ኬክ ለመሥራት – አራት ወራት

0
4

ስፔናዊው ማርክ ሱዋሬዝ በሳኡዲ ንጉሣዊ ቤተሰብ የሰርግ ኬክ ለመስራት በተሰጠው ትእዛዝ ውል ወስዶ ክብደቱ 500 ኪሎ ግራም የተለካ፣ 33 ሺህ ከስኳር የተሰሩ የአበባ ቅጠል ቅርፆች ያሉት ድንቅ ስራውን በአራት ወራት ማጠናቀቁን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በስፔን ካታሎናዊው ማርክ ሱዋሬዝ በድንቅ የቅንጦት ኬክ አዘጋጅነቱ ታዋቂ ነው፡፡ በቅርቡ በተቀበለው ትዕዛዝ ግን  “ማስተርፒስ” ወይም እጅግ ድንቅ የፈጠራ ስራው ውጤቱ ማሳያ መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

የሰርግ ኬኩ ቁመት ሦስት ነጥብ አምስት ሜትር፣ ስፋቱ ደግሞ አንድ ነጥብ ስምንት ሜትር ነው፡፡ በሰርግ ስነ ስርዓቱ ላይ በታዳሚዎች የሚበላ ብቻ ሳይሆን በቤተ መዘክር ለእይታ  የሚበቃ ድንቅ ጥበባዊ ቁስ መምሰሉ ነው ለንባብ የበቃው፡፡

ለሳኡዲ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሰርግ ስነ ስርዓት ትእዛዝ የተሰጠው ባለሙያው የተሻለ ኬክ ለመስራት እቅድ ለማውጣት አንድ ወር ተኩል፣ ያሰበውን ወደ ተግባር ለመቀየር ደግሞ አራት ወራት ወስዶበታል፡፡ ለዚህም ሱዋሬዝ በስራው ላይ ቤተሰቦቹን እና በሙያው የተካኑ ጓደኞቹን ማሳተፉን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡

ተጋቢዎቹ ቀደም ብለው የኬክ ስራውን ሲያዙ የሰርግ ኬኩ ኬክ ከመምሰል ባሻገር ለዝግጅቱ ድምቀት እና ክብር የሚያጐናፅፍ የመታሰቢያ ሀውልት መስሎ እንዲታይ መፈለጋቸውን በነገሩት መሰረት ሰርቶ ለውጤታ ማብቃቱን ነው ያስረዳው-ባለሙያው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የነሐሴ 25  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here