የአበቦች ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ

0
69

በህንድ ኡታራካንድ ግዛት በቻሞሊ አውራጃ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ቀጣናውን በ1931 እ.አ.አ ሁለት ተራራ ወጪዎች በአበባ የደመቀ መሆኑን ተመልክተው “ቫሊ ኦፍ ፍላወርስ” ብለው መሰየማቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡

የአበቦች ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በመንግሥት እውቅና አግኝቶ በይፋ በ1980 እ.አ.አ ነው የተመሰረተው፡፡ የፓርኩ ስፋትም 8750 ሄክታር ተለክቷል፡፡

የፓርኩ መገኛ ከፍታ ከ3352 እስከ 3658 ሜትር ከባህር ወለል በላይ መለካቱም ተረጋግጧል፡፡

የዓየር ንብረቱ መካከለኛው 19 ዲግሪ ሴልሺየስ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ሲሆን በጭጋግ የተሸፈነ  ቀዝቃዛው ደግሞ ከጥቅምት እስከ መጋቢት ያሉት ወራት ናቸው፡፡

የፓርኩ መልከአ ምድራዊ አቀማመጡ የተራራ ሜዳ ቀጣና ሲሆን በአልኘስ አበባዎች የተሸፈነም ነው፡፡ የፓርኩን ቀጣና የፑሽፓዋቲ ወንዝ ከግግር በረዶ ስር ወጥቶ ያረሰርሰዋል፡፡

ከእፅዋት 520 ዝርያዎች መገኘታቸውን በቀጣናው ጥናት ያደረጉ እና በመፃህፍት ለህትመት ያበቁት ኘሮፌሰር ቻንድራ ፓራኪሽ ማስፈራቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዱር አራዊት ጥቁር እና ቡናማ ቀለም ያለው ድብ፣ የበረዶ ነብር (ስኖው ሊኦፓርድ)፣ ቀይ ቀበሮ ማግኘታቸውም ተጠቅሷል፡፡

ከዓዕዋፍ የሂማሊያ ተራራዋ ምናልፊሳንት እና የተራራ ጫፍን  መኖሪያ ያደረጉ ዝርያዎች መገኛ ቀጣና ነው፡፡

ፓርኩን ለመጐብኘት ከህንዱ ደልሂ ከተማ በባቡር፣ ከሀርዲዋር እና ደሀርዱን በአውቶቡስ 270 ኪሎ ሜትር በሪሽኪሽ በኩል መድረስ ይቻላል፡፡ ለፓርኩ በቅርብ የምትገኘው ከተማ ጆሽማዝ ትባላለች፡፡

ጐብኚዎችም ከፓርኩ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኝ ጣቢያ ረዳት እና ጓዝ ተሸካሚ በቅሎ መያዝን ግድ ይላቸዋል፡፡

ፓርኩ ለጐብኚዎች ክፍት የሚሆነው  ከሰኔ እስከ መስከረም ብቻ ነው ፤ በቀሪዎቹ ወራት ቀጣናው  በበረዶ የሚሸፈን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ቫሊ ኦፍ ፍላወርስ፣ ብሉ ፓፒ ሆሊዴይ፣ ደብሊው ኤችሲ ዩኔስኮ እና  ዊኪፒዲያ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 4  ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here