ቶሬስ ዴል ፔይን ብሔራዊ ፓርክ

0
83

ብሔራዊ ፓርኩ በደቡባዊ ቺሊ ፓታጐኒያ ክልል ነው የሚገኘው፡፡ የፓርኩ ቀጣና በዓለም አቀፍ የአካባቢ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ስምንተኛው ተፈጥሯዊ አስደናቂ ቅርስ ተብሎም ተሰይሟል፡፡ በድርጀቱ እውቅና ያገኘው በ1978 እ.አ.አ ነው፤ ጠቅላላ ስፋቱም 1814 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡

 

ቶሬስ ዴልፔይን ብሔራዊ ፓርክ ወደ ሚገኝበት ቀጣና ለማምራትም ከቺሊ ዋና ከተማ ሳንቲያጐ በአውሮኘላን ወደ ፖርቶ ናታሌስ መብረርን ይጠይቃል፡፡ ለጉብኝት ምቹ በሆኑት ከታህሳስ እስከ የካቲት ባሉት ወራት በማንኛውም ቀን በረራ ላይገኝ ስለሚችል በአማራጭ ከዋና ከተማዋ ሳንቲያጐ ወደ ፑንታ ኤሪና በአውሮኘላን 242 ኪሎ ሜትር ተጓጉዞ ከሁለት ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ተሽከርካሪን ተጠቅሞ ሌላ የአውሮኘላን ጉዞ ማደረግን ግድ ይላል፡፡

 

ፓርኩ ከአድማስ ጫፍ እንደ ማማ ገዝፈው በ “w’’ ቅርፅ በሚታዩ የ “ግራናይት” ከረጭ ኮረብታዎቹ ተለይቶ ይታወቃል፡፡

ከኮረብታዎቹ ግርጌ ተነስቶ ጫፍ ለመድረስ 87 ነጥብ አምስት ሜትር ሽቅብ መውጣትን ግድ ይላል፡፡ ቀጣናው በተራራ ወጪ ጀብደኞች ምቹ እና የሚወደድ ሲሆን የኮረብታዎቹ ጫፍም 3007 ሜትር ተለክቷል፡፡በዓመት እስከ 250 ሺህ ሰዎች እንደሚጐበኙትም ነው ለንባብ የበቃው፡፡ ከተራሮች አናት አንስቶ ቁልቁል የተነጠፈው በረዶ በሸለቆው የታችኛው ንጣፍ ታቁቶ ኃይቆችን ፈጥሮ ይስተዋላል፡፡ ይህም ለጐብኚዎች ተጨማሪ የደስታ ምንጭ ሆኖ ይገለግላል፡፡

 

በፓርኩ ከሚገኙ 12 ያህል የዱር እንስሳት ፑማ፣ጉዋናኮስ፣ ቀበሮ የመሳሰሉት ቀጣናውን መኖሪያቸው አድርግዋል፤ ከአዓእዋፍ ፍላሚንጐ፣ ኮንዱር፣ ውድፒከር… ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ከእፅዋት ፓርኩ በቁጥቋጦዎች እና ቅጠላቅጠሎች የተሸፈነ መሆኑን ድረገፆች በማጠቃለያነት አስፍረዋል፡፡

ለዘገባችን ላስቶሬስ፣ ቺሊ ትራቭል እና ጐግል ድረገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጳጉሜ  2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here