ትምህርት የአንድን ልጅ የዛሬ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን፣ የነገ ሕይወቱንም የሚወስን መሠረታዊ መሣሪያ ነው። ተማሪዎች በትምህርታቸው በተሟላ ሁኔታ እንዲሳተፉ የትምህርት ቤት፣ የመምህራን እና የወላጆች ሚና ወሳኝ ነው፡፡
በተመሳሳይ የመማሪያ ቁሶች መሟላት ደግሞ የመማር ሂደቱ በውጤት እንዲታጀብ የሚያስችል መሠረታዊ መሣሪያ ነው።
ወቅቱ ደግሞ ለአዲሱ የትምሕርት ዘመን ዝግጅት የሚደረግበት፣ የትምሕርት ቁሶች የሚሟሉበት እና ት/ቤቶችም ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው የተማሪ ምዝገባ የጀመሩበት ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ዝግጅቱ ለሁሉም ተማሪዎች አልጋ በአልጋ አይሆንም፤ በተለይ ደግሞ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ቤተሰቦች ደብተር፣ እስክርቢቶና ሌሎች የመማሪያ ቁሶችን ማሟላት ከባድ ፈተና ነው። ይህም በልጆች የመማር ፍላጎትና የትምህርት ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፤ በቤተሰቦች ላይም የገንዘብ ጫናን ይጨምራል።
ከዚህ ጋር በተገናኘ ታዲያ ዘመናትን ያስቆጠረው የመረዳዳት ዕሴታችን በተግባር የሚገለጥበት ነው፤ በርካቶችም አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ የሚል የበጎ አድራጎት ሥራን እያከናወኑ ነው፡፡
እገዛውን ካገኙት ተማሪዎች መካከል የባህርዳር ከተማ ነዋሪዋ ተማሪ ተምኪን ኢብራሂም አንዷናት፡፡ ተምኪን እንደነገረችን ደብተር ለመግዛት ቤተሰቦቿ የሚያጋጥማቸውን የኢኮኖሚ ችግር ለመቀነስ የተደረገላት ድጋፍ ትልቅ እፎይታ ሰጥቷታል። የትምህርት ቁሳቁስ በማግኘቷም በክፍል ውስጥ ማስታወሻ ለመያዝ፣ የቤት ሥራዋን በአግባቡ ለመሥራትና ትምህርቷን ለመከታተል ያስችላታል።
ለተደረገላት እገዛ ምስጋና ያቀረበችው ተማሪዋ “የተደረገልኝ የደብተር እገዛም በጣም አስደስቶኛል፤ ለቤተሰቤም እፎይታን ሰጥቶልኛል፡፡ ትምህርቴን በአግባቡ በመከታተል የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንድጓጓ አድርጎኛል” ብላለች።
በተመሳሳይ ፊሊሞን ኃይሌ ሌላው የደብተር ድጋፍ የተደረገለት የባሕር ዳር ከተማ ተማሪ ነው፡፡ ተማሪው ለበኩር በሰጠው አስተያየት የተደረገልኝ ድጋፍ “ቤተሰቦቸ የትምህርት ቁሳቁስ ለመግዛት የሚያጋጥማቸውን ችግር በመቀነስ ትምህርቴን በአግባቡ እንድከታተል ያደርገኛል። በትምህርቴ ጥሩ ውጤት ለማምጣት የበለጠ እንድተጋም ያበረታታኛል” ብሏል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች የተሰጣቸው ደብተር ለቤተሰባቸው እፎይታን እንደሰጠላቸው በማንሳት እነሱም ትምህርታቸውን በትጋት ለመከታተልና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ቃል ገብተዋል። በራሳቸው እንዲተማመኑ እና የተሻለ ሕይወት እንዲገነቡ ተስፋ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ፣ በችግር ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን የሚደግፉ ተግባራት እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። መሰል ድጋፎች የአንድን ተማሪ የዛሬ ችግር ከማቃለል ባለፈ የነገን ተስፋ በመገንባት ወሳኝ ሚናም እንዳላቸው ነው የተናገሩት።
በዚህ እሳቤ መሠረት፣ በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰብ ሥራ እያካሄደ ነው። “አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ያለው ንቅናቄም በርካታ ተቋማት፣ ባለሀብቶችና ግለሰቦች ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው።
በንቅናቄው የተለያዩ ተቋማት ድጋፋቸውን አበርክተዋል። የዓባይ ሕትመትና ወረቀት ፖኬጂንግ ፋብሪካ አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር የሚገመት 60 ሺህ ደብተር ድጋፍ አድርጓል። በተጨማሪም፣ የአማራ ክልል ማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 135 ሺህ ብር፣ ዩኒሴፍ አማራ ፊልድ ኦፊስ 157 ሺህ ብር፣ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ደግሞ 88 ሺህ ብር ለትምህርት ቁሳቁስ መግዣ ድጋፍ አድርገዋል።
የአማራ ክልል መምህራን ማሕበርን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትም ድጋፍ ስለማድረጋቸው ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ መኳንንት አደመ፣ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በተለይም ዩኒፎርም (የደንብ ልብስ)፣ ደብተርና እስክርቢቶ መግዛት የማይችሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመላክ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለመቀነስ ይህ ዓይነቱ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ አሁን ባለው በክልሉ 234 ሺህ ደርዘን ደብተርና 29 ሺህ ፓኮ እስክርቢቶ መሰብሰቡን ቢሮው ገልጿል። የተሰበሰበው የትምህርት ቁሳቁስ በፍትሐዊነት እንዲሠራጭ የሚደረግ ሲሆን፣ የትምህርት ዘመኑ እስኪጀምር ድረስ የማሰባሰብ ሥራው እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በአጠቃላይ፣ ለተቸገሩ ተማሪዎች ደብተርና ሌሎች የመማሪያ ቁሶችን ማቅረብ የዛሬን ችግር ከማቃለል በላይ በተማሪዎች ዘንድ የመተማመን፣ የመማር ፍላጎትና የስኬት ተስፋን ይገነባል። ተማሪዎች ከጓደኞቻቸው ተለይተው እንዳይቀሩ፣ በቁሳቁስ እጥረት ትምህርታቸው እንዳይስተጓጎልና በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚደረገው ድጋፍ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ተናግረዋል።
“ልጆቻችን እኛ እያለን ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን የለባቸውም” የሚለው መልዕክትም የዚህን ጥረት ዓላማ በግልጽ ያሳያል። ስለሆነም፣ መንግሥት፣ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ የልማት ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች የተቸገሩ ተማሪዎችን በመደገፍ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመው፣ ይህ ሲሆን ደግሞ የትምህርት ተሳትፎን ከማሳደግ ባለፈ በዕውቀትና በችሎታ የበለጸገ ትውልድን ለመገንባት የሚኖረው አስተዋጽኦ የማይተካ ነው።
መረጃ
አቅመ ደካማ ተማሪዎችን መርዳት በትምህርታቸው፣ በማህበራዊ ኑሮአቸው እና በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው።
ከብዙዎቹ በጥቂቱ፦
የትምህርት ውጤታቸውን ማሻሻል – የትምህርት መጽሐፍ፣ ደብተርና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያግዛል።
የመማር ፍላጎታቸውን ማዳበር –
ተጨማሪ ድጋፍና ምክር ማግኘታቸው በትምህርት ላይ ያላቸውን ፍላጎት ያሳድጋል።
በራስ መተማመንን ማሳደግ– እንደሌሎች ተማሪዎች እኩል ዕድል እንዳላቸው ሲሰማቸው በራሳቸው ይተማመናሉ።
ትምህርት እንዳያቋርጡ መከላከል –
በገንዘብና በኑሮ ችግር ምክንያት ትምህርት ከመተው ያድናቸዋል።
የእኩልነት ባህልን ማጠናከር – በትምህርት ቤት ሁሉም ተማሪዎች እኩል ዕድል እንዲያገኙ ያግዛል።
ለወደፊት ማህበረሰብ ጥቅም ማበርከት – ዛሬ የተረዱ ተማሪዎች ነገ የተማሩና ለሀገር እድገት የሚያበረክቱ ዜጎች ሊሆኑ ይችላሉ።
በአጠቃላይ- አቅመ ደካማ ተማሪዎችን መርዳት የግለሰብን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የቤተሰብን፣ የማህበረሰብንና የሀገርን እድገት የሚያጠናክር ትልቅ አስተዋጽኦ ነው።
ምንጭ፡- UNICEF Data ።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


