ሮምን በባዶ እግሩ የወረረው ጀግና

0
64

አያት ቅድመ አያቶቻችን የወራሪውን የፋሽስት ጣሊያን ጦር ድባቅ መትተው ከሀገራችን ጠራርገው ካስወጡት ከ25 ዓመታት በኋላ ነበር ሻምበል አበበ ቢቂላ ሁሌም በታሪክ የሚዘከረውን ገድል በሮም ጎዳናዎች የፈጸመው፡፡

ሻምበል አበበ ቢቂላ እ.አ.አ በ1960 በሮም ኦሎምፒክ ለአፍሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማራቶን ውድድር ያጠለቀበት ድል፤ ጥቁር አፍሪካውያን በኦሎምፒክ እንዲሳተፉ በር ከፍቷል፤ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ለነበሩት የአፍሪካ ሀገሮችም ድል አብሳሪ ሆኖ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡

ሀገራችን በ1960 እ.አ.አ የሮም ኦሎምፒክ በሁለት የስፖርት ዓይነቶች መሳተፏን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ- በአትሌቲክስ እና በብስክሌት ስፖርት፡፡ የኢትዮጵያ ልዑክ ለሮም ኦሎምፒክ በስዊድናዊው አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን እየተመራ ቀደም ብሎ ወራት ሲቀሩት ነበር ዝግጅት የጀመረው፡፡

ቀኑ ሲቃረብም ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ቦታው ለማቅናት አትሌቶችን በመምረጥ ለጉዞ ተዘጋጀ፡፡ ዋሚ ቢራቱ፣ ንጉሤ ሮባ እና አበበ ዋቅጅራ በማራቶን ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ተመረጡ፡፡ ለወራት ጠንካራ ልምምድ ያደረገው አበበ ቢቂላ ግን በወቅቱ አልተመረጠም ነበር፡፡ በሌሎች ርቀቶች ሙሳ ሰይድ እና ማሞ ወልዴ፣ በብስክሌት ስፖርት ደግሞ ገረመው ደንቦባ፣ አላዛር ክፍሉ እና ሌሎች አትሌቶች ወደ አውሮፓ ለማቅናት በአውሮፕላን ማረፊያ መጠባበቅ ጀመሩ፡፡

በኦሎምፒክ ጨዋታዎች አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ልዑክ ጭምር እንዲመሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ አውሮፕላኑ ነዳጅ እስኪሞላ ድረስ ብዙዎቹ አትሌቶች የመጀመሪያቸው ስለሆነ ጉጉት፣ አግራሞትና ፍርሃት ተስተውሎባቸዋል፡፡ ማሞ ወልዴ፣ ንጉሤ ሮባ እና ባሻዬ ፈለቀ በ1956ቱ የሜልቦርን ኦሎምፒክ በመሳተፋቸው የተረጋጋ ስሜት ታይቶባቸዋል፡፡ በተለይ ባሻዬ ፈለቀ ከአሰልጣኝ ኒስካነን ጋር ስዊድን ደርሶ የመጣበትን ልምድ በማስታወስ ያበረታታቸው ነበር፡፡ አበበ ዋቅጅራም ወጣት አትሌቶች ፍርሃታቸውን እንዲያስወግዱ ይመክራል፡፡ ከዚህ ልዑክ ጋር ያልነበረው ግን በሮም ኦሎምፒክ ያሸንፋል ተብሎ ትልቅ ግምት የተሰጠው ዋሚ ቢራቱ ነበር፡፡

ዋሚን ለማምጣት የስፖርት ዳይሬክተሩ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ ወደ ቤቱ አቅንተው ነበር፡፡ ከብዙ ጥበቃ በኋላ ሁለቱ የስፖርት ሰዎች አውሮፕላን ማረፊያው የተመለሱት ግን ያልተጠበቀ መርዶ ይዘው ነው፤ ለወራት ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ የነበረው ዋሚ ቢራቱ፣ እግር ኳስ ሲጫወት በደረሰበት ድንገተኛ ጉዳት ጉልበቱ በመጎዳቱ መሳተፍ እንደማይችል ሀኪሞች ማረጋገጣቸውን ተናገሩ፡፡

በዚህ የተደናገጡት አሰልጣኝ ኒስካነን፣ በዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ ያልነበረውንና በምርጫው ያልተካተተውን አበበ ቢቂላን እንዲተካ ወሰኑ፡፡ የክብር ዘበኛው ወታደር አበበ ቢቂላ ለኦሎምፒክ አለመመረጡን ቀድሞ ስላወቀ የዕለት ወታደራዊ ተግባሩን በማከናወን ላይ ሳለ ነበር አቶ ይድነቃቸው እና ጋዜጠኛ ፍቅሩ ያገኙት፡፡ ሁለቱ የስፖርት ሰዎች አበበን ይዘው አውሮፕላን ማረፊያው ደረሱ፡፡ አውሮፕላኑም ታላቅ ታሪክ ይሠራል ተብሎ ያልተጠበቀውን አበበ ቢቂላን ይዞ የሜዲትራንያንን ባሕር አቋርጦ ጣሊያን ገባ፡፡

ጣሊያን በደረሱ ማግስትም ልምምድ ተጀመረ፡፡ ውድድሩ ሊካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት አሰልጣኝ ኒስካነን የውድድሩን መነሻ እና መድረሻ መስመር ለማሳየትና ቴክኒኮችን ለማስረዳት አትሌቶችን ይዞ ወደ ሮም ደቡባዊ ክፍል አቀና፡፡ በሌሎች ርቀቶች እና በብስክሌት ውድድር የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ውጤት ባለማምጣታቸው፣ ብቸኛው የሜዳሊያ ተስፋ በማራቶን ላይ ብቻ አረፈ፡፡

“በማራቶን ውድድር ፍጥነት አስፈላጊ ነው፤ ፍጥነት መቀነስ ዋጋ ያስከፍላል፤ ጥንካሬ እና ብርታት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ድካምና ህመሙን በመርሳት ወደ ፊት መሮጥ ይኖርብኛል፡፡ አትጨነቁ፣ አሸንፋለሁ” ሲል የክብር ዘበኛው ወታደር አበበ ቢቂላ ከውድድሩ አስቀድሞ በልበ ሙሉነት ለአሰልጣኙ እና ለአቶ ይድነቃቸው ተናገረ፡፡ አሰልጣኙም በእርግጥ ቃሉን እንደሚፈጽም ቢተማመኑም፣ የሶቪየቱን ሰርጌ ፖፖቭን እና የሞሮኮውን ራህዲ ቤን አብዱሰላምን አሳንሶ እንዳያይ መከሩት፡፡

በአሰልጣኝ ኒስካነን መሪነት መስመሩን ሲቃኙ የነበሩት አትሌቶች፣ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ዘርፋ የወሰደችውን ጥንታዊውን የአክሱም ሐውልት ካቆመችበት የሮም አደባባይ ደረሱ፡፡ ሁሉም ከመኪና ወርደው የአክሱምን ሐውልት ተመለከቱ፡፡ የሐውልቱ ጥላ በላያቸው ላይ ሲያርፍ ውስጣዊ የቁጭት ወኔ ተሰማቸው፡፡

የአክሱም ሐውልት ከቆመበት አደባባይ አንስቶ እስከ ማራቶኑ መድረሻ የነበረው ርቀት ከአንድ እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል ብቻ ነበር፡፡ ስለሆነም ይህ ስፍራ የውድድሩ ወሳኝ የማሸነፊያ ታክቲክ የሚተገበርበት መሆኑን አሰልጣኝ ኒስካነን በውል ተረድቶታል፡፡ አትሌቶቹም ከዚህ ቦታ ሲደርሱ ፍጥነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ከተፎካካሪዎቻቸው ተነጥለው መውጣት እንዳለባቸው ጥብቅ መመሪያ ተሰጣቸው፡፡

አበበ ዋቅጅራ የአክሱምን ሐውልት እያየ ለኢትዮጵያ ክብር ሲል እንደሚዋደቅ ተናገረ፡፡ አሰልጣኝ ኒስካነንም አበበ ቢቂላን ስለሚጫማው ጫማ ጠየቀው፡፡ ሻምበል አበበ ቢቂላም የተሰጠው ጫማ እግሩን ስላሻከረው እንዳልተመቸው እና በለመደው መንገድ በባዶ እግሩ ለመሮጥ መወሰኑን አስረዳ፡፡ የሮምን ጥቁር አስፋልት እግሩ እንዲለምደውም በጎዳናዎቹ ላይ በባዶ እግሩ ልምምድ አደረገ፡፡

በመጨረሻም ከ37 ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች በመነሻው መስመር ተደረደሩ፡፡ በመስመሩ የቆሙት ተወዳዳሪዎች የአበበን ባዶ እግር ሲመለከቱ “አስር ኪሎ ሜትር እንኳ አይዘልቅም” በማለት ተሳለቁ፡፡ ውድድሩ በተጀመረ በ45 ደቂቃ ውስጥ ግን የተሳለቁት አትሌቶች ወደ ኋላ መቅረት ጀመሩ፡፡ ቀደም ብሎ ጥንካሬያቸው የተነገረላቸው የሶቪየት፣ የሞሮኮ እና የአውስትራሊያ አትሌቶች ጎን ለጎን ሲሮጡ፣ አበበም ሳይነጠል አብሯቸው ይጓዝ ነበር፡፡ ጣሊያናውያን በተኙበት በዚያ ውድቅት ሌሊት አበበ ቢቂላ በሮም ጎዳናዎች የሚሮጥ ሳይሆን የሚንሳፈፍ ይመስል ነበር፡፡

ውድድሩ ወደ ፍጻሜው ተቃርቦ የመጨረሻው ርቀት ሲቀረው፣ ሯጮቹ በሮም አደባባይ የአክሱም ሐውልት ካለበት ስፍራ ደረሱ፡፡ አበበ ቢቂላ ዘራፊዎችን በምድራቸው ለመበቀል የቆረጠ በሚመስል ወኔ፣ ከኋላው የሚከተለው ተፎካካሪ አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ፍጥነቱን በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ፡፡

ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር አፍሪካውያን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ድል በሮም ጎዳናዎች ተፈጸመ፡፡ አበበ 42 ኪሎ ሜትሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሰከንድ ከሁለት ማይክሮ ሰከንድ ነበር፡፡ ይህም አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ሆነ፡፡

የፍጻሜውን መስመር ካለፈ በኋላ እንደ ሌሎች አትሌቶች ተዝለፍልፎ ከመውደቅ ይልቅ ሰውነቱን ለማቀዝቀዝ ልምምድ ሲሠራ መታየቱ ዓለምን አስደነቀ፡፡ ጋዜጠኞችም “አልደከመህም ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡለት፣ አበበ “ተጨማሪ 20 ኪሎ ሜትር መሮጥ የሚያስችል ጉልበት አለኝ” በማለት አስደመማቸው፡፡

ውድድሩ በምሽት በመከናወኑ ክስተቱን ያልተከታተሉት ጣሊያውያን በማግስቱ ከእንቅልፋቸው ሲነሱ በከተማቸው አዲስ ታሪክ መሠራቱን ሰሙ፡፡ በርካታ የጣሊያን ጋዜጦችም “ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በርካታ ወታደሮችን አሰለፈች፤ ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ ግን በባዶ እግሩ ሮምን ወረረ” በማለት በዋና ርዕሶቻቸው ገድሉን አሞገሱት፡፡ አበበ ቢቂላ በዘመናት ሂደት የማይደበዝዝ ድንቅ አሻራውን አሳረፈ፡፡ የአበበ ቢቂላ የሮም ኦሎምፒክ ታሪካዊ ድል ዛሬ ጳጉሜ አምስት ላይ 66 ዓመታትን ደፍኗል፤ እኛም ገድሉን በዚህ መልኩ ዘክረነዋል፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመስከረም 4  ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here