በቻይና ደቡብ ምዕራብ ቾንግኪንግ ግዛት ውስጥ አንድ ነጥብ ሃያ ሁለት ካሬ ሜትር ወይም 170 የእግር ኳስ ሜዳዎችን ያክል የሚሰፋ ግዙፍ የባቡር ጣቢያ በ138 ወራት ተገንብቶ መጠናቀቁን ኦዶቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በዓለማችን በትልቅነቱ እውቅና የተቸረው የባቡር ጣቢያዉ ከኒውዮርኩ ግራንድ ሴንትራል የባቡር ጣቢያ በስድስት እጥፍ፣ በአውሮፓ በትልቅነቱ ከሚታወቀው ሊፕዚንግ ሃውፓንሆፍ አስራ አምስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ በሌላ አገላለጽ ከአንዳንድ ትናንሽ አገሮች ለአብነት በሮም መካከል ከምትገኘው ቫቲካን በእጥፍ እንደሚበልጥ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ለቾንግኪንግ ኢስት የባቡር ጣቢያ 29 ንጣፍ ወይም መድረክ፣ 15 የባቡር ሃዲድ / መጓጓዣ በረት/ እንዲሁም 16 ሺህ 500 ቶን የብረት ዘንግ ለጣሪያው ስራ ውሏል፡፡ በሰዓት 16 ሺህ ተጓዦችን ማስተናገድ የሚችል 400 ሜትር በ400 ሜትር የተለካ የተጓጓዦች መቆያ ሰገነትም በግንባታው ተካቷል፡፡
የባቡር ጣቢያው የተገነባው በከፍተኛ ተራራማ መልካምድር ላይ ነው፡፡ የባቡር ጣቢያን የመሰለ ደልዳላ ሜዳ የሚሻ ግዙፍ ፕሮጀክት በተጠቀሰው ስፍራ መገንባት የማይሞከር ቢመስልም በቻይና ግን እውን መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡
የቻይና የዜና ማሰራጫ ዢኒዋ እንደዘገበው ግንባታውን ለመጀመር በተራራማው ቀጣና ድማሚት ወይም ፈንጂ በመቅበር ተራራው እንዲፈራርስና መሬቱ ተደልድሎ ወደ ተስተካከለ ሜዳነት እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡በተለደለደለው ሜዳ ላይም ሁለት ሚሊዬን ኪዩቢክ ሜትር “ኮንክሪት” የተቦካ ጠጠር እና ሲሚንቶ – ለአስፋልት እንዲሁም 366 ሺህ ቶን ክብደት የሚመዝን ብረት ለሀዲድ ስራው በግብአትነት የዋለ ሲሆን 40 ሺህ የሰው ኃይል እና ሮቦቶችም በግንባታው መሣተፋቸው ነው ለንባብ የበቃው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


