መሬት እና እኛ!

0
78

መሬት እጅግ ውድ እና ውስን የተፈጥሮ ሀብት ነው። ለግብርና፣ ለመኖሪያ፣ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት እንዲሁም ለተፈጥሮ ሥነ-ምህዳር ሚዛን መጠበቂያነት የሚያገለግለው መሬት   በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት የልማት ሁሉ የጀርባ አጥንት ነው።

በተለይ ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ  የሚሆነው ሕዝብ ኑሮው በቀጥታ ከመሬት ጋር በተቆራኘው በአማራ ክልል  ይህ የተፈጥሮ ሀብት ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የአማራ ክልል ለሀገር ውስጥ ፍጆታም ሆነ ለውጭ ንግድ የሚውሉ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሰሊጥ እና የቅባት እህሎች በስፋት የሚመረቱበት በግብርና ጓዳ ነው። መሬቱ ለሰብል ልማት ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት እርባታ፣ ለደን ሀብት እና ለማዕድን ልማት ጭምር ምቹ መደላድልን የፈጠረ ነው።

 

ይህን ወሳኝ ሀብት በሳይንሳዊ መንገድ በመንከባከብ፣ በአግባቡ በማሥተዳደር እና ለታለመለት ዓላማ በማዋል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ ብልጽግናን ማምጣት ይቻላል። ይህንን ራዕይ ሰንቆ የሚንቀሳቀሰው የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር የክልሉን የ25 ዓመት አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ግብ መሠረት በማድረግ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክን አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንዳብራሩት በበጀት አመቱ የአሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ  ልማት ፍኖተ ካርታ  ዕቅድ ላይ የጋራ መግባባት በመያዝ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል። ክልሉ የነበረበት የጸጥታ ችግር በርካታ ተግዳሮቶችን ቢደቅንም ቴክኖሎጂን በመጠቀም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በተለይም የመሬት መረጃ አያያዝን ወደ ዲጂታል ሥርዓት በማሸጋገር ረገድ የተሠራው ሥራ ለአርሶ አደሩ የፈጠረው ዕድል ከፍተኛ ነው።

አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸውን በማስያዝ ከአበዳሪ ተቋማት ከሦስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማግኘት ችለዋል። ይህም አርሶ አደሩ የፋይናንስ እጥረቱን በማቃለል ወደ ዘመናዊ ግብርና እንዲሸጋገር ትልቅ አቅም ፈጥሮለታል ነው ያሉት።

ከዚህም በተጨማሪ የብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ አሥተዳደር ሥርዓት በ143 ወረዳዎች ተደራሽ መደረጉ፣ የመሬት ግብይት፣ ውርስ፣ ስጦታ እና የኪራይ አገልግሎቶች ቀልጣፋ እና ከብልሹ አሠራር የጸዱ እንዲሆኑ አስችሏል።

የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበው አዲሱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 452/2009 ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱም የሕግ ማዕቀፉን ይበልጥ አጠናክሮታል።

 

በመድረኩ የምዕራብ ጎጃም ዞን መሬት መምሪያ ችግሮችን በመቋቋም ሥራዎችን ሲያከናዉን መቆየቱን ነው የተመላከተው። የዞኑ መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥበቡ አማረ እንዳሉት ዞኑ አለመረጋጋት ከነበረባቸው አካባቢዎች አንዱ ቢሆንም በ2018 በጀት ዓመት የታቀዱ ግቦችን ከ88 በመቶ በላይ ማሳካት ተችሏል።

እንደ አቶ ጥበቡ ማብራሪያ ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ የነበረው የመሬት ወረራ በ2018 በጀት ዓመት እንዲቀለበስ ተደርጓል፡፡ በዚህም  ፍርድ ቤቶች በማይሠሩባቸው አካባቢዎች በሕዝባዊ ውይይት ይዞታዎች እንዲመለሱ ተደርጓል። በከተሞች ደግሞ በሕገ-ወጥ መንገድ የመንግሥትን መሬት አሳልፈው የሰጡ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ተችሏል።

መሬት የተወሰነ የተፈጥሮ ሀብት ከመሆኑ አንጻር በዘመናዊ እና በአግባቡ ማሥተዳደር እንደሚገባ የገለጹት አቶ ጥበቡ በገጠር የተሰጠው የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ለአርሶ አደሩ ሁለንተናዊ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ብቻ አይደለም በዞኑ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተርን በመጠቀም አርሶ አደሮች የባንክ ብድር በማግኘት ወደ ሜካናይዜሽን እርሻ እየገቡ ነው። “እንደ ወንበርማ፣ ጃቢ ጠህናን እና ቡሬ ዙሪያ ባሉ ቆላማ ወረዳዎች አርሶ አደሩ ተደራጅቶ ትራክተሮችን እና ዘመናዊ መሣሪያዎችን በመግዛት ምርታማነቱን እያሳደገ ይገኛል” ሲሉ አቶ ጥበቡ ተጨባጭ ውጤቶችን በአብነት አንስተዋል። በቀጣይም የ25 ዓመቱን የመሬት ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ በማድረግ ሌብነትን በካዳስተር ሥርዓት ለማስቀረት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ አበረታች አፈጻጸም ያስመዘገበው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር መሬት መምሪያ ነው። የመምሪያው ኃላፊ አቶ በላይነህ የኔሰው ለበኵር እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በገጠር መሬት አስተዳደር ዘርፍ ከተከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል ለአርሶ አደሩ የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የመስጠት ሥራ በስፋት ተከናውኗል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ያለውን የባለቤትነት ዋስትና ከማረጋገጡም በላይ ከዚህ ቀደም የነበረውን የፋይናንስ አቅርቦት ክፍተት ያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ በላይነህ አክለውም አርሶ አደሩ ያገኘውን የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንደ ማስያዣ (ዋስትና) በመጠቀም ከአበዳሪ ተቋማት ብድር እንዲያገኝ ሰፊ ሥራ መከናወኑን አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም በርካታ አርሶ አደሮች ያገኙትን ብድር ለግብርና ግብዓት ማሟያ፣ ለእንስሳት ርባታ እና ለተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች በማዋል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ችለዋል። ከዚህ ጎን ለጎን በተለያዩ ምክንያቶች የተነጠቁ የአቅመ-ደካሞች መሬት እንዲመለስላቸው የተደረገበት አበረታች ተግባር ተከናውኗል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ ውጤቶች ቢመዘገቡም በተለይም በአካባቢው አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የበጀት እጥረት እንዲሁም ከፍትሕ እና ከፍርድ ቤት አካላት ጋር ያለው የቅንጅት አሠራር ውስንነቶችን  እንደ ነበሩም አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ መምሪያው ችግሮቹን እንደ ዕድል በመጠቀም አቻችሎ ለመጓዝ ጥረት ማድረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል። በተለይ በከተማም ሆነ በገጠር የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለመግታት እና ለመከላከል ግብረ-ኃይል  በማቋቋም  ወደ ሥራ መግባቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ እመርታ ማሳየቱ ተገልጿል።

 

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ በ2019 በጀት ዓመት የከተማ እና የገጠር መሬት የሚለውን ክፍፍል በማጥበብ “አንድ መሬት፤ አንድ ተቋም” በሚል የተቀናጀ እይታ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቋል። የቢሮ ኃላፊው አቶ ሲሳይ ዳምጤ እንዳብራሩት በበጀት ዓመቱ ትኩረት ከሚሰጥባቸው አበይት ተግባራት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

የካዳስተር ሥርዓትን ማስፋፋት፦ ቀደም ሲል በ14 ከተሞች ብቻ ተወስኖ የነበረውን የከተማ መሬት ምዝገባ እና ካዳስተር ወደ 66 ከተሞች ማሳደግ።

ዲጂታላይዜሽን እና የፋይዳ መታወቂያ፦ የመሬት ባለቤትነት መረጃዎችን ከብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር በማስተሳሰር አርሶ አደሩ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ።

ተጋላጭ ክፍሎችን መጠበቅ፦ የአቅመ-ደካሞች፣ አረጋውያን እና ወላጆቻቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ ሕጻናትን የመሬት ባለቤትነት መብት በሕግ እና በአሥተዳደራዊ ውሳኔዎች ማረጋገጥ።

የልማት ተነሺዎችን ማቋቋም፦ ለልማት የሚነሱ አርሶ አደሮች ካሳ ብቻ ተከፍሏቸው እንዳይበተኑ፤ የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታ፣ የብድር አቅርቦት እና ተለዋጭ የገቢ ማስገኛ ዕድሎች እንዲመቻቹላቸው ማድረግ የሚሉት ናቸው።

 

በአጠቃላይ መሬትን በፍትሐዊነት፣ በተጠያቂነት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማሥተዳደር የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን የዕቅድ ንቅናቄው እስከ ቀበሌ ድረስ ወርዶ ሕዝቡ የዕቅዱ ባለቤት እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል። ቢሮው በ2019 በጀት ዓመት በ25 ዓመቱ አሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ላይ የተመሠረቱ ግቦችን ለማሳካት የመሬት አሥተዳደር አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ማዘመን፣ ሕገ-ወጥ አሠራሮችን እና የመሬት ወረራ ቁጥጥርን ማጠናከር እንዲሁም ለልማት ተነሽዎች የካሳ ክፍያ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ አመላክቷል።

የታቀደውን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ሁሉም የዘርፉ አካላት በቁርጠኝነት ሊረባረቡ እንደሚገባም አቶ ሲሳይ ዳምጤ ለባለድርሻ አካላት መልዕክት አስተላልፈዋል።

መረጃ

ውስን እና ውድ የሆነውን የተፈጥሮ ሀብት (መሬት) ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እና ዘላቂነቱን  ለማረጋገጥ የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን ይገባል፡-

     የአፈር እና የተፋሰስ ጥበቃ፦ በክልሉ በተለይም በተራራማ አካባቢዎች ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ስለሚታይ የዛፍ ተከላ፣ እርከን ሥራ እና የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀምን በዘመናዊ መንገድ መምራት ያስፈልጋል።

     ሕገ-ወጥነትን መከላከል፦ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራን፣ ያለአግባብ የመሬት ሽያጭን እና ድልድልን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት መግታት ይገባል።

     የህብረተሰቡን ተሳትፎ እና ግንዛቤ ማሳደግ

ማህበረሰቡ (በተለይ አርሶ አደሩ) ስለ መሬት እና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጥቅም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመስከረም 4 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here