በእግር ኳስ የዝውውር ታሪክ ብራዚላዊው ኔይማር ጁኒዬር ከስፔኑ ባርሴሎና ክለብ ወደ ፈረንሳዩ ፓሪሰን ዠርማ (ፒኤስጂ) ያደረገውን ዝውውር ያህል ውድ ዋጋ የተከፈለበት ተጨዋች የለም።
ኔይማር ባርሴሎናን ለቅቆ የአረብ ባለ ሀብቶች ንብረት ወደ ሆነው ፒኤስጂ ሲያመራ 222 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ተደርጎበታል ።ይህ የዝውውር ወጪ እስካሁንም ድረስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
በዓለማችን ላይ ለኮከብ እግር ኳስ ተጨዋቾች የሚከፈለው ውድ ገንዘብ ከሌሎች የመዝናኛ ዘርፎች ላቅ እያለ መምጣቱም ብዙዎቻችንን በማስገረም ላይ ይገኛል ።
እንደ ትራንስፈር ማርኬት ዘገባ ከሆነ አሁን ላይ በዓለማችን የእግር ኳስ ክህሎታቸው ላቅ ብሎ ከታዩ ተጨዋቾች ውስጥ ኖርዌያዊው የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ እና ስፔናዊው የባርሴሎናው ተጨዋች ላሚን ያማል 220 ሚሊዮን ዩሮ ግምት ያላቸው ተጨዋቾች ናቸው።
ፈረንሳዊው የሪያል ማድሪድ አጥቂ ኪሊያን ምባፔም ከሁለቱ ተጨዋቾች ቀጥሎ የ200 ሚሊዮን ዩሮ ተመን ወጥቶለታል።
ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2026/27 የውድድር ዘመንን ከመጀመሩ በፊት በክረምቱ የዝውውር መስኮት ለተጨዋቾች በጣም ውድ የሚባሉ የዝውውር ክፍያዎችን እያስመለከተን ይገኛል።
ቼልሲ እንግሊዛዊውን ሞርጋን ሮጀርስን ከአስቶን ቪላ በ138 ሚሊዮን ዩሮ ወይም በ117 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያስፈርመው ዋጋው የእንግሊዛዊያን ተጨዋቾች ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
እንግሊዛዊው ሮጀርስ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በጥብቅ ይፈለግ የነበረው በአርሰናል ቢሆንም ማረፊያው ግን ቼልሲ ሆኗል። አርሰናሎች በሮጀርስ ዋጋ መወደድ ምክንያት ሌላ ተጨዋች በገበያው ላይ እያፈላለጉ ሲሆን ቼልሲዎች ግን ወጣቱን ሞርጋን ሮጀርስ ለብዙ ጊዜ ያገለግለናል በሚል እሳቤ ከአስቶንቪላ አስኮብልለውታል።
አምና ሊቨርፑሎች አሌክሳንደር አይዛክን ከኒውካስል ዩናይትድ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውዱ ፈራሚ በማድረግ በ145 ሚሊዮን ዩሮ ወደ አንፊልድ ማምጣታቸው ብዙዎችን ጉድ አሰኝቶ ወይም እግር ኳስ እያበደ ነው አስብሎ ነበር።
ሊቨርፑሎች ግን በአይዛክ ብቻ ሳይወሰኑ በዚያው ዓመት ጀርመናዊውን ፍሎረን ዊርትዝን በ125 ሚሊዮን ዩሮ ከባየር ሊቨርኩሰን ሲያስፈርሙ እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን ሊቨርፑሎችም አበዱ ተብለው እንደነበረ አይዘነጋም።
ሊቨርፑሎች በ2024/25 ሻምፒዮን በሆኑበት የውድድር ዓመት ማግሥት ላይ እነ አይዛክን በውድ ዋጋ የሸመቷቸው ሻምፒዮንነታቸውን ለማስቀጠል እንደሆነ አያጠራጥርም ። ያም ሆኖ ግን ሊቨርፑሎች በ2025/26 የውድድር ዘመን ከሻምፒዮንነታቸው ቁልቁል ወርደው በአምስተኛ ደረጃ አጠናቀዋል።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በ2025/26 የውድድር ዓመት በአውሮፓ አስገራሚ ውጤትን አስመዝግበዋል። አስቶንቪላ የዩሮፓ ሊግ አሸናፊ ሲሆን ክሪስታል ፓላስም የኮንፈረንስ ሊግ አሸናፊ በመሆን በአውሮፓ ከሚዘጋጁ ሦስት ዋንጫዎች ውስጥ ሁለቱን ወደ እንግሊዝ አምጥተዋል ።
አርሰናል ምንም እንኳን ዋንጫውን በፈረንሳዩ ፒኤስጂ ቢነጠቅም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ተፋላሚ መሆኑ ለእንግሊዝ ክለቦች ውጤታማነት አንደኛው ማሳያ ሆኗል።
የእንግሊዝ ክለቦች ዘንድሮም ይሄንኑ ኃያልነታቸውን በአውሮፓ መድረኮች ለመድገም በሚመስል መልኩ ትላልቅ ተጨዋቾችን በትላልቅ ዋጋዎች በማዛወር ላይ ይገኛሉ።
ኔይማር ጁኒየር በ222 ሚሊዮን ዩሮ ከባርሴሎና ወደ ፒኤስጂ ያደረገው ዝውውር የእስካሁኑ ውዱ ዝውውር ሲሆን ኪሊያን ምባፔ ከፒኤስጂ ወደ ሪያል ማድሪድ በ180 ሚሊዮን ዩሮ ያደረገው ዝውውርም የዓለማችን ሁለተኛው ውድ ዝውውር ነው።
ሌላኛው ፈረንሳዊ የአጥቂ መስመር ተጨዋች ኦስማን ዴምቤሌ ከባርሴሎና ወደ ፒኤስጂ ያደረገው የ148 ሚሊዮን ዩሮ ዝውውር ደግሞ በሦስተኛ ውድ ዝውውርነት ተመዝግቧል።
ከሦስተኛው የዓለማችን ውድ ዝውውር በኋላ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ያለውን ውድ የተጨዋቾች ዝውውር ያካሄዱት ደግሞ የእንግሊዝ ክለቦች ናቸው።
ሊቨርፑል አሌክሳንደር አይሳክን ከኒውካስል ዩናይትድ በ145 ሚሊዮን ዩሮ ፣ቼልሲ ሞርጋን ሮጀርስን ከአስቶንቪላ በ138 ሚሊዮን ዩሮ እና ማንቸስተር ሲቲ ኤሊየት አንደርሰንን ከኖቲንግሃም ፎረስት በ135 ሚሊዮን ዩሮ ያዛወሩባቸው ዋጋዎች በዓለማችን የውድ ተጨዋቾች ዝውውር ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃዎችን ይዘዋል።
ፍሎረን ዊርትዝ ከባየር ሊቨርኩሰን ወደ ሊቨርፑል በ125 ሚሊዮን ዩሮ ፣ኤንዞ ፈርናንዴዝ ከቤኔፊካ ወደ ቼልሲ በ121 ሚሊዮን ዩሮ ፣ ጃክ ግሪሊሽ ከአስቶንቪላ ወደ ማንቸስተር ሲቲ በ117 ሚሊዮን ዩሮ፣ ዴክላን ራይስ ከዌስትሃም ወደ አርሰናል በ116 ነጥብ 60 ሚሊዮን ዩሮ ፣ሞይሰስ ካይሲዶ ከብራይተን ወደ ቼልሲ 116 ሚሊዮን ዩሮ እና ሳንድሮ ቶናሊ ከኒውካስል ወደ ቶተንሃም በ108 ሚሊዮን ዩሮ የተዛወሩባቸው ሒሳቦችም በጣም ውድ እና ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የወጣባቸው ሆነው ተመዝግበዋል።
የእንግሊዝ ክለቦች በውድ የዝውውር ዋጋ ራሳቸውን ማጠናከራቸውን አሁንም ቀጥለዋል። ሮጀርስን በቼልሲዎች የተነጠቀው ሻምፒዮኑ አርሰናል ብራዚላዊውን ብሩኖ ጉማሬሽ ከኒውካስል በውድ ዋጋ ለማስፈረም እየጣረ ይገኛል።
አርሰናል ከአርጀንቲናዊው የአትሌቲኮ ማድሪድ አጥቂ ሁሊያን አልቫሬዝ እና ከሌሎችም የአጥቂ ተጨዋቾች ጋር ስሙ እየተያያዘ በመሆኑ ትልቅ ወጪ ይጠበቅበታል።
ተጨዋቾችን በውድ ዋጋ ወደ ክለቡ በመቀላቀል የማይሳቀቀው ሊቨርፑልም ፈረንሳዊውን ብራድሊ ባርኮላን ከፒኤስጂ በሌላ እጅን በአፍ በሚያስጭን ውድ ዋጋ ለማዛወር መጣሩም የእንግሊዝ ክለቦች እና የዝውውር ዋጋዎች እብደትን ማሳያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የትኛው ክለብ ማንን አስፈርሞ ውጤታማ ይሆናል ? ወደፊት በጋራ የምንመለከተው ነው።
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


