የ2027ቱ ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም በኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ በጋራ አዘጋጅነት ከሰኔ 12 እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል። በማጣሪያው 48 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን ምድባቸውን አንደኛ እና ሁለተኛ ሆኖው የሚጨርሱ ብሄራዊ ቡድኖች በ46ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የሚያስችላቸውን ትኬት ይቆርጣሉ፡፡ በቅድመ ማጣሪያው ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔን በድምር ውጤት አራት ለባዶ አሸንፎ ያለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 ከሴኔጋል፣ ሱዳን እና ሞዛምቢክ ጋር ተደልድሏል።
ቡድኑ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን መስከረም 15 ቀን ከሱዳን ጋር ከሜዳው ውጪ በማድረግ የሚጀምር ይሆናል፡፡ መስከረም 19 ቀን ደግሞ ሴኔጋልን በአሸናፊነት ምሽጉ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያስተናግዳል። ለአምስት ዓመታት ያህል በሜዳ እጦት የቤት ጨዋታዎቹን በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በስደት ሲያደርግ መቆየቱ የተጫዋቾችን የስነ-ልቦና ዝግጁነት በእጅጉ ጎድቶት ቆይቷል። ይሁንና አሁን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የሰጠውን ጊዜያዊ ፍቃድ ተጠቅሞ በገዛ ምድሩ ከደጋፊው ፊት መቅረቡ አዲስ የታሪክ ምዕራፍና ከፍተኛ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን የተገኘውን የባሕር ዳር ስታዲየም የቤት ውስጥ ዕድል ተጫዋቾቹ እንደ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሊጠቀሙበት ይገባል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በታሪክ ለዋሊያዎቹ ጠንካራ ምሽግ ሆኖ አገልግሏል። ቡድኑ በዚህ ስታዲየም ባደረጋቸው አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ግጥሚያዎች አስደናቂ የማሸነፍ ታሪክ አለው። ለምሳሌ ሌሶቶን እና ኬንያን ከ60 ሺህ በላይ ደጋፊ ፊት ያሸነፈበት፣ ማዳጋስካርን ባማረ የኳስ ፍሰት አራት ለባዶ የረታበት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በከዋክብት የተገነባችውን ጠንካራዋን ኮትዲቯርን ሁለት ለአንድ ያሸነፈበት ታሪካዊ ክስተት የሚጠቀስ ነው። የባሕር ዳር ስቴዲየም ያለ መሸነፍ ታሪክ እና የሕዝብ ድጋፍ የቡድኑን ወኔ የሚያነሳሳ ትልቅ ስነ-ልቦናዊ ስንቅ ነው።
ወደ ምድብ ድልድሉ ከተቀላቀለ በኋላ የተጠናከረ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው ብሔራዊ ቡድኑ፤ በዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሰሀሌ እየተመራ የሀገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾችን እና ወጣቶችን ያካተተ ስብስብ በመያዝ ልምምዳቸውን ሲያከናውኑ ሰንብተዋል። ይህም ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ከሚያሳየው ድክመት ወጥቶ በገዛ ሜዳው የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያስመዘግብ ታስቦ የተቃኘ ነው።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሰሀሌ የሚመራው ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሱዳን ጋር በደቡብ ሱዳን በጁባ ብሄራዊ ስቴዲየም ላይ ያደርጋል፡፡ የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጠንካራ የቡድን አንድነት እና የታክቲክ ዲሲፕሊን አላቸው። ነገር ግን በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በሜዳቸው ማድረግ የነበረባቸውን ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ መገደዳቸው የሜዳ ባለቤትነት ስሜታቸውን ይቀንሰዋል። በተጨማሪም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ የትኩረት ማነስ ይታይባቸዋል። በመሆኑም ዋሊያዎቹ ጨዋታውን በጥንቃቄ በመጀመር የስነ-ልቦና የበላይነቱን መውሰድ አለባቸው። የሱዳን ተከላካዮች ፍጥነት ስለሚጎድላቸው በፈጣን ክንፍ አጥቂዎች በመጫን ስህተት እንዲሰሩ ማድረግ እና ጨዋታው ሊጠናቀቅ በሚቃረብበት ወቅት የሚኖረውን የትኩረት ማነስ መጠቀም የድል ቁልፍ ነው።
ሰቀድሞው የአርሴናል ኮከብ ፓትሪክ ቬራ የምትመራው ሴኔጋል በአውሮፓ ታዋቂ ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱ ከዋክብት ስብስብ ያላት ሲሆን ተጫዋቾቿ ከፍተኛ የአካል ብቃት እና ፍጥነት ልዩ መገለጫቸው ነው። ነገር ግን ከደካማ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር በሚጫወቱበት ወቅት ከመጠን በላይ በራስ መተማመን ስለሚታይባቸው ክፍተቶችን ይፈጥራሉ። ታዲያ ዋሊያዎቹ ከኳስ በስተጀርባ በመሆን “ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከላከል” የሜዳውን ክፍተት ማጥበብ ይኖርባቸዋል። በተለይም በባሕር ዳር ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታ የአየር ሁኔታውን እና የደጋፊውን ድጋፍ በመጠቀም ከኳስ ውጪ ያለውን እንቅስቃሴ በማጠናከር በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ስልት የኋላ ክፍላቸውን መስበር ይቻላል።
የሞዛምቢክ ብሄራዊ ቡድን ደግሞ ኳስን መሬት ለመሬት በማደራጀት እና በፈጣን የሰንሰለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ክፍል በመድረስ ረገድ የተካኑ ናቸው። ነገር ግን በአካል ብቃት እና ረጅም ኳሶችን ከመከላከል አንጻር ተጋላጭ ናቸው። በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ከፍተኛ ጫና በመፍጠር የኳስ ቁጥጥር ፍሰታቸውን ማቋረጥ ወሳኝ ነው። እንደ ጋቶች ፓኖም ያሉ የአካል ብቃት ያላቸውን አማካዮች በመጠቀም እና ብልጫ በመውሰድ በሚገኙ የቆሙ ኳሶች (Set-pieces) አማካኝነት ግቦችን ማግኘት ይቻላል።
ይህን ተግባራዊ ላመድረግ ግን ቀላል እንደማይሆን ይገመታል፡፡ የመጀመሪያው እና ዋናው ስጋት በአህጉራዊ መድረክ ላይ የሚታየው የተጫዋቾች የልምድ ማነስ እና የዓለም አቀፍ ግጥሚያዎች እጥረት ነው። አብዛኞቹ የዋሊያዎቹ ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ ሊግ ላይ ብቻ የሚጫወቱ በመሆናቸው እንደ ሴኔጋል ካሉ ከዋክብት ጋር ሲጋጠሙ የስነ-ልቦና ጫና ሊያርፍባቸው ይችላል- የብዙዎች ስጋት ነው።
ሁለተኛው ተግዳሮት የስትራቴጂካዊ እቅድ እና የረጅም ጊዜ ዝግጅት እጥረት ነው። ብሔራዊ ቡድኑ ብዙ ጊዜ ለአጫጭር ቀናት ብቻ ተሰብስቦ ልምምድ ማድረጉ የተጫዋቾችን የሜዳ ላይ ተግባቦት እና የአጨዋወት ፍልስፍና ፍፁም እንዳይሆን ያደርገዋል። ሌላው እንደ ስጋት የሚነሳ የስፖርት መሠረተ ልማት እጥረት ሲሆን የባሕር ዳር ስታዲየም ያገኘው ፍቃድ ጊዜያዊ በመሆኑ ወደፊት የሚኖሩ ጨዋታዎችን በዘላቂነት ለማስተናገድ ስታዲየሞችን ሙሉ በሙሉ የማዘመን ሥራ ገና አለመጠናቀቁ ስጋት ይፈጥራል።
ታዲያ ለእነዚህ ስር የሰደዱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ የድል ጉዞው መነሻ ነው። የተጫዋቾችን የስነ-ልቦና ጥንካሬ ለመገንባት ቀጣይነት ያለው ሙያዊ እገዛ የሚያስፈልግ ሲሆን ተጫዋቾች ከየትኛውም ትልቅ ቡድን ጋር እኩል መጫወት እንደሚችሉ በራስ መተማመናቸው ከፍ ሊል ይገባል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሰሀሌም ግልጽ የታክቲክ እቅድ ይዘው ሜዳ መግባት ይጠበቅባቸዋል። ጨዋታዎችን በጥንቃቄ በማንበብ፣ ወቅታዊ የተጫዋቾች ቅያሬን በአግባቡ በመጠቀም እና የተጋጣሚን ደካማ ጎን በማጥናት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ወጣት ተጫዋቾችን ከነባሮቹ ጋር በማጣመር ሚዛናዊ ቡድን መገንባትም ዋሊያዎቹ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያደርጋል፡፡
ተጨዋቾች በጨዋታ ወቅት የሚፈጠሩ ጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ተገንዝበው 90 ደቂቃ ሙሉ በጥንቃቄ መጫወት እና የቡድን ሥራን ከግል ክብር ማስቀደም አለባቸው። ፌዴሬሽኑም ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኞች ቡድን የሚገባቸውን ማበረታቻዎች በወቅቱ ማቅረብ፤ የትራንስፖርት እና የሆቴል ማረፊያዎችን ያለምንም ጉድለት ማዘጋጀትና ከካፍ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የሜዳ ፍቃድ ጉዳዮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ መሥራት ይኖርበታል።
በመጨረሻም ደጋፊው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰነዝራቸውን አፍራሽ ትችቶች በመቀነስ በተለይም ወጣት ተጫዋቾች ላይ የሚፈጠረውን የሳይበር ጫና መከላከል እና አዎንታዊ የሆኑ አነቃቂ መልዕክቶችን ማሰራጨት የዲጂታል ማኅበረሰቡ ትልቅ ኃላፊነት ነው። ቡድኑ ሲያሸንፍም ሆነ ሲሸነፍ የማያቋርጥ ድጋፍ በመስጠት የተጫዋቾችን ወኔ ማደስ ከደጋፊዎች የሚጠበቅ ተግባር ነው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


