የመስቀል ወፍ ከየት ነው ምትመጣው?

0
47

የጨለማው ክረምት ድቅድቅ ደመና ተገፎ የብርሃኑ መስከረም ሰማይ ሲከፈት ከተፈጥሮ ጓዳ ድንገት ብቅ የምትለው የመስቀል ወፍ በክንፎቿ ላይ የቀለማትን ውበት ብቻ ሳይሆን የታደሰ ሕይወትን ተስፋ ይዛ ትመጣለች፡፡

ይህች ፍጡር ከአደይ አበባ ቢጫ ምንጣፍና ከመስቀል ደመራ በዓል ጋር ያላት ትስስር ተራ ወቅታዊ ክስተት ሳይሆን በሥነ ጽሑፍ፣ በሥዕል እንዲሁም በአፈ ታሪክ ውስጥ ጥልቅ ተምሳሌት ያላት ሕያው ምልክት ናት፡፡

በኢትዮጵያ ምድር መስከረም ሲጠባ የተፈጥሮ ለውጥ ከሰው ልጆች መንፈሳዊ ጉዞ ጋር ተዋሕዶ አዲስ ራእይና ተስፋ ይፈነዳል፡፡

በሳይንሳዊው እውነታ የመስቀል ወፍ ከየት እንደመጣች ሳይታወቅ በመስከረም ብቻ ብቅ የምትል እንግዳ ፍጡር አይደለችም፤ ዓመቱን ሙሉ እዚሁ ምድራችን ውስጥ ትኖራለች፡፡

ጆን አሽ እና ጆን አትኪንስ ባዘጋጁት “የኢትዮጵያና ኤርትራ አእዋፋት” በተሰኘው የምርምር መጽሐፍ መሠረት የመስቀል ወፍ “ዩፕሌክተስ” በሚባለው የአእዋፍ ወገን ሥር የምትመደብ ናት።

በተለይም ቀይ አንገቷ ወፍና ደማቅ ቀይዋ ወፍ በመባል ትታወቃለች፡፡ ወንዶቹ ወፎች በክረምት ወቅት ደብዛዛ ቡናማ ላባ ለብሰው በሳር ውስጥ ይደበቃሉ፤ በመስከረም ወቅት ግን ለመራባት ሲዘጋጁ አሮጌው ላባቸው ረግፎ እጅግ የሚያምር ደማቅ ጥቁርና ቀይ ካባ ያበቅላሉ፡፡

ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ክስተት ከእጽዋት ልምላሜ፣ ከእሸት መድረስና ከአደይ አበባ መፈንዳት ጋር በትክክል ይገጥማል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ቤት ደግሞ የመስቀል ወፍ መገለጥ ከመስቀሉ መገኘት ምስጢር ጋር በቅኔ ተዛምዶ ይተነተናል፡፡

ሊቃውንቱ ንግሥት ዕሌኒ የከበረውን የክርስቶስ መስቀል ከቆሻሻ መሬት ቆፍራ ማውጣቷንና የመስቀል ወፍ በክረምት ተሰውራ ቆይታ በመስከረም ውበቷን መግለጧን በጉባኤ ቃና ቅኔ በሚከተለው ስንኝ አነጻጽረውታል፦

“ከመ ዕሌኒ ንግሥት ዘአስተርአየት ዕፀ መስቀል ክቡረ፤ ዖፈ መስቀል በፀደይ አግሀደ ወአብርሀ ኅብረ” በማለት ተቀኝተዋል፡፡

የቅኔው ሰም መስቀል ወፍ በመስከረም ወቅት አምራና ተውባ ደማቅ ቀለሟን ማሳየቷ ሲሆን፤ ወርቁ ደግሞ ለዘመናት ተቀብሮ የነበረው መስቀል በዕጣን ጢስና በጸሎት ተፈልጎ ተገኝቶ ለዓለም ሁሉ የነጻነትና የበረከት ብርሃን መሆኑን ያመለክታል፡፡

በዘመናዊው ሥነ ጽሑፍ ውስጥም ደራሲያን የመስቀል ወፍንና የአደይ አበባን ተፈጥሯዊ መመሳጠር በስፋት አንስተውታል፡፡ አንጋፋው ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ

“የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ

ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፤

ማን ያውቃል?”

በማለት የተፈጥሮን ድንቅ ሥርዓትና የጊዜ ጠባቂነት በተጠየቃዊ ውበት ገልጸውታል፡፡

በሕዝባዊ ባህልም ውስጥ ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው አልፎ አልፎ ብቅ የምትለውን ውድ ፍቅረኛውን በመስቀል ወፍ እየመሰለ ፦

“የመስቀል ወፍ እና አንቺ ልጅ ያው ናችሁ፤

በዓመት አንዴ ብቻ ብቅ ትላላችሁ”

ሲል ያንጎራጎረው የዚሁ ማኅበራዊ ፋይዳ ማሳያ ነው፡፡

የታሪክና የባህል ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሚያትቱት የቀለማት አጠቃቀም በቤተ ክርስቲያን ሥነ ጥበብ ውስጥ ምስጢራዊ መልእክት አለው።

ጥቁሩ ቀለም የዓለምን ጨለማና የሰው ልጅ የኃጢአት ባርነት ሲወክል ደማቁ ቀይ ላባ ደግሞ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን የክርስቶስን ቤዛዊ ደም እና የድል አድራጊነት ብርሃን ያመለክታል፡፡

ሠዓሊያን በሸራና በብራና ላይ የመስቀል ወፍን ከቢጫው የዓደይ አበባ ጎን ለጎን ሲያሰፍሩ ተመልካቹ የመስከረምን ለምለም ድባብ፣ የበዓሉን ፍሥሐ እንዲሁም የተፈጥሮን ጸጋ በአይነ ኅሊናው እንዲያስተውል በር ይከፍቱለታል፡፡

በኮምዩኒኬሽን ሳይንስና በምልክት ጥናት ንድፈ ሐሳብ የመስቀል ወፍ የቃል አልባ ተግባቦት ኃያል ተምሳሌት ናት፡፡

ኧርነስት ካሲረር “የተምሳሌታዊ ቅርጾች ፍልስፍና” በተባለው መጽሐፉ የሰው ልጅ ዓለምን በምልክቶች እንደሚረዳ እንደገለጸው ሁሉ ኡምበርቶ ኤኮ እና ሮላንድ ባርትስም ማኅበረሰቦች ለተፈጥሮ ምልክቶች ባህላዊ ትርጉም በመስጠት የጋራ ትውስታቸውን እንደሚገነቡ ያረጋግጣሉ፡፡

የመስቀል ወፍም ለኢትዮጵያውያን ያለ ድምፅ የምታስተላልፈው ጽኑ መልእክት አለ፤ እርሱም መከራ ጊዜያዊ መሆኑን፣ ከክረምት በኋላ ብርሃን እንደሚመጣ እንዲሁም ተስፋ መቼም ቢሆን እንደማይጠፋ ነው፡፡

ይህ ግንኙነት በሕዝቡ ዘንድ የጋራ መረዳዳትን፣ ይቅር ባይነትንና ሰላማዊ አብሮነትን ያጎለብታል፡፡

በተጨማሪም የመስቀል ወፍ ከመስከረም ወር ጋር ያላት ውሕደት አካባቢያዊና ሥነ ምኅዳራዊ እሴቷን በጉልህ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን እንደሚያስገነዝበው ወፏ በሳር ምድርና በሸለቆዎች ውስጥ መራባቷ የተፈጥሮ ብዝኀ ሕይወት ጤናማ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሥነ ምኅዳራዊ መለኪያ ነው፤ ሥነ ምኅዳሩ ካልተጠበቀ የወፏ መራባትም ሆነ የተፈጥሮ ለውጡ ይዛባል፡፡

ስለዚህ ይህችን ወፍ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥዕልና በቃል ትውፊት ውስጥ ማክበር ማለት ተፈጥሮን የመንከባከብ ባህልን ማሳደግ ጭምር ነው፤ ምክንያቱም ተፈጥሮ ከተጎዳ የመስከረም ወር ለምለም ድባብ አብሮ ይጠፋልና፡፡

በአጠቃላይ የመስቀል ወፍ ለኢትዮጵያውያን ተራ የወፍ ዝርያ ሳትሆን የጥበብ፣ የታሪክና የማንነት ዘመን ተሻጋሪ ድንቅ ማሰሪያ ናት፡፡

በሳይንሳዊው ዓለም የመራቢያ ወቅቷን ጠብቃ ላባዋን የምትቀይር የተፈጥሮ ተዓምር ስትሆን፤ በቤተ ክርስቲያን ቅኔ ደግሞ ከመስቀሉ ምስጢር ጋር የተዛመደች የድልና የተስፋ አብሳሪ ናት፡፡

በመንግሥቱ ለማ  ብዕር ከአደይ አበባ ጋር ቀጠሮ ያላት የታማኝነት ምልክት ተደርጋ ስትወደስ በባህላዊ ሥዕሎቻችን ውስጥ ደግሞ የቤዛነትና የብርሃን ንግሥት ሆና ተሥላ ትኖራለች፡፡

ይህች ድንቅ ፍጡር የውጪያዊ ውበት መገለጫ ብቻ ሳትሆን የሰው ልጅ መንፈስ ሁልጊዜም ከመከራ ጨለማ ወጥቶ በአዲስ ተስፋ የመብቃት ጽናት እንዳለው የምታበስር ሕያው የጥበብ ቋንቋ ናት፤ እርሷ በሰማይ ስትበር ምድር በደስታ ትሞላለች፡፡

ስለዚህ መስከረም በጠባ ቁጥር የመስቀል ወፍ የምታመጣውን የተስፋ ብርሃን በልባችን አንግሠን የፍቅር፣ የሰላምና የዕድገት ዘመን እንዲሆንልን የተፈጥሮን ጥሪ በክብር ተቀብለን በአንድነት ወደፊት መጓዝ የሠለጠነ ሕዝብ ዘመን ተሻጋሪ ታላቅ ጸጋ ሆኖ ይኖራል፡፡

ማረፊያ

~የመኖር ትርጉሙ~

የመኖር ትርጉሙ

የእንባ ቅብብል ነው በትውልዶች መሀል

አባትህ ያነባው ላንተም ይደርሰሀል

ሰው የሆንሁ ለታ  ደርሶኛል ይህ አጣ

አልቅሼ አንደገባሁ

አስለቅሼ ልውጣ፡፡

©በዕውቀቱ ስዩም

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here