የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ በ1957 እንደ ተመሠረተ ከታሪክ ማኅደር እንረዳለን፡፡ መሥራቾቹም ኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብጽ ነበሩ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በ1957 በሱዳን ርእሰ ከተማ ካርቱም ተካሄደ። ግብጽ አሸንፋ ዋንጫውን ስትወስድ ኢትዮጵያ በሁለተኛነት አጠናቀቀች።
ሁለተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ ያዘጋጀችው ግብጽ ነበረች። ኢትዮጵያም እጹብ ድንቅ በተሰኘ የአጨዋወት ጥበብ ለፍጻሜ ደርሳለች። በፍጻሜው ጨዋታ በግብጽ ተረትታ ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ በ1962 የተደረገውን ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጀች። ሀያ አምስት ሺህ ተመልካች እና ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በታደሙበት ስታዲየም ኢትዮጵያ በማራኪ ጨዋታ እና ስፖርታዊ ጨዋነት ግብጽን 4 ለ 2 በመርታት ዋንጫውን ወስዳዋለች። ሦስቱ ሀገራት የአፍሪካ ዋንጫ መሥራች በመኾንም በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ሁሌም ስማቸው በመልካም ሲወሳ ይኖራል።
በአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የበላይ አስተዳዳሪነት የሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ተወዳጅነቱ እና ተቀባይነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በዚህም መሠረት ሌሎች ሲያመነቱ የነበሩ እና በሂደት ነጻነታቸውን የተጎናጸፉ ሀገራት ውድድሩን መቀላቀል ጀመሩ።
ከ2019 ጀምሮም የአፍሪካ ዋንጫ 24 ሀገራት እየተሳተፉበት ይገኛሉ። በ2025 ሞሮኮ ያዘጋጀችውን 35ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ስድስት ቢሊዮን የስፖርት ቤተሰቦች በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ አማራጮች ተከታትለውታል። “ይህ ውድድር በዓለም ሕዝብ ዘንድ ምን ያህል ተመርጦ እንደሚታይ፣ እንደሚነበብ እና እንደሚደመጥ ነጋሪ ነው” ሲል ካፍ ኒውስ ዘግቧል። ካፍ ከሰሞኑ “የተሳታፊ ሀገራትን ቀጥር ከ24 ወደ 28 ለማሳደግ እየሰራሁ እገኛለሁ”ማለቱን የዜና ምንጩ ጨምሮ አብራርቷል።
የኾነው ኾኖ 36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በ2027 በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በሚገኙት ታንዛንያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል። ጨዋታው “ፓሞጃ 2027” የሚል ስያሜም ተችሮታል። ‹‹ፓሞጃ›› ማለት “ጠንካራ ትብብር” ወይም “አንድነት መፍጠር” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
“ፓሞጃ 2027 የአፍሪካ ዋንጫ ለኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ይበልጥ ቅርብ ነው፤ በጥበባዊ ትጋትም ልትይዘው ይገባል” ሲሉ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች እና የስፖርት ቤተሰቦች ይደመጣሉ።
አፍሪካን ፕሬስ እንደዘገበው በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 48 ሀገሮች በ12 ምድብ ተደልድለው የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እያንዳንዱ ምድብም አራት ሀገሮችን ይዟል፤ ሀገራቱ ሦስት ሦስት የደርሶ መልስ ጨዋታዎችንም ያደርጋሉ፡፡
ከእያንዳንዱ ምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ በመኾን የሚያጠናቅቁት ሁለት ቡድኖች ወደ 36ኛው ‹‹ፓሞጃ 2027›› የአፍሪካ ዋንጫ የሚወስደውን ትኬት በእጃቸው ያስገባሉ፡፡ ለዚህ ለመብቃትም የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከመስከረም እስከ ኅዳር ወር 2019 ዓ.ም ይካሄዳሉ ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን በማለፍ በምድብ 10 ከሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ እና ሱዳን ጋር ተደልድሏል። እስኪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ ሀገራትን ወቅታዊ አቋምን እንዳስስ፤ ኢትዮጵያ እንዴት ብትጫወት ነው ልታሸንፍ የምትችለው የሚሉትን ጉዳዮች የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን ዋቢ አድርገንም እንመልከት።
ሴኔጋል
የሴኔጋል ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ አለው። ቡድኑ እ.አ.አ በ2021 የመጀመሪያ ዋንጫውን ወስዷል። በ2002 እና 2019 ደግሞ በሁለተኛነት አጠናቋል። በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇን ሞሮኮን 1 ለ0 በመርታትም ሻምፒዮን መኾን ችሎ ነበር። ይሁንና ካፍ ቡድኑ “የሥነ ምግባር ጉድለት አሳይቷል” በሚል ያሸነፈውን ዋንጫ ተነጥቆ ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን እንዲሰጥ መበየኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ይህ ያለፈ የብሔራዊ ቡድኑ ታሪክ ነው። በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ግን ቡድኑ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሦሥቱ ተሸንፏል። ማሸነፍ የቻለው የኢራቅን ብሔራዊ ቡድን ብቻ ነው። በእድሜ የጠኑ ተጫዋቾችን ማሰባሰቡና ማሰለፉ፣ የተጫዋቾች ለከት የለሽ በራስ የመተማመን ስሜት፣ ተጋጣሚን ዝቅ አድርጎ የመመልከት አባዜ፣ የአጥቂዎች ቆሞ ጠባቂነት እና በተወሰኑ ሰመ ጥር ተጫዋቾች መተማመን የቡደኑ መለያ ድክመቶች ናቸው ተብሏል። ኢትዮጵያም በእነዚህ ክፍተቶች ውስጥ ለማለፍ ተግታ መሥራት ይኖርባታል።
ሞዛምቢክ
የሞዛምቢክ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ማምባዎቹ) በፊፋ የዓለም ደረጃ 103ኛ ላይ ይገኛል፡፡ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ጥሩ የሚባል አይደለም። በመኾኑም በአማካይ ከፍ ያለ የግብ መጠን ይቆጠርበታል። ከ1 ነጥብ 9 በላይ ግቦች በግጥሚያ ተቆጥሮበታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ቡድኑ በመስመር የሚያጠቁ ኹነኛ ተጫዋቾች የሉትም ነው የተባለው ።
ሱዳን
የሱዳን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በ2026 መረጃ መሠረት በዓለም 117ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የብሔራዊ ቡድኑ ዋነኛ ድክመት በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የሀገር ውስጥ እግር ኳስ ጨዋታ መቋረጡ ነው። ቡድኑ “ስደተኛ” ተጫዋቾችን በብዛት እያሰለፈ ይገኛል ነው ያለው። እነዚህ “ስደተኛ ተጫዋቾች” የሀገር ክብር ስሜታቸው የወረደ መኾኑን ጋዜጣው በድክመት ጠቅሷል።
በሀገር ቤቱ ያለው የፖለቲካ ትኩሳትም በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ የኾነ የሥነ-ልቦና ጫና ፈጥሯል። ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ተረጋግተው እንዳይጫወቱም አድርጓቸዋል ሲል ጋዜጣው አትቷል።
የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች እና የስፖርት ቤተሰቦች “ፓሞጃ 2027” የአፍሪካ ዋንጫ ለኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ይበልጥ ቅርብ ነው የማለታቸው ሚስጢር በዚህ የሒሳብ ስሌት መሠረት መኾኑን ልብ ይሏል። “ጠላትህ አሥር ሺህ ሠራዊት መኖሩን ከተረዳህ አንተ ደግሞ 20 ሺህ ሠራዊት አሰልፈህ ግጠመው” ብሒል ለብሔራዊ ቡድኑም ይሠራል። የተጋጣሚውን ቡድን ድክመት ካወቀ ድክመቱን አስከንድቶ በሥራ በልጦ መቅረብ ይኖርበታልና ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ጠንሳሽ ብትኾንም በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ከሦሥት ተሳታፊ ሀገራት ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች። ሦሥተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በ1962 አዘጋጅታ ግብጽን በማሸነፍ ዋንጫ ወስዳለች።
ከዚህ በኋላ ወደ መሠረተችው የአፍሪካ ዋንጫ የተመለሰችው ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ፊት አውራሪነት ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው ጨዋታ ነው። ይህን ግለት ማስጠበቅ ተስኗትም ሌላ ስምንት ዓመታትን ጠብቃ ነው በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራች ካሜሩን ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻለችው።
“የፊተኞቹ ኋላ፤ የኋለኞቹ ፊት” እንዲሉ የኢትዮጵያ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኑ በጅማሯቸው የሚያሳዩትን ጥንካሬ ማስቀጠል የማይችሉበት ምክንያት ምን ይኾን ?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ እና የስፖርት ማኔጅመንት መምህር ዳንኤል ጌትነት (ዶ/ር) በስልክ በሰጡት አስተያዬት በሀገሪቱ የሚገኙ ክለቦች ተተኪ ተጫዋቾችን ከሥር ወደ ላይ በቴክኒክ፣ በታክቲክ ፣ በሥነ ምግባር እና በሀገር ፍቅር ወኔ ኮትኩቶ የማሳደግ ልምዳቸው ደካማ ነው ብለዋል።
ክለቦች ተጫዋቾችን የሚመለምሉበት መሥፈርትም ሳይንሳዊ አይደለም ነው ያሉት። ከአጨዋወት ብቃት እስከ ባሕርይ፣ ከትንፋሽ እስከ መለያ ፍቅር ድረስ ብዙ ነገሮችን ከግምት ውስጥ አስገብተው መመልመል ግድ ይላቸው ነበር። ተጫዋች በስማ በለው (ስሚ ስሚ) ሳይኾን ሀገር ባወቀው ፀሐይ በሞቀው በሚታይ ችሎታቸው መመረጥ አለባቸው። አሁን ላይ የሚታየው የተጫዋቾች የብቃት መዋዠቅ፣ የወጥነት አቋም ችግር እና የመለያ ፍቅር መዳከም ለቦታው የሚመጥን ተጫዋች መመልመል እና መምረጥ ባለመቻሉ እንደኾነ ተናግረዋል። የክለቦች መዳከም ነው ብሔራዊ ቡድኑ ውጤት እንዲያጣ የሚያደርገው ሲሉ ምሁሩ ተናግረዋል።
ምሁሩ አያይዘውም በኢትዮጵያ የሚገኙ ክለቦች በረጅም ጊዜ ዕቅድ ታዳጊዎችን አሰልጥነው ለረጅም ጊዜ የመጠቀም ልምድን ሊጠናክሩ ይገባቸዋል ብለዋል። የክለቦች መጠንከር የብሔራዊ ቡድኑን ጠንካሬን ያመጣልና ነው ያሉት።
እንደ ክለብም እንደ ብሔራዊ ቡድንም “ኮቺንግ ስታፉ” አሠራሩን ሙያዊ (ፕሮፌሽናሊዝም) ሊያደርግ ይገባዋል። አሠልጣኞች የዓለምን አኹናዊ የእግር ኳስ ባሕርይን በየጊዜው እያነበቡ ማሰልጠን አለባቸው ብለዋል።
ዋና አሠልጣኙ ፣የሥነ ምግብ ባለሙያው፣ የአካል ብቃት አሠሪው፣ የግብ ጠባቂ አሠልጣኙ፣ የቡድን መሪው… የየራሳቸውን የቤት ሥራ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ከሠሩ እና ጥሩ ተግባቦት ከፈጠሩ ሌሎች ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኖች የሚያስመዘግቡትን ውጤት እኛም ማናስመዘግብበት የተለየ አመክንዮ የለም ነው ያሉት።
እንደ መውጫ
በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ከ560 ሺህ የማይበልጥ ሕዝብ ያላት ኬፕ ቨርዲ የወቅቱ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋን ስፔንን እና የደቡብ አሜሪካዋን ዑራጓይን አፍረክርካ የፈተነችበት መንገድ የዕቅድ ውጤት መሆኑን የዘ ጋርዲያን መረጃ አስነብቧል፡፡ ከ22ኛው የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጀንቲና ጋር ኬፕ ቨርዲ ያደረገችው ጨዋታም ልዩ ነበር። ኬፕ ቨርዲ በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ያሳየችው የእግር ኳስ ጥበብ ለብዙ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች ትልቅ የሥነ ልቦና ትምህርት ሰጥቷል፡፡
ኬፕ ቨርዲ በማራኪ ጨዋታ እና በሠከነ ሥነ ምግባር ወደ ጥሎ ማለፍ ከመሸጋገሯም በላይ ትንሿ ደሴት በዓለም እግር ኳስ ካርታ ላይ ስሟ በወርቅ ቀለም በክብር እንድትሰፍር አድርጓታል፡፡ ኬፕ ቨርዲ ስሟ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ እንደ መልካም ሽቶ ናኝቷል። ሚጢጣዋ ሀገር በዓለም አደባባይ ገዝፋም ታይታለች። በማራኪ የእግር ኳሰ የአጨዋወት ዘይቤዋ።
የኬፕ ቨርዲ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ውብ ጨዋታ ያሳየው ከግብ ጠባቂው እስከ አጥቂው ክፍል ወጥ አቋም በመያዙ ነው።
ቢቢሲ ” የኬፕ ቨርዲ ሰንደቅ ዓላማ በመላው የቡድኑ አባላት ልብ ውስጥ ይውለበለብ ነበር” ሲል አሞካሽቷቸዋል።
ቸር ያሰማን!
(ሙዋ ሊሙ)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


