የታፈኑ ስፖርተኞች

0
178

በዓለም ላይ ተወዳጅ በሆነው የእግር ኳስ ስፖርት በ90 ደቂቃ ውስጥ የአንድ ጊዜ ወይም የ15 ደቂቃ እረፍት ብቻውን በቂ ወደማይሆንበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡

በቅርቡ በሸኘነው 23ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ  ሳይቀር ተጨዋቾች ከእረፍት በፊትና ከእረፍት በኋላ የውሃ እረፍት ወይም የማቀዝቀዣ ጊዜ በሚል እረፍት ሲሰጣቸውም  አስተውለናል፡፡

በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም የረጅም ርቀት ሯጮች ውሃ ሳይጠጡ ወይም በራሳቸው ላይ ሳይደፉ ብዙ ርቀቶችን መሮጥ እየተሳናቸው ሄዷል፡፡

በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ለስፖርተኞች መታፈን  ወይም ትንፋሽ ማጣት ቀዳሚው ምክንያት የዓለም ሙቀት መጨመርና የዓየር ንብረት መዛባት መሆኑን ዓለም በተጨባጭ አረጋግጣለች፡፡

የተለያዩ ሀገራት የእግር ኳስ ክለቦች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየመጡ ባሉ ነገሮች ላይ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፡፡ እንደ ፊፋ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከሆነ  የተለያዩ የእግር ኳስ ክለቦች በዓየር ንብረት ለውጥ  ላይ  ጠንካራ  ሥራዎችን  እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ፎረስት ግሪን ሮቨርስ በእንግሊዝ ውስጥ የሚገኝ የእግር ኳስ ክለብ ነው፡፡ ይህ ክለብ በዓለም ላይ ካሉ ክለቦች ሁሉ በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ስሙ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ፎረስት ግሪን ሮቨርስ በስታዲየሙ ውስጥ ከአትክልትና ፍራፍሬ ውጪ የሆኑ ምግቦች እንዲሸጡ አይፈቅድም፡፡ ራሱ የሚያለማቸውንና ሌሎች አረንጓዴ አልሚዎችን በመደገፍ ጭምር  በእጅጉ ይታወቃል፡፡ ፎረስት ግሪን በጸሐይ ኃይል እና በሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጮች ይጠቀማል፡፡

ክለቡ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ይሠራል፡፡

የስፔኑ ሪያል ቤቲስ የእግር ኳስ ክለብም በዓየር ንብረት ለውጥ እና አከባቢ ጥበቃ ሥራዎቹ ስሙ በጉልህ የሚነሳ ክለብ ነው፡፡

ይህ ክለብ “ሁሌም አረንጓዴ “ ወይም  for ever green  በሚለው መርሁና ዘመቻውም ይታወቃል ፡፡ ሪያል ቤቲስ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በማስወገድ፣ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀምና ከሌሎች ክለቦች፣ ድርጅቶችና ከደጋፊዎቹ ጋር በመተባበር የዓየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማገዝም ይታወቃል ።

ዓለማችን በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በርካታ ጉዳቶችን ከማስተናገድም አልፋ ችግሩ በስፖርት ቱሪዝም ላይ የተደቀነ ከፍተኛ አደጋ ሆኗል፡፡

በብዙ ሀገራት ውስጥ የተገነቡት ትላልቅ እና ዘመናዊ ስታዲየሞች የሚገኙት ሰማይ ጠቀስ በሆኑ ፎቆች መካከል ነው፡፡ በነዚህ ስታዲየሞች ውስጥ ምንም እንኳን ንጹሕ ዓየር ወደ ውስጣቸው እንዲገባ ጥረት ቢደረግም በተግባር እያየነው የሚገኘው እውነት ግን የተመልካቾችንና  የስፖርተኞችን መታፈን ነው፡፡

በእግር ኳሱም ይሁን በሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ውድድሮች ስፖርተኞች በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወይም በመታፈን ሕመም ለከፋ ችግር ሲዳረጉ እያስተዋልን እንገኛለን፡፡

በርካታ የእግር ኳስ ክለቦች ለአብነትም ሊቨርፑል እና ቶተንሃም ሆትስፐር የካርበን ልቀትን በመቀነስ፣ በስታዲየሞቻቸው ኃይል ቆጣቢ ነገሮችን በመጠቀም በችግሩ ዙሪያ ፕሮጀክቶች ቀርጸው እየሠሩ ቢሆንም ከችግሩ ግዝፈት አንጻር ሥራዎቻቸው በቂ ሆነው አልታዩም፡፡

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በአረንጓዴ ልማት ላይ አተኩረው ሲሠሩ ይስተዋላሉ፡፡

ጎረቤታችን ኬኒያ እና ሀገራችን ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ እያሳረፉት ያለው አሻራ ከአህጉሩ አልፎ ለሌሎችም ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ የኬንያ እና የኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ሯጮች ለዓለም አቀፍ ውጤታማነታቸው  የየሀገራቱ ዓየር ንብረት መልካምነት አስተዋጽኦ አላበረከተም ማለት አይቻልም፡፡

ለዚህ ማሳያ ይሆነን ዘንድ እንደ ሞ ፋራህ ያሉ የረጅም ርቀት ሯጮች ከለንደን ወደ ኢትዮጵያ በመብረር ልምምዳቸውን በእንጦጦ ተራራ ላይ ሲያደርጉ አይተናቸዋል፡፡

የዓለማችን ሙቀት መጨመር በብዙ ሀገራት ምጣኔ ሀብት እና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሏል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የስፖርት ቱሪዝሙም የዚሁ ችግር ሰለባ እየሆነ ነው፡፡

የእግር ኳስ ተጨዋቾችም ሆኑ አትሌቶች  ንጹሕ ዓየር በማጣት ወይም በመታፈን የብቃታቸውን ጥግ የማያሳዩን ከሆነ ፈተናው ላቅ ብሎ መቀጠሉ አልቀረም፡፡

መፍትሔው በብዙ ሀገራት እና በአንዳንድ ክለቦች የተጀመሩትን የአረንጓዴ ልማቶች ማስቀጠል ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ሚሊዮነር ያደረገው የእግር ኳስ ስፖርትን ጨምሮ ብዙ ስፖርተኞች በዓየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከስፖርቱ እንዳይሸሹ ለነገው ዛሬ ላይ መሥራት ግድ ሆኗል፡፡

 

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የነሐሴ  4  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here