ሰው ለትንኝ እንዴት ይረታል?

0
225

የሰው ልጅ በታሪኩ ውስጥ ከተጋፈጣቸው እጅግ አጥፊ እና ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩ ጠላቶች መካከል አንዷ በእጅ መዳፍ ውስጥ የምትሸፈነው ትንሽ ክንፍ ያላት ናት – የወባ ትንኝ። በአማራ ክልልም ወባ ለዘመናት የበርካቶች ሕይወት የተቀጠፈበትና የኢኮኖሚ ዕድገት ፈተና ሆኖ ቆይቶቷል። ይህ በሽታ በየወቅቱ መልኩን እየቀየረ፣ መድኃኒቶችንና ፀረ-ትንኝ ኬሚካሎችን እየተላመደ የሚነሳ ቢሆንም፣ በክልሉና በሀገር ደረጃ በሽታውን ፈጽሞ ለማጥፋት የሚደረገው ፍልሚያ አሁንም በከፍተኛ ትግል ውስጥ ይገኛል።

ዛሬ ላይ የሳይንሱ ዓለም አዳዲስ የክትባት ግኝቶችን እና ዘመናዊ የቁጥጥር ስልቶችን ይዞ ወደፊት እየገሰገሰ ባለበት ወቅት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ግን ችግሩ አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የወባ በሽታ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ገዳይ ከሆኑ ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ነው። በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የቅርብ ጊዜ የወባ ዘገባ (World Malaria Report) መሠረት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ240 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የሕመም አጋጣሚዎች የሚመዘገቡ ሲሆን፣ ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ከዚህ አጠቃላይ የበሽታው ስርጭት እና የሞት መጠን ውስጥ ወደ 95 በመቶ የሚሆነው ድርሻ የሚሸፈነው በአፍሪካ አህጉር ሲሆን፣ ይህም በሽታውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት ትልቅ ማነቆ አድርጎታል። ዘርፈ ብዙ ችግር ላለባት አህጉሪቱም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል።

በወባ ምክንያት ከሚሞቱት መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች መሆናቸውን የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል (Centers for Disease Control and Prevention – CDC) መረጃ ያመላክታል።

የዓለም ጤና ድርጅት የ2025 እ.አ.አ ሪፖርት እንዳመላከተው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተላላፊ በሽታዎች (Infectious Diseases) መካከል ወባ ከሳንባ ነቀርሳ (TB) እና ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ (HIV/AIDS) ቀጥሎ ገዳይ በሽታ ነው። በዕድሜ ክልል ሲታይ ደግሞ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ወባ ከግንባር ቀደም ገዳይ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው።

የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያስገነዝቡት በ1940ዎቹ መገባደጃ በጎንደርና አካባቢዋ የወባ ወረርሽኝ በስፋት ተከስቶ ነበር፤ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝም የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ስላልነበር ሰዎችን እንደ ቅጠል ያረግፍ ነበር። በወቅቱ በወረርሽኙ ሳቢያ በቀን እስከ ሰባት ሺሕ የሚደርሱ ወገኖች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይነገራል።

ይህ ታሪካዊ እልቂት ግን ለአንዲት ሀገር የጤና ሥርዓት መወለድ እና ለመላው ዓለም አዲስ የሕዝብ ጤና ፍልስፍና መመንጨት መሠረት ሆነ። ዛሬ ግዙፍ የምርምር ማዕከል የሆነው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የቆላ ድባ ጤና ጣቢያ የተመሠረቱት ከዚሁ ከወባ ወረርሽኝ ጋር በተደረገ የሞት ሽረት ፍልሚያ ምክንያት ነበር።

ወረርሽኙን ለመግታት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ዓለም አቀፍ ትብብር ተፈጥሮ ዘመቻ መጀመሩ ይታወቃል፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ወቅትም ታሪክ ራሱን የደገመ እስኪመስል ድረስ ወረርሽኙ አሁንም የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል። የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕክምና ከተወለደ ሰባት ዐሥርት ዓመታትን ቢያስቆጥርም ወባ ግን ዛሬም የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል።

የቆላ ድባ ጤና ጣቢያ እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አመሠራረት – ከወባ እልቂት የወጣ ብርሃን

በ1940ዎቹ መጨረሻ በደንቢያና በበለሳ የተከሰተው አስከፊ የወባ እልቂት በወቅቱ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የአሜሪካ የልማት ድርጅት (USAID) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በጋራ ባደረጉት ጥናት ሚያዚያ 28 ቀን 1953 (እ.ኤ.አ) የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ። ይህንን ተከትሎም ጥቅምት 04 ቀን 1954 (እ.ኤ.አ) በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የማስተማር ፍልስፍናን የተከተለ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ተቋም (የዛሬው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ) በጎንደር ከተማ ተመሠረተ።

“ሕመምተኛው ወደ ጤና ተቋም እስኪመጣ ድረስ አትጠብቁ፤ የምታገለግለውን ማኅበረሰብ ጤና መጠበቅና በሽታን መከላከል ዋነኛ ኃላፊነትህ በመሆኑ፣ ሁልጊዜም ማኅበረሰቡ መሃል እየተገኘህ ጎብኝ” የሚለው መርህ ደግሞ የተቋሙ መመሥረት መርህ ነበር ይላሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ተመራማሪ እና የሕብረተሰብ አገልግሎት ባለሙያ ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ።

ፕሮፌሰር አምሳሉ ለበኩር እንዳሉት መርሁን ወደ ተግባር ለመለወጥና ተማሪዎችን በቡድን (የጤና መኮንኖች፣ የማኅበረሰብ ነርሶች እና የሳኒቴሪያን ባለሙያዎች) በመስክ ለማሰልጠን የተግባር መለማመጃ ማዕከል አስፈለገ። በዚህም መሠረት ታኅሣሥ 04 ቀን 1949 ዓ.ም በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ የቆላ ድባ ጤና ጣቢያ (የአሁኑ የምሥራቅ ደንቢያ ጤና ጣቢያ) በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ጤና ጣቢያ ሆኖ ተመረቀ።

በወቅቱ ተማሪዎቹ በእግርና በጋማ ከብት እየተጓዙ ደም በመመርመር፣ ሕክምና በመስጠት፣ የትንኝ መራቢያዎችን በማድረቅና ቤቶችን በዲዲቲ (DDT) ኬሚካል በመርጨት ባከናወኑት የተቀናጀ ሥራ ወረርሽኙን መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር ፕሮፌሰር አምሳሉ አስታውሰዋል።

በሽታው ለምን ቀጠለ? – መሠረታዊ ክፍተቶች

በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሀገራት ወባን ከታሪክ መዝገብ እንዳሰናበቱ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል፤ በኢትዮጵያ ግን በሽታው የትውልድ ቅብብሎሽ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ለምን? ስንል ለፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ ጥያቄ አቅርበንላቸዋል።

እንደ ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ ማብራሪያ፤ ላለፉት ሰባት ዐሥርት ዓመታት ወባ ያልጠፋው የሚከተሉትን መሠረታዊ ክፍተቶች በዘላቂነት መዝጋት ስላልተቻለ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳሩ ተግዳሮት እና የአካባቢ ቁጥጥር መላላት፣ የማኅበረሰቡ የባሕሪ ለውጥ እና የትግበራ ክፍተት፣ የመድኃኒት አወሳሰድ መዛባትና የሰውነት መከላከያ አቅም መዳከም፣ የተቋማዊ ትስስር መላላትና የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥር አለመኖር ጫናው እስከዛሬም ችግር ሆኖ እንዲቆይ አድርጎታል፡፡

የክልሉ ወቅታዊ ገጽታ

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዘንድሮው ዓመትም ወባ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች ውስጥ የደራ ወረዳ አንዱ ነው። በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ የወባ ጫና ከፍተኛ ቢሆንም፣ በቅርብ ሳምንታት የታካሚዎች ቁጥር መቀነሱ የሚያበረታታ ምልክት ሆኗል። በ2018 ዓ.ም በወረዳው 97,299 ሰዎች በወባ ተይዘው ሕክምና ማግኘታቸው የችግሩን ስፋት ያሳያል። በ2019 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ሳምንታትም 16,916 ታካሚዎች መመዝገባቸው፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ሳምንት ጋር ሲነጻጸር የ12 ነጥብ አምስት በመቶ ጭማሪ መኖሩን የደራ ወረዳ የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አወጣ ተፈራ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአንድ ሳምንት 3,097 የነበረው የታካሚ ቁጥር በአሁኑ ወቅት መቀነሱ የቁጥጥር ሥራዎች ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን ያመላክታል። የጤና ተቋማትን ሳያቋርጡ ማስኬድ፣ የመድኃኒትና የምርመራ ግብዓት አቅርቦትን ማረጋገጥ፣ የቤተ ሙከራ አቅምን ማጠናከር እና የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማጽዳት ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል ናቸው።

“የታካሚዎች ቁጥር መቀነስ የወባ ስጋት አብቅቷል ለማለት አያስችልም” ያሉት ባለሙያው በተለይ የዝናብና የአካባቢ ሁኔታዎች ለትንኝ መራባት አመቺ ከሆኑ ጫናው እንደገና ሊጨምር እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል በተለይም በምዕራባዊ ክፍሎች የወባ ጫና አሁንም ከፍተኛ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ገልጸዋል። በተለይ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ፣ ሰሜን ጎጃም፣ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የበሽታው ጫና የሚታይባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ተጠቅሷል። በወረዳ ደረጃ ደግሞ ደራ ወረዳ ከፍተኛ ጫና ካላቸው አካባቢዎች መካከል ቀዳሚ መሆኑ ተገልጿል።

መውጫ መንገዶች

በባሕር ዳር ከተማ የወባ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ ሲነሳ፣ የግንባታ ቦታዎች መስፋፋት እና ለውሃ ማጠራቀሚያ የተሠሩ የኮንክሪት ታንከሮች በአግባቡ አለመያዛቸው እና የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች አለመሸፈናቸው ለትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠሩ አስተባባሪው ጠቅሰዋል። ይህ ችግር የወባ መከላከል ሥራ የጤና ቢሮ ብቻ የሚፈጽመው ሥራ እንዳልሆነ ያሳያል። የከተማ አስተዳደር፣ የግንባታ ዘርፍ፣ የውሃ አጠቃቀም እና ኅብረተሰቡ በጋራ የሚሳተፉበት የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እንደሚያስፈልግ አቶ ዳምጤ ላንክር አብራርተዋል።

ከ70 ዓመታት የሽንፈት አዙሪት ለመውጣት የታሪክን ስኬታማ ገጾች መልሶ መክፈት ግድ ይላል። ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ እንደሚሉት፣ ወባን ለመቆጣጠር ብሎም ለማጥፋት የሚከተሉት የተቀናጁ እርምጃዎች መተግበር አለባቸው፦

  • ወደ ማኅበረሰቡ ሂድ የሚለውን መርህ ማደስ፦ የጤና ባለሙያዎች ታካሚ ወደ ተቋም እስኪመጣ በቢሮ ተቀምጠው ከመጠበቅ ይልቅ፣ ልክ እንደ ቀደሙት አበው ወደ ማኅበረሰቡ ዘልቀው በመግባት የትንኝ መራቢያ ረግረጋማ ቦታዎችን የማድረቅና የማፋሰስ ሥራን በዘመቻ ሊመሩ ይገባል።
  • የሕክምና ታማኝነት እና ግንዛቤ፦ ኅብረተሰቡ የትኩሳትና የማንቀጥቀጥ ስሜት ሲሰማው በአፋጣኝ ተመርምሮ የታዘዘለትን መድኃኒት በአግባቡ እስከ መጨረሻው እንዲወስድ እና አጎበርን ያለመሰልቸት እንዲጠቀም የማያቋርጥ የባሕሪ ለውጥ ትምህርት መስጠት።
  • የተቀናጀ የወረዳዎች ጥምረት፦ በክልሉ ያሉ አዋሳኝ ወረዳዎች በተመሳሳይ ሳምንት የሚከናወን ወጥ የኬሚካል ርጭትና የአካባቢ ጽዳት ዘመቻ በጋራ ሊመሩ ይገባል።
  • የምርምርና የተግባር ዳግም ውህደት፦ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና የቆላ ድባ ጤና ጣቢያ ታሪካዊ ቁርኝታቸውን በማደስ፣ የወባ ትንኝ ፀባይን እና የመድኃኒት መላመድን የተመለከቱ ወቅታዊ ምርምሮችን በቀጥታ ከመስክ ሥራ ጋር ማስተሳሰር አለባቸው።

“ወባ በሳይንስ የሚታወቅ፣ መከላከያውና መድኃኒቱ በእጃችን ያለ በሽታ ነው። ከሰባት አሥርት ዓመታት በኋላም ከወረርሽኙ መላቀቅ  ያልተቻለው በዕውቀት ማነስ ሳይሆን ቁርጠኛ ሆነን መፍትሔዎችን ባለመተግበራችን ነው። አሁን ግን መዘናጋቱ የሚያበቃበት ጊዜ ደርሷል፤ ወባን ለማጥፋት የትናንቱን ታሪክ መሠረት አድርገን ዛሬ በጋራ ልንነሳ ይገባል” ሲሉ ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ በአጽንኦት ይናገራሉ።

በቀጣይም የዝናብ ወቅት ከመጠናቀቁ ጋር ተያይዞ በመስከረም መጨረሻ፣ በጥቅምትና በኅዳር አካባቢ የወባ ሥርጭት ሊጨምር እንደሚችል የክልሉ ጤና ቢሮ የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ገልጸዋል። ስለዚህ አሁን የሚታየው መሻሻል (መቀነስ) የመከላከያ ሥራዎችን ለመቀነስ ምክንያት ሳይሆን ቁጥጥሩን ለማጠናከር ዕድል ሊሆን ይገባል። በአካባቢ የትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማጥፋት ሥራን ማጠናከር፣ የቤት ውስጥ የኬሚካል ርጭት፣ የሕክምና እና የመድኃኒት አቅርቦት እንዳይቆራረጥ ማድረግ እንዲሁም ኅብረተሰቡን በመከላከል ሥራዎች ላይ በንቃት ማሳተፍ ወሳኝ ናቸው።

በተጨማሪም የወባ ምልክት የሚሰማው ሰው በፍጥነት ወደ ቅርብ የጤና ተቋም ሄዶ ምርመራና ሕክምና ማግኘቱ የበሽታውን ጫና ለመቀነስ እንደሚያግዝ አቶ ዳምጤ ላንክር አስገንዝበዋል።

በአማራ ክልል የወባ ሥርጭት መቀነሱ አዎንታዊ ለውጥ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ጫና ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸው እና ሥርጭቱ ወቅታዊ ባሕሪይ ማሳየቱ ችግሩ አሁንም ትኩረት እንደሚፈልግ ያሳያል።

የወባ ቁጥጥር ከመድኃኒት አቅርቦትና ከሕክምና አገልግሎትን ባለፈ የአካባቢ ንጽህና፣ የውኃ አያያዝ፣ የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና የጤና ተቋማት ዝግጁነት በአንድ ላይ የሚገናኙበት ጉዳይ ነው። በመሆኑም በሚቀጥሉት ወራት የወባ ጫና እንዳይጨምር ሁሉም የድርሻውን በመወጣት የወባን ስርጭት መግታት ይገባል።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here