ይህች ቀን የመጨረሻዬ ብትሆንስ?

0
163

ሮም በድል አድራጊነቷ በደመቀችበት በጥንቱ ዘመን አንድ የጦር አበጋዝ በወታደራዊ ሰልፍ የከተማዋን አደባባዮች በድል ያቋርጥ ነበር።

ሕዝቡ በአድናቆትና በእልልታ ሲያወድሰው በሠረገላው ውስጥ ከጀርባው የቆመ አንድ ባሪያ በጆሮው በሹክሹክታ ያለማቋረጥ እንዲህ ይለው ነበር፦ “ወደ ኋላህ ተመልከት፤ ሰው መሆንህን አስታውስ፤ ሟች መሆንህንም አትርሳ!”

ይህ ጥንታዊ የሮማውያን ሥርዓት እጅግ አስገራሚ የሆነውን የሰው ልጅ ባሕርይ የሚያሳይ ሕያው ምስክር ነው፡፡

ሰው በስኬት፣ በዝና፣ በሥልጣን እና በቁሳቁስ ሲከበብ የማያልፍ ሕይወት ያለው መስሎ ይታየዋል፤ ከዚህ ድንዛዜ የሚያነቃውና መሬት የሚያስረግጠው ግን ሞት መኖሩን ማስታወስ ብቻ ነው፡፡

የላቲኑ ፅንሰ ሐሳብ “ሜሜንቶ ሞሪ” ፍቺው “ሟች መሆንህን አስታውስ” የሚል ነው፡፡

በዘመናችን ለብዙዎች ሞትን ማሰብ የመከፋት ወይም የጭንቀት ምልክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፤ በጥንታውያን ፈላስፎች፣ በሳይንሳዊ ምርምሮች እና በታላላቅ የጥበብ ሰዎች ዕይታ ግን ሞትን ማስታወስ ሕይወትን በሚገባ ለመምራት የሚያስችል ዋነኛ መመሪያ ነው፡፡

የሮማው ንጉሠ ነገሥትና የስቶይክ ፍልስፍና መምህር የነበረው ማርከስ ኦሬሊየስ “ሜዲቴሽንስ” በተሰኘው ታዋቂ ማስታወሻው ላይ፦ “ከዚህች ሕይወት አሁኑኑ ልትሰናበት ትችላለህ፤ ይህም የምታደርገውን፣ የምትናገረውን እና የምታስበውን ይወስነው” በማለት አስፍሯል፡፡

ኦሬሊየስ ዓለምን የሚያንቀጠቅጥ ሥልጣን በእጁ እያለ እንኳ የሕይወትን አላፊነት እንደ መስታወት በመጠቀም ራሱን ከትዕቢት ለመጠበቅ፣ ፍትሕን ለማስፈን እና ጊዜውን በአግባቡ ለመጠቀም ይተጋ ነበር፡፡

ሞትን የማያስታውስ መሪ ወይም ግለሰብ በቀላሉ ለትዕቢት፣ ለስግብግብነት እና ለራስ ወዳድነት ይጋለጣል፡፡

ሌላኛው ስመ ጥር ፈላስፋ ሴኔካ “ስለ ሕይወት አጭርነት” በተሰኘው ድንቅ ድርሰቱ ላይ እጅግ አስገራሚ እውነታን ያነሳል፤ “ሕይወት አጭር ሆና የተሰጠችን አይደለችም፤ እኛ ግን በከንቱ በማባከን አጭር እናደርጋታለን፡፡”

ሰዎች ገንዘባቸው ወይም ንብረታቸው ሲሰረቅ በብርቱ ይቆጣሉ፤ በዋጋ የማይተመነውንና ተመልሶ የማይገኘውን ውድ ጊዜያቸውን ግን ለከንቱ ጭውውት፣ ለማይረባ ቅናት እና ለይስሙላ ክብር አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡

ሞትን ማስታወስ ግን ይህን የባከነ አካሄድ በመግታት እያንዳንዱን ደቂቃ በንቃት እንድንኖር ያስገድደናል፡፡

በዘመናዊው የሥነ-ልቦና ዓለም ሞትን ማሰብ በሰው ልጅ አእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በጥልቀት ተጠንቷል፡፡ የሥነ-ልቦና ምሁራኑ ሼልደን ሶሎሞን፣ ጄፍ ግሪንበርግ እና ቶም ፒስዚንስኪ የቀረጹት “ቴረር ማኔጅመንት ቲዎሪ” የተሰኘው ጥናት እንደሚያስረዳው፤ ሰዎች ሞትን በፍርሃት ሳይሆን በተረጋጋ ግንዛቤ ሲያስተውሉት ጠባያቸው በጎ ለውጥ ያሳያል፡፡

ተመራማሪዎቹ እንዳረጋገጡት የሕይወትን አላፊነት የሚያስተውሉ ሰዎች ከቁሳዊ ሀብት ይልቅ ለሰብአዊ ግንኙነቶች፣ ለፍቅር፣ ለይቅርታ እና ለደግነት ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡

ሞትን መዘንጋት ሰዎችን ወደ ቁሳቁስ አምልኮና ወደ ውጫዊ ውድድር ሲገፋፋቸው ሞትን ማሰብ ግን ወደ ውስጣዊ ሰላም ይመራቸዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በሕክምናው ዘርፍ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ስትረዳ የቆየችው ብሮኒ ዌር “የሟቾች አምስቱ ታላላቅ ጸጸቶች” በተሰኘው መጽሐፏ የሰዎችን የሕይወት ማጠቃለያ ታሪኮች አጋርታለች፡፡

በምርምሯ መሠረት በሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሰዎች ከሚጸጸቱባቸው ነገሮች ዋነኞቹ፦ “ሌሎች ከእኔ በሚጠብቁት መንገድ ሳይሆን በራሴ እውነተኛ ማንነት ባለመኖሬ፤ ለሥራ ብዬ ከመጠን በላይ በመልፋቴ፣ እንዲሁም ከወዳጆቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ባለመጠበቄ” የሚሉ ናቸው፡፡

ማንም ሰው በመጨረሻው ቅጽበት “ምነው ብዙ ገንዘብ በሰበሰብኩ” ወይም “ምነው ብዙ የቢሮ ሰዓት ባሳለፍኩ” ብሎ አይጸጸትም፡፡ ሞትን ማስታወስ ከእንደዚህ ዓይነት ዘግይቶ ከሚመጣ መሪር ጸጸት ይታደገናል፡፡

የቴክኖሎጂው ፈጣሪ ስቲቭ ጆብስ እ.ኤ.አ በ2005 በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ዝነኛ ንግግር ላይ የ “ሜሜንቶ ሞሪ”ን መርህ ለዘመናችን ትውልድ በሚገባ ገልጾታል፤ “በቅርቡ እንደምሞት ማስታወሴ በሕይወቴ ታላላቅ ውሳኔዎችን ለማድረግ የረዳኝ እጅግ ወሳኝ መሣሪያ ነው፡፡

ምክንያቱም ውጫዊ ግምገማዎች፣ ኩራት፣ የውድቀት ወይም የኀፍረት ፍርሃቶች ሁሉ በሞት ፊት ይረግፋሉ፤ በእርግጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ብቻ ይቀራል፡፡” ጆብስ ሞትን የሕይወት የለውጥ ሞተር አድርጎ ተመልክቶታል፡፡

የሰው ልጅ ሰብዕና የሚፈተነው በሚያጋጥሙት ፈተናዎች ብቻ ሳይሆን ለሕይወት በሚሰጠው ትርጓሜ ጭምር ነው፡፡ ሞትን የሕይወት መመሪያ ያደረገ ግለሰብ የሌሎችን ስሜት አይጎዳም፤ በትዕቢት አይወጠርም፤ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲል ክብሩን አያረክስም፡፡

ምክንያቱም ነገ ይህች ምድር የምትተወው ባዶ ሜዳ መሆኗን ጠንቅቆ ይገነዘባል፡፡ ዛሬ የምንጣላበት፣ ቂም የምንይዝበት፣ ሌሊት እንቅልፍ የምናጣበት እና በጭንቀት የምንዋጥበት አብዛኛው ጉዳይ ከሞት አንጻር ሲመዘን እዚህ ግባ የማይባል ከንቱ ነገር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ይህ መስታወት በየቀኑ በዓይናችን ፊት ሲቀመጥ ግን እውነተኛ ማንነታችንን እንድንመረምር፣ ለበጎ ምግባር እንድንተጋ እና የተረጋጋ ሰብዕና እንዲኖረን ያደርገናል፡፡ ቂምና ቁስልን ቶሎ ይቅር እንድንል የሚያስችለን ትልቁ ኃይል ሟች መሆናችንን መረዳት ነው፡፡

ይህንን የጠራ መስታወት በየማለዳው ፊት ለፊታችን የምናስቀምጠው ከሆነ ለማን እና ለምን እንደምንኖር ግልጽ ይሆንልናል፤ ለቤተሰብ፣ ለጓደኛ እና ለሰብአዓዊነት የሚኖረን ጊዜ ጥራት ይኖረዋል፤ ጊዜያዊ ውዳሴን ሳይሆን ዘላቂ በጎ አሻራን እንድናሳርፍ ይገፋፋናል፤ ለተሰጠን እያንዳንዷ እስትንፋስ ጥልቅ ምስጋና እንዲሰማን ያደርገናል፡፡

ሞት ከፊታችን መቆሙን ማወቅ ሕይወትን እንዳናባክን የሚቀሰቅስ ብርቱ ደወል ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ሕይወትን የሚኖረው ሁልጊዜ በምድር ላይ የሚኖር ይመስል ነው፤ ሥራውን ያዘገያል፣ ፍቅሩን ሳይገልጽ ያድራል፣ ይቅርታ ሳይጠይቅ ዘመናትን ያሳልፋል፡፡

ሟችነታችንን ማስታወስ ግን ዛሬን እንድንኖር፣ አሁን ባለችው ቅጽበት እንድንደሰት እና መልካምነትን ሳናዘገይ እንድንፈጽም ያደርገናል፡፡

ሞትን ማሰብ የመኖርን ጣዕም ያጎላዋል፤ ቀለማቱንም ያደምቃል፡፡ አበቦች ውብ ሆነው የሚታዩን ዘላለማዊ ስላልሆኑ፣ በወቅታቸው ፈክተው ስለሚረግፉ ነው፡፡ እኛም ሕይወታችን ውብ የሚሆነው ውሱን በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ማለዳ ስትነቁ ይህችን ጥያቄ ራሳችሁን ጠይቁ፦ “ይህች ቀን በምድር ላይ የመጨረሻዬ ብትሆን ኖሮ ዛሬ ልሠራው ያሰብኩትን እሠራው ነበር?” መልሳችሁ “አይሆንም” ከሆነ የሆነ ነገር መለወጥ እንዳለበት እወቁ፡፡ ሞትን አትፍሩት፤ ይልቁንም ሕይወታችሁን በደግነት፣ በእውነት እና በጥልቅ ፍቅር ለመምራት እንደ ጠራ መስታወት ተጠቀሙበት፡፡

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here