‘‘የሰው ባሕር’’ የሚታይበት –     የባሕር ዳርቻ

0
3

ቻይና በስተደቡብ ባህር በምትዋሰንበት ክልል በሚገኘው አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ርዝመት የተለካው ”ዳሜሻ” የተሰኘው የባህር ዳርቻ በአንድ ጊዜ ሁለት መቶ ሺህ የሚደርሱ ተገልጋዮችን በማስተናገድ በእጅጉ የሚጨናነቅ ዳርቻ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡

በአሸዋ የተሸፈነው የዳሜሺ የባህር ዳርቻ በቻይና በረፍት እና በበዓላት ቀናት በተገልጋዮች የሚጨናነቅ ወይም የ “ሰው ባህር” ሆኖ ነው የሚስተዋለው፡፡ የባህር ዳርቻውን መጨናነቅ አስመልክቶ ተገልጋዮች ወደ ቦታው አቅንተው ባህሩን ሳይነኩ ቦታ አጥተው የተመለሱ በብሶት የፃፉትን በማህበራዊ ድረ ገጾች መመልከት በቂ ማስረጃ መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

በባህር ዳርቻው የሚከሰተውን መጨናነቅ በመመልከት የቀጣናው አስተዳደር አካላት ከግንቦት እስከ ጥቅምት ባሉ ወራት በየእለቱ  ወደ ዳርቻው የሚሄዱ ተገልጋዮች ቁጥር 80 ሺህ ብቻ እንዲሆን ለመገደብ መወሰናቸው ነው የተገለፀው፡፡ ለዚህም ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ቀድመው ቦታ እንዲያዝላቸው መመዝገብ ግድ እንደሚላቸው ነው የጠቆሙት – የአስተዳደር አካላቱ፡፡

የባሕር ዳርቻው በተገልጋዮች ለመጨናነቁ ዋናው ምክንያት ለማንኛውም ተገልጋይ ክፍት እና ያለ ክፍያ መስተናገድ መቻል አንዱ ሲሆን ሁለተኛው ከየአቅጣጫው ወደ ስፍራው ለሚጓጓዙ አውቶቡሶች እና  የባቡር መስመር  መገኘቱ በቀጣናው ኗሪዎችም ሆነ በጐብኚዎች ተወዳጅ ያደረገው መሆኑን ድረ ገጹ በማጠቃለያት አስፍሯል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር  የነሐሴ 25  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here