ዘንገና

0
26

 ዘንገና ሐይቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት እጅግ አስደናቂ፣ ውብ እና ምስጢራዊ የተፈጥሮ ቦታዎች አንዱ ነው። ይህ አስደናቂ ሐይቅ የሚገኘው በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ውስጥ በምትገኘው በባንጃ ወረዳ (ከእንጅባራ ከተማ ወጣ ብሎ) ነው። ዘንገና ተራራማ በሆነ ቦታ ላይ የሚገኝና ፍጹም ክብ ቅርጽ ያለው የክሬተር ሐይቅ ነው (ክሬተር ሐይቅ ማለት ከብዙ ዓመታት በፊት በአካባቢው የነበረ እሳተ ገሞራ ፈንድቶ ከቆመ በኋላ በፍንዳታው ምክንያት በተፈጠረው ጥልቅ እና ክብ ጉድጓድ ውስጥ የዝናብ ውኃና የከርሰ ምድር ውሃ በመከማቸት የሚፈጠር የሃይቅ ዓይነት ነው)፡፡ ዘንገና ሐይቅ የተፈጠረውም ከብዙ ዓመታት በፊት በፈነዳ የእሳተ ገሞራ ጉድጓድ ውስጥ ውኃ በመተኛቱ ነው። ከላይ ሆኖ ለሚመለከተው ሰው ጥቅጥቅ ባለ ጫካ መካከል የተቀመጠ ትልቅ እና ክብ አረንጓዴ መስተዋት ይመስላል።

ሐይቁን ለየት የሚያደርገው በለምለም እና ጥንታዊ በሆኑ አረንጓዴ ዛፎች መከበቡ ነው። እነዚህ ዛፎች ለብዙ ዘመናት የቆዩ እና አካባቢው ሁልጊዜ ቀዝቃዛና ንጹሕ አየር እንዲኖረው ያደረጉ ናቸው። በዛፎቹ ላይ የተለያዩ የሚያማምሩ ወፎች እና ትናንሽ ጦጣዎች ይኖራሉ። ወደዚህ ሐይቅ የሚሄዱ ልጆች የተፈጥሮን ውበት በቅርበት ማየት፣ የወፎችን ጣፋጭ ዝማሬ ማዳመጥ እና በጫካው ውስጥ እየተዘዋወሩ መጫወት ይችላሉ። የሐይቁ ውኃ በጣም ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ በውስጡ አስደናቂ የሆኑ የውኃ ፍጥረታት እና አሳዎች ይኖሩበታል።

ለልጆች ዘንገና ሐይቅን መጎብኘት ታላቅ የመዝናኛ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ስለ እሳተ ገሞራ አፈጣጠር፣ ስለ ዕፅዋት እና ስለ አካባቢ ጥበቃ ጠቃሚ ትምህርት የሚያገኙበት ክፍት የተፈጥሮ ሳይንስ መማሪያ መድረክ ነው። በአካባቢው ያሉ አባቶችም ሐይቁ እንዴት እንደተፈጠረ ለልጆች የሚነግሩት የሚስብ ጥንታዊ ተረት እና ታሪክ አላቸው። በሃይቁ ዙሪያ ከቤተሰብ ጋር በሰላም ለመጫወት እና የማይረሳ ትዝታ ለመሰብሰብ ዘንገና ፍጹም ቦታ አንደሆነ ከአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተረት

ዝንጀሮዎቹ

በአንድ ወቅት በአዋሽ ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ በርካታ ዝንጀሮዎች ነበሩ። እነዚህ ዝንጀሮዎች በቡድን የተከፋፈሉና ዘወትር እርስ በርሳቸው የሚጣሉ እና አንዱ የያዘውን ሌላው ለመንጠቅ የሚዋጉ ነበሩ። በመካከላቸው ምንም ዓይነት ሰላምና መተማመን አልነበረም።

አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ በድንገት ከባድ ዝናብ ዘንቦ ወንዙ ሞላ። የጎርፉ መነሳት ያስፈራቸው ዝንጀሮዎች በየፊናቸው እየሮጡ በአቅራቢያቸው ወደነበሩት ትላልቅ ዛፎች ላይ ወጡ። ጎርፉ ግን እየበረታና እየጨመረ መጣ። በመጨረሻም ዝንጀሮዎቹ የወጡባቸው ዛፎች በጎርፉ መሃል ተከበቡ።

ከዛፎቹ አንዱ በጎርፉ ኃይል መናወጥና መነቀል ጀመረ። በዚያ ዛፍ ላይ የነበሩት ዝንጀሮዎች መጮኽና “እርዱን” ማለት ጀመሩ። በሌላኛው ጠንካራ ዛፍ ላይ የነበሩት ዝንጀሮዎች ግን መጀመሪያ ላይ «ይገባቸዋል! ድሮም እኛን አይወዱንም ነበር» በማለት ሊሳለቁባቸው ሞከሩ።

ነገር ግን የዛፉ መውደቅ ቅርብ መሆኑንና ጎርፉ ሁሉንም ሊያጠፋቸው እንደሚችል የተረዳ አንድ አንጋፋ ዝንጀሮ እንዲህ ሲል ጮኸ፦ «ወገኖቼ! ዛሬ እነሱ ከጠፉ ነገ ተራው የእኛ ነው። ጥላቻችንን ትተን እጃችንን ካልዘረጋንላቸው ሁላችንም እንሰምጣለን!»

በዚህ ጊዜ ዝንጀሮዎቹ ካለፈው ጠባቸው ይልቅ ህይወታቸው እንደሚበልጥ ተረዱ። ጠንካራው ዛፍ ላይ የነበሩት ዝንጀሮዎች እርስ በርሳቸው እጅና እጅ በመያያዝ ረዥም ሰንሰለት ሰሩና ወደ ሚወድቀው ዛፍ ተዘረጉ። በጭንቅ ላይ የነበሩት ዝንጀሮዎችም የተዘረጋላቸውን እጅ በመያዝ ወደ ማይወድቀው ዛፍ ተሻገሩ። ዛፉ ተነቅሎ በጎርፍ ሲወሰድ ሁሉም ዝንጀሮዎች በአንድነት ተረፉ።

ከዚያ ቀን ጀምሮ ዝንጀሮዎቹ መጣላታቸውን ትተው «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» የሚለውን የኢትዮጵያውያን የጥበብ አባባል በተግባር ተረድተው በአንድነት መኖር ጀመሩ ይባላል።

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ የቃል ሥነ-ጽሑፍ

ሞክሩ

  1. አንድ ዛላ አደይ አበባ ስንት ክፍልፋይ አላት?

መልስ፡- ስምንት

  1. ዞራ ዞራ ራቷ ጥፊ ምንድን ናት?

መልስ፡- ወንፊት

  1. በኢትዮጵያ ትልቁ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ማን ይባላል?

መልስ፡- ንጋት ሐይቅ (በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተፈጠረ)

ነገር በምሳሌ

-«ታጥቦ ጭቃ»፦ አንድን ስህተት ደጋግሞ መሥራትን ወይም ድካምን ከንቱ የሚያደርግ የማይረባ ተግባር መፈጸምን ይገልጻል።

-«የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር»፦ አንድ ሰው በሚስጥር የሚያወራውን ነገር እንኳ ቢሆን አመክንዮአዊና ተአማኒነት ያለው ካልሆነ ለሰው ማካፈል እንደሌለበትና ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያሳስባል።

– «የማያቁት ሀገር አይናፍቅም»፦ አንድ ሰው አይቶት ወይም አጋጥሞት የማያውቀውን ነገር ሊመኘው ወይም ሊናፍቀው እንደማይችል ያመለክታል።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here