢ ነው፡፡

ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች

ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ደግሞ ታክሱን የሚከፍሉት በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሳይሆኑ በተዘዋዋሪ የምርቱ ወይም የአገልግሎት ተጠቃሚዎች በመሆናቸው ቀጥተኛ ከሆነው ታክስ ይለያሉ፡፡ እነዚህ የታክስ ዓይነቶችም የተርን ኦቨር ታክስ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የቴምብር ቀረጥ ናቸው፡፡

ተርን ኦቨር ታክስ

ተርን ኦቨር ታክስ በአዋጅ ቁጥር 308/95 መሰረት በተጨማሪ እሴት ያልተመዘገቡ ሰዎች በሀገር ውስጥ በሚሸጧቸው ምርቶችና በሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች ላይ ተሰልቶ የሚከፍሉት የታክስ አይነት ነው፡፡ አከፋፈሉም በማናቸውም በሀገር ውስጥ በሚሸጡ እቃዎች ላይ ሁለት በመቶ ፣ የሥራ ተቋራጮች፣ የእህል ወፍጮ ቤቶች፣ የትራክተርና ኮምባይን ሃርቨስተሮች አገልግሎት ሁለት በመቶ (2ከመቶ)እና ሌሎች አገልግሎቶች አስር በመቶ (10ከመቶ) ሲሆን ታክሱ የሚሰላው በጠቅላላ የሽያጩ ወይም የአገልግሎቱ ዋጋ ላይ ነው፡፡

ኤክሳይዝ ታክስ

ኤክሳይዝ ታክስ ደግሞ የቅንጦት እንዲሁም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ እቃዎች እና የኀብረተሰቡን ጤና በሚጎዱና የማህበራዊ ችግር በሚያስከትሉ እቃዎች ላይ አጠቃቀሙን ለመቀነስ ሲባል የሚጣል የታክስ አይነት ነው፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ ሀገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የተወሰኑ እቃዎች ላይ የሚጣል ሲሆን የክፍያ መጠኑም ከአስር እስከ መቶ ከመቶ (ከ10 አስከ 100) የሚደርስ ነው፡፡

ተጨማሪ እሴት ታክስ

ተጨማሪ እሴት ታክስ ቀደም ሲል ይጣል የነበረውን የሽያጭ ታክስ በመተካት በሥራ ላይ የዋለ የታክስ አይነት ሲሆን የሚጣለውም በማንኛውም በተመዘገቡ ሰዎች ታክስ በሚከፈልበት ግብይት ነፃ ከተደረጉት በስተቀር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ነው፡፡ በተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈለው ከላይ በተገለጹት ምርትና አገልግሎቶች አጠቃላይ የሽያጭ ዋጋ ላይ አስራ አምስት ከመቶ በማስላት ነው፡፡

በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ አንቀጽ 16 መሰረት ታክስ የሚከፈልበት የንግድ ሥራ የሚያንቀሳቅስ ሆኖ በአንድ ዓመት ውስጥ ያከናወነው ግብይት ከብር 500,000.00 /ከአምስት መቶ ሺህ ብር/ በላይ ከሆነ መመዝገብ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቢያንስ ከሰባ አምስት ከመቶ በላይ ዕቃ የማቅረብና አገልግሎት የመስጠት ሥራ  ለተመዘገቡ ሰዎች የሆነ ነው፡፡ ከላይ በተገለፀው መሰረት አገልግሎት የሚሠጡ ለመመዝገብ የማይገደድ ሰው በፍላጎቱ መመዝገብ እንደሚችልም እንደዚሁ በአዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡

የቴምብር ቀረጥ

የቴምብር ቀረጥ የሚከፈለው ሰነዶችና ውሎች ሕጋዊ ማስረጃ ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ ሲሆን ይሄውም በመመስረቻና መተዳደሪያ ጽሑፎች፣ የግልግል ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ወይም በሚሰጥበት ጊዜ፣ በውል ወይም በስምምነት ሰነዶች ላይ፣ በማረጋገጫ ሰነዶች፣ በመያዣ ሰነዶችና በንብረት ባለቤትነት ስም ማስመዝገቢያ ሰነዶች ላይ ተግባሩ ከመፈፀሙ በፊት ወይም በሚፈፀምበት ወቅት ክፍያው መፈፀም እንዳለበት የቴምብር ቀረጥ አዋጅ 110/1990 ዓ.ም ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ግብር አለመክፈል ያለው ተጠያቂነት

እንደ ፌዴራል አቃቢ ሕግ መረጃ ግብር መክፈል ግዴታ ከሆነ ግብርን በተገቢው ጊዜ አለመክፈል በሕጉ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116 እና ቀጥሎ ባሉት ድንጋጌዎች መሰረት ግብርን አለመክፈል፣ ማጭበርበር፣ ግብር መሰወር፣ ቫት ማጭበርበር እና በጠቅላላው ከታክስ ጋር ተያይዘው ለሚፈጸሙ ወንጀሎች በእስር እና እንደየወንጀሉ ክብደት በብርም የሚያስቀጡ ናቸው፡፡

በኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንቀጽ 39 እና ቀጥሎ ባሉት ድንጋጌዎች መሰረት ኤክሳይስ ታክስን አለመክፈል ከሦስት ዓመት ጽኑ እስራት ጀምሮ በተለያየ ደረጃ በእስር እና በገንዘብ እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡

በሁሉም የግብር አይነቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከወንጀል ተጠያቂነት በተጨማሪ አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ያስከትላሉ፡፡ እሱም በገንዘብ፣ ከሥራው ማገድ እና የመሳሰሉትን አስተዳደራዊ ርምጃዎች ያስከትላል፡፡ ለዚህም ግብር መክፈል ለሀገር እድገት እና ለዜጎች ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች መረጋገጥ ካለው ፋይዳ አንጻር አስፈላጊ ከመሆኑም ባለፈ በአንድ ሉአላዊ ሀገር ግብርን ለመንግሥት መክፈል ግዴታ ነው፡፡  ይሄን አውቆ በወቀቱ አለመክፈል ግን  የወንጀል እና አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ያስከትላል፡፡

የሕግ አንቀፅ

ግብርን በአግባቡ ባለመክፈል የሚመጡ ተጠያቂነቶች

  • የገንዘብ ቅጣትና ወለድ፡-

ግብር በወቅቱ ባለመክፈል፣ የተሰወረ ግብር ሲገኝ ወይም የተጭበረበረ ደረሰኝ ሲያዝ ከመደበኛ ግብሩ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የወለድ እና የቅጣት ክፍያ ይወሰናል።

  • የንግድ ፈቃድ መሰረዝ /እገዳ/ –

የንግድ ሥራ ለመሥራት የቀረበውን የግብር ግዴታ የመወጣት ቅድመ ሁኔታ ስለሆነ፤ ግብር መክፈል አቁመው የተገኙ ድርጅቶች ፈቃዳቸው ይታገዳል ወይም ይሰረዛል።

  • የወንጀል ክስ-

ሆን ብሎ ግብር በመደበቅ፣ ሀሰተኛ መረጃ በማቅረብ ወይም ግብርን በአግባቡ ባለመክፈል የሚታወቁ አካላት በወንጀል ሕግ እስከ እስራት የሚያደርስ ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል።

  • የባንክ ሂሳብ እና ንብረት መታገድ- ግብር ከፋዩ በተደጋጋሚ ሲጠራም ግብር ካልከፈለ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ የግብር ከፋዩን የባንክ አካውንት እና ንብረቶች የማገድ ስልጣን አላቸው።
  • የአገልግሎት መቋረጥ-

እንደ ፍቃድ ማደስ፣ ከቀረጥ ነፃ የሆኑ እቃዎችን ማስገባት እና ከመንግሥት ጋር ውል መዋዋል ባሉ ጉዳዮች ላይ ግብር መከፈሉን የሚያሳይ ማስረጃ (Clearance) ማቅረብ ግዴታ ነው፡፡

ምንጭ- ፍትሕ ሚኒስትር

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here