በሻንጣ ውስጥ የተገኘው የዓዞ ጭንቅላት

0
46

በጣሊያን ሰሜን ምእራብ የቱሪን የፋይናንስ ፖሊስ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች በካሴል ዓየር ማረፊያ ባደረጉት  ፍተሻ በተጓዠ ሻንጣ        ውስጥ የዓዞ ጭንቅላት ማግኘታቸውን ዩፒአይ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምነት አስነብቧል፡፡

የቁጥጥር ባለሙያዎቹ እና የአውሮኘላን ማረፊያ ኃላፊዎች በተጓዡ ቦርሳ ውስጥ በተራ ወረቀት የተጠቀለለ የተቆረጠ የዓዞ ጭንቅላት ካገኙ በኋላ በግለሰቡ ላይ ጥብቅ ምርመራ እያደረጉ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡ ተጓዡ በቱርክ ኢስታንቡል በኩል ከሚያሚ እንደመጣም ነው ያረጋገጡት፡፡

የጣሊያን የፋይናንስ ፖሊስ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ከጉምሩክ ባለስልጣናት ጋር ለአደጋ የተጋለጡ የእንስሳት ዝርያዎች ንግድ እና ዝውውር ጥበቃ ላይ ተጨማሪ ፍተሻ ማድረጋቸውንም ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡  ለዚህም  በ1973 እ.አ.አ በአሜሪካ ዋሽንግተን ለአደጋ የተጋለጡ እፅዋት እና እንስሳትን ከህገወጥ ንግድ ለመጠበቅ በተደረሰው ስምምነት መሰረት  መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

የፍተሻ እና ቁጥጥር ባለሙያዎቹ ተጓዡ የተሳቢውን እንስሳ የተቆረጠ ጭንቅላት አድርቆ በመጠቅለያ ወረቀት መጠቅለሉ ከመነሻው ሀገር በፍተሻ  ባለሙያዎች እንዳይያዝ ሆን ብሎ አስቦበት ለማምለጥ የፈፀመው መሆኑን እንደሚያመላክትም ነው በመግለጫው ያሰመሩበት፡፡

በተጓዡ ላይ በመካሄድ ላይ ያለው ምርመራ ተጠናቆ ጥፋተኛነቱ በህግ ሲረጋገጥ በገንዘብ ከ20 ሺህ እስከ 200 ሺህ ዩሮ ወይም ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት እስር ሊወሰንበት እንደሚችል በማጠቃለያነት ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here