የነገው ዓለም በዛሬው ሲቃኝ – የተስፋ ብርሃን ወይስ የስጋት ጥላ?

0
186

የሰው ልጅ የፈጠረው መሣሪያ አሁን ደግሞ ሰውን መርዳት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ማሰብም ጀምሯል፤ ከጋርዮሽ ዘመን ጀምሮ የሰው ልጅ የሕይወቱን ዘይቤ ለመቀየር መሣሪያዎችን ፈጥሯል። ማተሚያ ቤቱ ዕውቀትን ከጥቂቶች እጅ አውጥቶ ለብዙዎች አደረሰ፤ በእንፋሎት የሚዘወር ሞተር የሰውን ጉልበት በማሽን ተካ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል የሌሊትን ጨለማ አሸነፈ፤ ኮምፒውተር የሂሳብና የመረጃ ዓለምን ቀየረ፤ ኢንተርኔት ደግሞ ዓለምን በአንድ የመረጃ መረብ አገናኘ።

ይህ በዘመን ኡደት የቀጠለው የሰው ልጅ ግሩም ድንቅ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ መራቀቅ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የተለየ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማሽኖች እጃችንን ከመርዳት ባለፈ ጽሑፍ ይጽፋሉ፤ ምስል ይፈጥራሉ፤ ድምፅ ያመነጫሉ፤ በኮድ ይጽፋሉ፤ መረጃ ያቀናጃሉ፤ ቋንቋ ይተረጉማሉ- የሰውን ቋንቋና ተግባር መረዳት የሚመስል ችሎታም አሳይተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰዋዊ አስተሳሰብን በመላበስ ሰዋዊ ተግባራትን በፍጥነት በማከናወን የዘመኑን የቴክኖሎጂ ልቀት ካበሰሩት የፈጠራ ውጤቶች መካከል ሮቦቶች ይጠቀሳሉ፤ እነዚህ ሰው መሰል ሮቦቶች ታዲያ ዜግነት እስከ  ማግኘት በመድረስ ሰዋዊ መብትን እስከመጋራት ደርሰዋል፡፡

በ2017 እ.አ.አ ሳውዲ አረቢያ ሶፊያ ለተሰኘችው ሰው መሰል ሮቦት ሙሉ የዜግነት መብት ስትሰጥ የዓለምን መገናኛ ብዙኃን ጉድ ያሰኘ ታሪካዊ ክስተት ተመዘገበ። በመድረኩ ላይ ሶፊያ “የመጀመሪያዋ ሕጋዊ ዜግነት ያገኘች ሮቦት በመሆኔ ኮርቻለሁ” ስትልም  ተናገረች፤ ሮቦቶች ከሳይንስ ልብወለድ ፊልሞች ወጥተው የማኅበረሰቡ አካል የመሆናቸውን እውነታም ለዓለም አሳይታለች።

በተመሳሳይ በቻይናዋ መዲና ቤጂንግ ከተማ ከተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰው መሰል ሮቦቶች ውድድር ጀምሮ እስከ ግዙፍ ቤተ ሙከራዎች ድረስ የሚታየው ምጥቀት “የነገው ዓለም ከሮቦቶች ጋር እጅግ ጥገኛ ስለመሆኑ ያረጋገጠ ሁኗል” ሲል ያስነበበው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ መረጃዎችን የሚያጋራው ሮቦቲክ ፊርምስ የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ነው።

በቤጂንጉ ውድድር ላይ ከ26 በላይ ሀገራት የተወጣጡ ከአንድ መቶ በላይ ሰው መሰል ሮቦቶች በተለያዩ የውድድር መስኮች ተሰማርተው አስደናቂ ትዕይንት ለዓለም አሳይተዋል፡፡

የመረጃ ምንጩ እንዳስነበበው በዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ ከሦስት መቶ በላይ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂም ከሙከራ ደረጃ አልፎ ወደ ግዙፍ የንግድ ማዕበል መሸጋገሩ ተገልጧል።

በአሁኑ ወቅት ሰዎች በስልካቸው ላይ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ይወያያሉ። ተማሪዎች ለመማር ይጠቀሙበታል። የጤና ባለሙያዎች ምርመራን ለመደገፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓቶችን ይጠቀማሉ። ኩባንያዎች የደንበኞች አገልግሎትን፣ የመረጃ ትንተናን እና የምርት ሂደትን ለማሻሻል ይጠቀሙበታል።

በኢንዱስትሪ ዘርፍ ሮቦቶች እና ሰው ሠራሽ አስትዉሎት በመጣመር የማምረት ሂደትን እያሻሻሉ ነው። በግብርና ዘርፍ የሰብል ጤናን ለመከታተል፣ የውኃ አጠቃቀምን እና የምርት ትንበያን ለማሻሻል የሰው ሠራሽ አስተውሎት መፍትሔዎች እየተሞከሩ ነው።

የገንዘብ እና የኢኮኖሚ አኃዞችም የዚሁ ፈጣን ሽግግር ግልጽ ማሳያ ናቸው። ፎርብስ እንዳስነበበው ደግሞ ሰው መሰል ሮቦቶች በ2023 እ.አ.አ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋ ነበራቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ ዘርፉ በ50 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ ነው፡፡ በ2030 እ.አ.አ የዘርፉ ዕድገት እስከ 13 ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎም ይጠበቃል።

መሠረቱን በኒውዮርክ ባደረገው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ እና የባንክ ተቋም ጎልድማን ሳክስ ትንበያ መሠረት እስከ 2035 እ.አ.አ ድረስ የዘርፉ ገበያ 38 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሮቦቶች በፋብሪካዎችና በንግድ ዘርፍ አገልግሎት ላይ እንደሚሰማሩ ተቋሙ በትንበያው አስቀምጧል። ሀገራትም በዚህ ቴክኖሎጂ የበላይ ለመሆን ከወዲሁ ፈጣን እሽቅድምድም ውስጥ ገብተዋል፡፡

የቻይና መንግሥት በዘርፉ የዓለም መሪ ለመሆን አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በጀት መድቦ የውድድሩን አቅጣጫ እያፋጠነው ስለመሆኑም  ነው በትንበያው የተመላከተው፡፡

ከመንግሥታቱ ባለፈ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ሰው መሰል ሮቦቶቹ ለወደፊት የዓለምን ኢኮኖሚ ለመሸከም እና አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ቁልፍ እንደሆኑ ይናገራሉ። የቴስላ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢሎን ማስክ ኦፕቲመስ የተሰኘውን ሮቦት ሲያስተዋውቁ፣ “ሰውን ከአደገኛና ከባድ የአካላዊ ጉልበት ሥራዎች ነፃ በማውጣት የዓለምን ኢኮኖሚ በእጥፍ ያሳድጋሉ” ሲሉ ይሞግታሉ። ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ እንደዘገበው ባለሀብቱ የሮቦቶችን የጅምላ ሽያጭ ዋጋ አሁን ካሉበት ወደ 20 ሺህ ዶላር ዝቅ በማድረግ በመላው ዓለም ለማሰራጨት እየሠሩ ነው፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘመኑ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰውኛ አስተሳሰብ ዓለማችን በፍጹም ፍጥነት እየተቀየረች ትገኛለች፤ ይህ ደግሞ ተስፋዎች እንዳሉት ሁሉ ስጋቶችንም እያስከተለ ነው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን የፈጠራ ባለቤቶችንም ሳይቀር ስጋት ውስጥ አስገብቷቸዋል፡፡

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተስፋ እና ስጋት

የሰው ልጅ አስተሳሰብን መኮረጅ የጀመረው ሰው ሠራሽ አስተውሎት አዲስ የዕድል በር እየከፈተ ነው። በጤና፣ ትምህርት፣ ግብርና እና ንግድ ውስጥ ሥራን ማቅለል፣ ምርታማነትን ማሳደግና አዳዲስ መፍትሔዎችን ማምጣት ተስፋው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በተለይ የሕክምናውን ዘርፍ ተደራሽ ማድረግ፣ ማሳደግ፣ አዳዲስ ሥራዎችንና የንግድ ዕድሎችን መፍጠር እንዲሁም መረጃን በፍጥነት መተንተንና ውሳኔን ማገዝ ቴክኖሎጂው ያመጣቸው አበርክቶዎች ናቸው፡፡

በሌላ ጎኑ ደግሞ የግል መረጃ ጥሰት፣ የሐሰት መረጃ መስፋፋትና የሰዋዊ ቁጥጥር መዳከም፣ የውሳኔ መዛባት፣ በቴክኖሎጂ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆን እንዲሁም ለማጭበርበርና የሳይበር ጥቃት አጋላጭነት ዘርፉ ያመጣቸው ስጋቶች ናቸው። እንደ ሳም አልትማን ያሉ የቴክኖሎጂ መሪዎች፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የሮቦቲክስ ጥምረት ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጭ የመሆንና የደኅንነት ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

ስጋቶች እንዴት ይገቱ?

ይህንን የቴክኖሎጂ ስጋት ለመግታት ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጠንካራ ሕጎችን መደንገግ ጀምረዋል። የአውሮፓ ህብረት ታሪካዊውን የኤ አይ  (የሰው ሠራሽ አስተውሎት) ሕግ አውጥቷል፡፡ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ የሮቦቶች እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት የሰው ልጅ ቁጥጥርና የደኅንነት ማረጋገጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ ሕብረቱ በሕግ አስገድዷል።

በተመሳሳይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የራስ ገዝ የጦር መሣሪያዎችና የሮቦቶች አጠቃቀም ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲኖር እየሰራ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የጥራት ምዘናዎች ድርጅት ደግሞ ISO 13482 የተሰኘውን የሰው መሰል ሮቦቶች የአካል ደኅንነት መስፈርት በመተግበር ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ቻይና እና አሜሪካ የሮቦቶችን የሳይበር ደኅንነትና የግል መረጃ አያያዝ የሚቆጣጠሩ ጥብቅ መመሪያዎችን አውጥተዋል።

የቴክኖሎጂው ስጋት ግን በቁጥጥር ማጣት እና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ ብቻ  የተወሰነ አይደለም። የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም መረጃ እንደሚያሳየው በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሮቦቶች ቴክኖሎጂ ምክንያት 85 ሚሊዮን ሰዎች ከሥራ ገበታቸው የመሰናበት ስጋት ተደቅኖባቸዋል፡፡ በተለይም የአምራች ድርጅቶች፣ የዕቃ አቅርቦት ስርጭት እና አስተዳደር ሥራዎችን ቴክኖሎጂው ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠራቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

በሌላ ጎኑ ግን ተቋሙ ለ97 ሚሊዮን አዳዲስ ሥራዎች መፈጠር ቴክኖሎጂዎች ምክንያት እንደሚሆኑ መረጃው ያመላክታል፡፡

ቴክኖሎጂው ወደፊት በሕክምናው፣ በአረጋውያን እንክብካቤና ድጋፍ፣ በአደጋ ጊዜ ፍለጋ እና የነፍስ አድን ሥራዎች ላይ የሚኖረው ሚና እንደ ታላቅ ተስፋ ይቆጠራል።

ኢትዮጵያስ?

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዓለም አቀፍ ለውጥ ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህ ውጭ አትሆንም። ጥያቄው የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆን ብቻ ወይስ የፈጠራ ሥራ ባለቤት መሆንም ጭምር? ይህን ለማሳካት የዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ የመረጃ ጥራት፣ የምርምር አቅምና የሰው ኃይል ወሳኝ ናቸው።

በተለይ የአካባቢያዊ ቋንቋዎች፣ ግብርና፣ ጤና እና ትምህርት ላይ የሚውሉ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መፍትሔዎችን ማሳደግ ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን በራሷ ችግሮች ላይ መፍትሔ የምታመነጭ እንድትሆን ያግዛታል።

በአጠቃላይ ሰው መሰል ሮቦቶች ወደ ዓለማችን መምጣታቸው ሊገታ የማይችል የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው። ቴክኖሎጂው በራሱ መልካም ወይም ክፉ አይደለም፡፡ የነገዋን ዓለም መልክ የሚወስነው የሰው ልጅ ይህንን ምጥቀት በምን ዓይነት ሕጋዊ እና ሥነ-ምግባራዊ ማዕቀፍ ይመራዋል? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ትልቅ ተስፋ ነው፤ ያለቁጥጥር ከዋለ ግን ትልቅ ስጋትም ነው፡፡ በመሆኑም በሰዋዊ ቁጥጥር በአግባቡ መጠቀም ይገባል የሚለው የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ነው። ባለሙያዎቹ እንደሚያስገነዝቡት ቴክኖሎጂዎች በአንድ መሠረታዊ ሐሳብ ላይ ይመሠረታሉ – በሰዎች ትዕዛዝ ይመራሉ፣ እነሱ ይፈጽማሉ።

 

(በፈቃዱ ሄሮዳ)

በኲር የመስከረም  4  ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here