በቴክኖሎጂ መራቀቅ እና በከተሞች መስፋፋት ሳቢያ የዘመናችን የሰው ልጅ አኗኗር በከፍተኛ ሁኔታ እንቅስቃሴው እየቀነሰ መጥቷል። ይህ ተቀምጦ የመዋል አባዜ ጥንቃቄ ከጎደለው አመጋገብ ጋር ተዳምሮ እንደ ደም ግፊት፣ ስኳርና የልብ ሕመም ላሉ ተላላፊ ላልሆኑ ሥር የሰደዱ ሕመሞች መበራከት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዜጎችን ለብቸኝነትና ለመንፈስ ጭንቀት ሲዳርግ ይስተዋላል።
ይሁን እንጂ የንጋት ጎሕ ሲፈነጥቅ በየአደባባዩ፣ በየመንገዱ እና በየስፖርት ሜዳው በአንድነት ተሰልፈው በኅብረት ላባቸውን እያንጠፈጠፉ በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ ጤናቸውን ለመጠበቅ እና ቀናቸውን በብርታት ለመጀመር በጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይህ በኅብረት የሚከወን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ(ማስ ስፖርት) ከቀላል እንቅስቃሴ ባለፈ የአካልና የአእምሮ ሕክምና እንዲሁም የጠበቀ ማኅበራዊ ትስስር መፍጠሪያ ድልድይ ሆኗል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ ገብረሥላሴ መሰረት በጠዋት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ገብረሥላሴ ስፖርቱን የጀመሩት በድንገት አልነበረም። ከዓመታት በፊት ባጋጠማቸው የደም ግፊት ሕመም ምክንያት በሐኪም ጥብቅ ትእዛዝ ነበር ወደ ሜዳ ያመሩት። ከዚያ በፊት በግላቸው እንቅስቃሴ ለማድረግ ቢሞክሩም ብቻቸውን ሲሆኑ የሚደግፋቸው እና የሚያበረታታቸው ስለሌለ የተናጠል ልምምድ ውጤታማ ባለመሆኑ ተግተው እንዳልሠሩ ያስታውሳሉ። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ግን የማስ ስፖርትን በቋሚነት ከሌሎች ሰዎች ጋር ተቀላቅለው መሥራት ጀመሩ፡፡ ላለፉት 15 ዓመታትም ሳያቋርጡ ቀጥለዋል።
አሁን ላይ ስፖርት ለእሳቸው የቀን ተቀን የሕይዎታቸው እስትንፋስና መልካም ሱስ ሆኖባቸዋል። “ባልወጣሁበት ቀን ቤተሰቦቼ ታምሜ የቀረሁ ይመስላቸዋል” በማለት የማስ ስፖርትን እና የርሳቸውን ትስስር አቶ ገብረሥላሴ ገልፀውልናል፡፡ከዚህ በተጨማሪም “የምሠራው የጉልበትና የቴክኒክ ሥራ ነው፤ እረፍት የሚባል ነገር አላውቅም’የሚሉት አቶ ገብረስላሴ፤ ከስፖርቱ ጎን ለጎንም ሀኪም ያዘዘላቸውን በቀን አንዲት የደም ግፊት ክኒን እየወሰዱና በየሦስት ወሩ ምርመራ እያደረጉ እጅግ የተረጋጋና ጤናማ ሕይወት እየመሩ ይገኛሉ።
ለእሳቸው በጥዋት በሚሳተፉበት የአካል ብቃት ስፖርት ጤናቸውን ከመጠበቅ ባሻገር አብረዋቸው ከሚሠሩት ጋር ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር ፈጥረዋል፡፡ “በመካከላችን ከፍተኛ የዕድሜ ልዩነት ቢኖርም ስንገናኝ እንደ እኩያ ጓደኛና እንደ እውነተኛ ወንድም እና እህት በፍቅር ነው የምንሠራው፡፡ ስለጤንነታችን ሁኔታም በጋራ ስለምናወራ ፍጹም ሰላም ነው የሚሰማኝ፤ ለራሳችን የምንጠራራበት ቅጽል ስምም አለን” ይላሉ።
አቶ ገብረሥላሴ ለመላው ማኅበረሰብ፤ “ ማንኛውም ሰው የአካል እንቅስቃሴ ማድረጉ ጠቀሜታው ከፍያለ ነው፡፡ ብቻን ሲሆን ምክንያት አይታጣም፤ በጋራ ግን ሌላው ሲሮጥ በማየት እናንተም ወኔ ታገኛላችሁ፡፡ ያሰባችሁትን ግብም ታሳካላችሁ” በማለት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እየፈለጉ ከቤታቸው መውጣት ላቃታቸው ሰዎች ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በተመሳሳይ እንደ አቶ ገብረሥላሴ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሳተፉት ወይዘሮ ኤደን ገነት ናቸው። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ኤደን እንቅስቃሴ የጀመሩት የጎላ የጤና እክል ገጥሟቸው ሳይሆን ቅድሞ በሽታን ለመከላከል፣ ለአእምሮ የሚሰጠውን እርካታ በማሰብ እና በቡድኑ ውስጥ የሚታየውን መልካም መስተጋብር ከሌሎች በማየት እንደሆነ ነው የተናገሩ። ወ/ሮ ኤደን በቤት ውስጥ ኃላፊነትና በማኅበራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም ሳያቆራርጡ መሳተፍ ከጀመሩ ሰባት ዓመታትን አሳልፈዋል።
ወይዘሮ ኤደን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመጀመራቸው በፊት የጠና የጤና ችግር ባይገጥማቸውም በቀላሉ የመድከምና የመዝለፍለፍ ስሜት ይሰማቸው እንደ ነበር አስታውሰዋል፡፡ “አሁን ግን ያ ዓይነቱ ድካም ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል። ስፖርት ከሠራሁ በኋላ ሰውነቴን እታጠባለሁ፡፡ ከዛም ቀኑን ሙሉ እጅግ ደስተኛና ንቁ ሆኜ ነው የምውለው” በማለት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመሥራታቸው ያገኙትን ጥቅም ጠቁመዋል።
“ብዙ ሰዎች ቀኑን ሙሉ በቤት ውስጥ ሥራ ስለምንሠራ ወይም በሥራ ቦታ በእግር ስለምንጓዝ ስፖርት አያስፈልገንም” የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ እንዳላቸው የሚገልጹት ወይዘሮ ኤደን፤ “የቤት ውስጥ እንቅስቃሴ ከስፖርት ጋር ፈጽሞ አይገናኝም፤ ስፖርት በሥርዓት የሚሠራ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አስደናቂ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቅም የሚኖረው ሳይንሳዊ መርሆውን ከተከተለ ነው፡፡ ካልተከተለ ግን ያልተጠበቀ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ያሉት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የጤና እና አካል ብቃት መምህርና አሰልጣኝ አቶ ደጀኔ ብዙነህ ናቸው፡፡ የማስ ስፖርት አጠቃላይ ግብ ጤናው የተጠበቀ፣ ማኅበራዊ ግንኙነቱ የዳበረና አምራች ዜጋ ማፍራት መሆኑን ያብራሩት አሰልጣኙ፤ ስፖርቱ ውጤታማ እንዲሆን፦
ማሟሟቅና ማቀዝቀዝ፦ ወደ ዋናው ልምምድ ከመግባቱ በፊት ሰውነትን ማሟሟቅ፤ ሲጠናቀቅ ደግሞ ጡንቻዎችንና የውስጥ አካላትን አሠራር ወደ ነበሩበት ለመመለስ ማቀዝቀዝ የግዴታ ነው።
ጫናን በሂደት መጨመር፦ አንድ ሰልጣኝ ሁልጊዜ በተመሳሳይ መጠን መሥራት የለበትም። ሰውነት እንቅስቃሴውን ሲለምደው የልምምዱን መጠን፣ ድግግሞሽና ፍጥነት በሂደት ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
የሰዎችን ልዩነት ከግምት ማስገባት፦ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የተለየ ሆርሞንና የአካል ብቃት አለው። ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም በዕድሜ የተራራቁ ሰዎች በአንድ ዓይነት መጠን መሥራት ስለማይችሉ እንቅስቃሴው እንደ ግለሰቡ አቅም ሊመጠን ይገባል።
የማይቋረጥ ቀጣይነት፦ የአካል ብቃት ልክ በባንክ እንዳስቀመጥነው ገንዘብ አይደለም፤ ባንክ የተቀመጠ ገንዘብ ባናንቀሳቅሰውም አይጠፋም፣ ስፖርት ግን ባቆምንበት ቅጽበት ያገኘነው ጥቅም ሙሉ በሙሉ ይጠፋል፡፡ በማለት መምህር ደጀኔ የስፖርቱ ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አሰልጣኝ ደጀኔ በልምምድ ሜዳ ላይ የሚያጋጥማቸውን ትልቅ ተግዳሮት ሲገልጹ፤“አንድ ሰልጣኝ የጤና ምርመራ ሳያደርግ ወደ ስፖርት እንዲገባ በሳይንሱ አይመከርም ይላሉ። ከእኛ ጋር ካሉ 80 ሰልጣኞች መካከል የጤና ሁኔታቸውን በግልጽ ሞልተው የሰጡን ስድስት ሰዎች ብቻ ናቸው። ሰዎች የጤና ሁኔታቸውን ለመናገር ፈቃደኛ አይደሉም፤ ነገር ግን ይሄ ባለመደረጉ በድንገት ለከፋ የጤና ቀውስ ወይም ለህልፈት ሊዳረጉ ስለሚችሉ ቀዳሚ ተጎጂው ራሱ ሰልጣኙ ነው፡፡ስለዚህም ሰልጣኞች ከስልጠና በፊት በሃኪም የተሰጠ የህክምና ማስረጃ ማቅረብ የደህንነታቸው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ”።
በተጨማሪም በማስ ስፖርት ወቅት የሚመነጩት ‘ኢንዶርፊን’ የተባሉ ሆርሞኖች ጭንቀትንና ድብርትን ስለሚያስወግዱ ሰልጣኞች ደስተኞች ናቸው፡፡በቡድኑ ውስጥም በሕመማቸው ዙሪያ የሚወያዩበት መድረክ መኖሩም የእርስ በርስ መስተጋብራቸውን የበለጠ እንዲያዳብሩ እና ቤተሰባዊ ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ አቶ ደጀኔ ጠቁመዋል፡፡ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናን በነጻ የምንሸምትበት ተፈጥሯዊ መድኃኒት፣ ብቸኝነትን የምናባርርበትና ማኅበራዊ መስተጋብራችን የምናጠነክርበት ድንቅ ሕዝባዊ መድረክ ነው። ይሁን እንጂ ስፖርቱ የሚፈለገውን ዘላቂ በረከት እንዲሰጥ አስቀድሞ የጤና ምርመራ ማድረግ፣ የባለሙያዎችን መመሪያ መከተልና ሳይንሳዊ አሠራሩን መጠበቅ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።ከዚህ በተጨማሪም ስፖርት ሠርቶ ወዲያውኑ ጥሬ ሥጋ፣ ጮማና አልኮል መውሰድ የስፖርቱን ፋይዳ እንደሚያመክነው አስገንዝበዋል፡፡
አቶ ደጀኔ አያይዘውም በሽታ ቀድሞ ሳይጥለን እኛ ቀድመን በስፖርት እንጣልለው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መረጃ
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ(ማስ ስፖርት) ብዙ ሰዎች በአንድነት በተደራጀ መልኩ የሚያደርጉት የአካል እንቅስቃሴ ነው። ዋና ዓላማውም የማኅበረሰቡን አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጤና ማሻሻል ነው።
ጤናን ያሻሽላል – የልብ ሕመም፣ የስኳር በሽታና የደም ግፊት ስጋትን ለመቀነስ ይረዳል።
የአእምሮ ጤናን ይደግፋል – ጭንቀትንና የድብርት ስሜትን ለመቀነስ ያግዛል።
ማኅበራዊ ትስስርን ያጠናክራል – ሰዎች በጋራ እንዲገናኙ፣ እንዲተዋወቁና እርስ በርስ እንዲደጋገፉ ያደርጋል።
ንቁና አምራች ሕይወትን ያበረታታል – የአካል ብቃትንና የዕለት ተዕለት ጉልበትን ያሻሽላል።
ቀጣይነት ያስፈልገዋል – ለውጥ እንዲመጣ በመደበኛነት መሳተፍ አስፈላጊ ነው።
ጥንቃቄ:- ስፖርትን በተለይ ለረጅም ጊዜ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ የቆዩ ወይም የጤና ችግር ያላቸው ሰዎች ከመጀመራቸው በፊት የባለሙያ ምክር ቢያገኙ ይመረጣል።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


