የኢትዮጵያ ፈተና

0
43

ቢጣ አል-ኢስላሚያ፦ የኤርትራ ወደ እናት ሀገር መመለስ እና የአንድነት ፈተና እንደ  መነሻ ፦

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣር በታህሳስ 1946 ዓ.ም በከረን ከተማ የራቢጣ አል-ኢስላሚያ (የኤርትራ ሙስሊሞች አንድነት ማህበር) መመስረት ከኢትዮጵያ የታሪክ፣ የባህል እና የጂኦፖለቲካ ጥቅም አንጻር ቀጥተኛ ፈተና ይዞ ብቅ ያለ የመጀመሪያው የፖለቲካ ክስተት ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተምን እና የፋሽስት ጣሊያን የ50 ዓመታት የቅኝ ግዛት አገዛዝ ማብቃትን ተከትሎ ኤርትራ በእንግሊዝ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ስር ወደቀች። በዚህ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እና የኢትዮጵያ መንግሥት የጣሊያን ቅኝ ግዛት ያላቀቃትን ኤርትራን “ታሪካዊ ግዛታችን እና የባህር በር መተንፈሻችን ናት” በሚል ከእናት ሀገር ጋር ለመቀላቀል ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረጉ ነበር።

በኤርትራ ውስጥ በአብዛኛው የደጋማው ክፍል ክርስቲያን ማህበረሰብ ይደገፍ የነበረው “የአንድነት ፓርቲ” ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትቀላቀል በፅኑ ሲታገል። ራቢጣ አል-ኢስላሚያ ግን ይህንን ንቅናቄ በግልጽ ተቃወመ። ይህም የኢትዮጵያን የታሪክ ጥያቄ እና የታላቋን ኢትዮጵያ አንድነት የመጠበቅ ህልም አደጋ ላይ የጣለ ነበር። ድርጅቱ ኤርትራ ሙሉ በሙሉ እንድትገንጠል ወይም በእንግሊዝ ሞግዚትነት ስር እንድትቆይ መሟገቱ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን እና ቀይ ባህር ላይ ያላትን ስልታዊ የበላይነት ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ የፖለቲካ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር። ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) እ.አ.አ በ1950 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል መወሰኑ የኢትዮጵያን ስልታዊ የባህር በር ጥያቄ ለጊዜውም ቢሆን መፍትሔ ሰጥቶት ነበር።

የጀበሃ የትጥቅ አመፅ መፈጠር እና የሉዓላዊነት መሸርሸር ፦

እ.አ.አ ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ የተተገበረው የኢትዮ-ኤርትራ ፌዴሬሽን ብዙም አልዘለቀም። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት የኤርትራን የራስ ገዝ መብቶች፣ የራሷን ባንዲራ፣ ፓርላማ እና ቋንቋዎችን ደረጃ በደረጃ መሸርሸር ጀመረ። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጋዜጦች ታገዱ፤ የተቃውሞ ሰልፎችም በኃይል ተጨቆኑ። ይህ የፌዴሬሽኑ መፍረስ ሂደት እ.አ.አ በ1962 ኤርትራ የኢትዮጵያ 14ኛ ክፍለ ሀገር ሆና በይፋ ተጠቃለለች፡፡

በዚህ ድባብ በካይሮ (ግብፅ) በስደት ይኖሩ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች እ.አ.አ በሐምሌ 1960 ዓ.ም ጀበሃን (የኤርትራ ነፃነት ግንባር – ELF) መሰረቱ። ጀበሃ ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ወደ ወታደራዊ የትጥቅ ትግል ያሸጋገረ ቀዳሚ ድርጅት ሆነ። ድርጅቱ ከተመሰረተ ከአንድ ዓመት በኋላ መስከረም አንድ ቀን 1961 እ.አ.አ ሐሚድ እድሪስ ዓዋቴ በአዳሉ ተራሮች ላይ የመጀመሪያውን ጥይት በመተኮስ የኤርትራን የ30 ዓመት የትጥቅ ትግል በይፋ አስጀመረ ሲሉ “የኤርትራ ጉዳይ” በሚለው መጽሐፋቸው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር ጀበሃ የሉዓላዊነት ደህንነት ስጋት ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ጀበሃ የጀመረው የትጥቅ አመፅ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ለረጅም ዓመታት በኤርትራ ምድር ላይ እንዲጠመድ አድርጓል። ሀገሪቱ ለልማት እና ለዜጎቿ የኑሮ መሻሻል ማዋል የነበራትን ውስን የኢኮኖሚ አቅም ወደ ጦርነት ግንባር እንድታፈስ አስገድዷታል። በተጨማሪም ጀበሃ የአረብ ሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት ሲል የኤርትራን ጥያቄ “የአረብ እና የእስልምና ማንነት ጥያቄ” አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረሩ የውጭ ኃይሎች (በተለይም የግብፅ እና የሌሎች የአረብ ሀገራት) በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ እና የኢትዮጵያን አንድነት ለማዳከም ምቹ በር ከፍቷል ሲሉ ሪቻርድ ፓንክረስት “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፦ በሰነድ የተደገፈ መልክዓ-ምድር” (“Ethiopia and Eritrea: A Documentary Geography”) በተሰኘው መጽሐፋቸው ያስረዳሉ።

የሻቢያ (EPLF) የአንድነት መፍረስ እና የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት ፦

ጀበሃ በፍጥነት የህዝብ ድጋፍ ማግኘት የቻለ ቢሆንም ድርጅቱ በትግሉ ሜዳ ላይ የተሰለፉትን ክፍሎች በሃይማኖት፣ በጎሳ እና በክልላዊ ስሜት ከፋፍሎ ያስተዳድር ስለነበር በጦርነቱ ውስጥ ጠንካራ ብሔራዊ አንድነት መፍጠር አልቻለም። በዚህ የጀበሃ አመራር አካሄድ በውስጥ ክፍፍሉ እና በሃይማኖታዊ ፖለቲካው ቅር የተሰኙ በርካታ ወጣቶች እና ክርስቲያን የነበሩ የትግሉ አባላት (ኢሳይያስ አፈወርቂን ጨምሮ) እ.አ.አ ከ1970 – 1973 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተገንጥለው በመውጣት ሻቢያን (የሕዝባዊ ግንባር ሐርነት ኤርትራ – EPLF) መሰረቱ።

ሻቢያ ከቀድሞው ድርጅት ጀበሃ ፈጽሞ የተለየ የትግል ስትራቴጂ እና ርዕዮተ-ዓለም ይዞ ብቅ አለ። ድርጅቱ ማህበራዊ ለውጥን ከብሔራዊ ነፃነት ጋር አቆራኝቶ የያዘ፣ ፍፁም ዓለማዊ (Secular) የሆነ እና በጎሳ ወይም በሃይማኖት ሳይከፋፈል ሁሉንም ኤርትራዊ በአንድ ብሔራዊ ዓላማ ስር ያስተባበረ ነበር። በ1970ዎቹ መገባደጃ እና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጀበሃ እና በሻቢያ መካከል የነበረው የኃይል የበላይነት ፉክክር ወደ ከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት አመራ። በዚህ ጦርነት ሻቢያ ይበልጥ የተደራጀ እና ጠንካራ ማዕከላዊ ዕዝ የነበረው በመሆኑ ጀበሃን ሙሉ በሙሉ በማዳከም ወደ ሱዳን ድንበር ገፋው።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና አንድነት አንጻር ሲታይ የሻቢያ መፈጠር እና መጠናከር እጅግ አስከፊውን እና ዘላቂውን ታሪካዊ ጠባሳ የጣለ ክስተት ነው። ሻቢያ ይዞት የመጣው ዘመናዊ እና ቆራጥ ወታደራዊ መዋቅር የኢትዮጵያን የጦር ኃይል (ደርግን) በተከታታይ ጦርነቶች በመርታት በግንቦት 1991 እ.አ.አ አስመራን ተቆጣጥሮ የኤርትራን መገንጠል እውን አደረገ። ይህ ክስተት የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ድንበር ያፈረሰ እና ለዘመናት የኖረውን የኢትዮጵያን አንድነት በመስበር ትልቅ የታሪክ መለወጫ ሆነ።

በተጨማሪም የሻቢያ ጉዞ ኢትዮጵያን የዓለም ትልቋ የባህር በር የሌላት (Landlocked) ሀገር አድርጓታል። የአሰብ እና የምፅዋ ወደቦችን ማጣት የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የደህንነት ጥቅም ዛሬም ድረስ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። የኢትዮጵያ የወደፊት የኢኮኖሚ ዕድገት በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኝ እንዲሆን አድርጓል። ሻቢያ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ውስጥ ከነበሩ የብሔር የታጠቁ ቡድኖች (ለምሳሌ ከህወሃት እና ኦነግ ጋር) ግንኙነት በመፍጠር የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲዳከም እና ሀገሪቱ በብሔር ፌዴራሊዝም መዋቅር እንድትቀረጽ የራሱን ድርሻ አበርክቷል።

በአጭሩ የራቢጣ አል-ኢስላሚያ ምስረታ የዲፕሎማሲያዊ እና የፖለቲካ አንድነት ፈተና መነሻ ሲሆን የጀበሃ መነሳት ደግሞ ይህንን ፈተና ወደ ደም አፋሳሽ የትጥቅ አመፅ ቀይሮታል። በመጨረሻም የሻቢያ መፈጠር እና መጠናከር የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት በመስበር፣ ሀገሪቱ የባህር በሯን እንድታጣ እና ዘላቂ የጂኦፖለቲካ ስጋት ውስጥ እንድትገባ ያደረገ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ሳምንቱ በታሪክ

ሙከራው

መስከረም 13 ቀን 1969 ዓ.ም በወቅቱ የደርግ አንደኛ ምክትል ሊቀመንበር በነበሩት ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ክስተት ነው። ጥቃቱ የተሰነዘረው ኢትዮጵያን ወደ አምባገንነት እየመሩ ነው በሚል የሞት ቅጣት በወሰነባቸው በኢሕአፓ  የታጠቀ ክንፍ አባላት ነበር፤ መሸመቂያቸውንም በአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም አጠገብ አድርገው ነበር። የመንግሥቱ መኪና ወደ መኖሪያቸው በሚጓዝበት ወቅት ድንገተኛ እና ከባድ ተኩስ ተከፈተባቸው፤ ጠባቂዎቻቸው በሰጡት ፈጣን የአጸፋ ምላሽ እና መንግሥቱ መሬት ላይ ተኝተው በማምለጣቸው በቀኝ እጃቸው ላይ ከደረሰ ቀላል የመቁሰል አደጋ ውጭ ለጥቂት ከሞት ተረፉ።

ይህ የከሸፈው የግድያ ሙከራ በሀገሪቱ ቀጣይ የፖለቲካ ጉዞ ላይ እጅግ ዘግናኝ እና ደም አፋሳሽ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ሻለቃ መንግሥቱ ጥቃቱን የሰነዘሩትን ኃይሎች “የኢምፔሪያሊዝም ተላላኪዎች” በማለት ፈረጁ፤ ክስተቱንም ለራሳቸው የፖለቲካ መጠናከር እና በደርግ ውስጥ ሙሉ ስልጣን ለመጨበጥ ተጠቅመውበታል። ከሁሉ በላይ ግን ይህ አጋጣሚ የደርግ መንግሥት በተቃዋሚዎቹ ላይ ይፋዊ የጦርነት አዋጅ እንዲያውጅ ሰበብ ሆነ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ወጣቶች ያለቁበት የ”ቀይ ሽብር” የጭፍጨፋ ዘመቻ በሀገሪቱ ላይ በይፋ እንዲቀጣጠል በር ከፍቷል ይላል”የቅዠት ጉዞ” (የኢሕአፓ የውስጥ ታሪክ) — በሚል በክፍሉ ታደሰ የተጻፈ መጽሐፍ።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here