የመስቀል ሰሞን – ከ‘ጋሽ ቆራጡ ጀግና’ እስከ ‘ሮናልዶ’

0
42

መስከረም የታደለ ወር ነው። መስከረም በአደይ አበባ ታጅቦ፣ በጠራ የወንዝ ውኃ ፉጨት ተመስጦ፣ በመስቀል ወፍ ኑራ ኑራ መገኘት ተሸልሞ እና ወርሃ ጳጉሜን ሽምግልና ተልኮ ይጠባል።

ወይ መስከረም! መገረም ነው ይሄ ሁሉ ሽር ጉድ ለመስከረም የክት ገጠመኙ ሳይሆን የዓመት ዓመት በረከቱ ነው። ደግሞ የአዳም ልጅ ሁሉ መስከረም ሲባል በሃሴት መደንገጡ ከምን የመጣ ነው ቢባል ምን ይባላል? ያው ውዴታ ነው እንጂ ነው መልሱ።

አዲስ ዓመት ጠብቶ ዘመን ሲለወጥ ጠብቆ የመስቀል በዓልም ድንገት ከተፍ ይላል። መስቀል ሲመጣ ደግሞ ምድሯ ሌላ አልባስ ትለብሳለች። የወንዞቹ ድምፅ ይቀየራል፤ የደመናው ሽሽት ይጠፋና የአየሩ ጠረን ሳይቀር በዕጣን እና በደመራ ጭስ ታሽቶ የደስታ እንባ ያነባል። የመስቀል በዓል የምግብ ብቻ ሳይሆን የልብ ማዕድ ነው፤ ጨለማውን በደመራው እሳት አብርቶ፣ ሰዎችን በይቅርታና በፍቅር አቆራኝቶ፣ የማሕበረሰቡን የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባሕል አድሶ የሚያልፍ ታላቅ የጋራ ዕሴት መገለጫ ነው።

ይህንን እና ሌሎች የአውዳመት ትዝታዎች እያመላለስኩ ቡና ለመጠጣት ተሰየምኩ። ጋሽ ብሩክ ከቤቱ በረንዳ ላይ ባለው ረከቦት አጠገብ ከተቀመጡበት ትልቅ የእንጨት ወንበር ላይ ሆነው፣ የቡናዋን ጪስ በዓይናቸው ይከተላሉ። በእጃቸው የያዟት የቡና ስኒ ሙቀትና የእጣን ጠረን ተደባልቆ ከትዝታ ባሕር ውስጥ ያስገባቸው ይመስላል። በዚያ ላይ የሕፃናቱ ሆያ ሆዬ ጨዋታ ቀየውን ያናውጠዋል። ጋሽ ብሩክ ሕፃናቱን ሲመለከቱ ድንገት ፈገግ አሉና በረጅም ትንፋሽ ወደ ኋላ ተመሰጡ። ጋሽ ብሩክ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ነዋሪ የዕድሜ ባለጸጋ አዛውንት ናቸው።

ጋሽ ብሩክ የምንላቸው ካለን አክብሮት የተነሳ ሲሆን ሙሉ ስማቸው ብሩክ ሕብስቱ ይባላሉ፤ ትውውቃችን የቆዬ ነው፡፡ ሁለታችንም ቡና አፍቃሪ መሆናችን ደግሞ ለትውውቃችን መሠረት ጥሎልናል፤ ዛሬም ከጋሽ ብሩክ ጋር የተገናኘነው ቡና ለመጠጣት በተሰየምኩበት ወቅት ነበር፡፡ የዛሬው ሰላምታ ልውውጣችን ግን ከወትሮው የተለዬ ነበር፤ ሕጻናት በሆያ ሆዬ ጭፈራ ለቡና የተሰየምንበትን ቤት ማድመቃቸው ደግሞ ስለ መስቀል ያላቸውን ትዝታ ወደ መለዋወጥ ከፍታ እንዲሸጋር አደረገው፡፡

የሕጻናቱ ጭፈራ የጋሽ ብሩክን የፊት ገጽታ በትዝታ ስሜት አስገባው፤ እኔም ታዲያ የማወቅ ጉጉት አድሮብኝ “ጋሽ ብሩክ፣ ምነው እንዲህ በትዝታ ተዋጡ? ምን ትዝ አለዎት?” ብዬ ጠየቅኳቸው።

ጋሽ ብሩክ በራሳቸው ላይ የደፉትን ባርኔጣ አውልቀው ጉልበታቸው ላይ አስቀመጡት። ከዚያም ያንን በግንባራቸው ላይ ያለውን ጠባሳ እያሳዩኝ፣ በረጋና ማራኪ ድምፃቸው እንዲህ ሲሉ ያጫውቱኝ ጀመር፣ “ልጅ ሆኖ መቼም ‘ሆያ ሆዬ’ ብሎ ያልጨፈረ ‘ዓመት አውዳመቱን ድገመነ’ ብሎ ያልመረቀ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ልጃገረድ ሆና ‘አበባ አየሁሽ’ ብላ ያልዘፈነች፣ ‘ከብረው ይቆዩን ከብረው’ ብላ ያልመረቀች ሴት ትኖር ይሆን ብሎ ማሰብም ይፈትናል።”

ጋሽ ብሩክ ይህንን ሲናገሩ የዓይኖቻቸው ብርሃን ይበልጥ ደመቀ። እኔም ከአንደበታቸው የሚወጡትን ቃላት ውበት ራሴን በመነቅነቅ አድናቆቴን በመግለጽ የመስቀል ሰሞን የልጅነት ትዝታቸውን እንዲያጫውቱኝ ጥያቄዬን አስከተልኩ።

“ያኔ በልጅነታችን የነበረው የእርድ ገጠመኝ ዛሬም ድረስ ትላንት የሆነ ይመስለኛል” አሉ ጋሽ ብሩክ፣ ጺማቸውን እየዳሰሱ። “በደመራው ዋዜማ የቀዬው ሰዎች ተሰባስበን በጋራ በሬ እንገዛለን። ይህም የአንድነትና የማሕበራዊ ትስስር ማሳያችን ነው። የበሬው እርድ አደገኛና አድካሚ እንደመሆኑ፣ ያንን ግዙፍ በሬ ለመያዝ የምናደርገው ግብግብ ደግሞ ሌላ ታሪክ ነበር” በማለት ገጠመኛቸውን አጫወቱኝ።

“አንድ ጊዜ ትዝ ይለኛል፤ ለእርድ የቀረበውን በሬ ለመጣል ጎረምሶች ገመዱን ሲያዘጋጁ በሬው ከእጃቸው አመለጠ! ወጣቱ ሁሉ ያዙት! ያዙት! እያለ በየሜዳውና በየጓሮው ሲሯሯጥ የቀዬው አቧራ ሰማይ ነካ። በሬው በፍርሃትና በቁጣ እያነፈነፈ የአጥር ግንብ ጥሶ ሊያልፍ ሲል፣ እኔ በልጅነት ወኔ ገመዱን ልይዝ ፊቱ ላይ ስቆም የበሬው ቀንዶች አየር ላይ አነሱኝ! ይኸውልህ ይህን ግንባሬን በቀንዱ መትቶ መሬት ላይ ዘረረኝ። ዘመዶቼ ደንግጠው አነሱኝ፣ በሬውንም ጎልማሶቹ ከበው በረጅሙ ገመድ ጠልፈው ያዙት። በመጨረሻም በዕድሜ አንጋፋ በሆኑት አባታችን ተባርኮ ታረደ። ይህ ጠባሳ ያኔ ከበሬው የተቀበልኩት የበዓል ማስታወሻዬ ነው!” አሉ ጋሽ ብሩክ ከፊታቸው ላይ የሚታየውን ጠባሳ እየጠቆሙ በራሳቸው ገጠመኝ እየሳቁ።

ከእርዱ በኋላ ወንዶች ጃኬታቸውን አውልቀው፣ እጅጌያቸውን ጠቅልለው ስጋውን በብልት በብልቱ እንደሚለዩ፣ ‘ቀይ ስጋ’ እና ‘ጮማ’ ተብሎ በፍትሃዊነትና በዕጣ ለሁሉም ተሳታፊዎች እንደሚከፈል፣ በዚህም ሂደት ቀልብ ገዥ የሆኑ ቀልዶችና ጨዋታዎች እንደሚቀርቡ በትዝታ በተዋጠ ደስታ ውስጥ ሆነው ተረኩልኝ።

ጋሽ ብሩክ ስለ ደመራውና ስለ ምሽቱ ደስታ ሲያወጉኝ፣ ድንገት ሌላ ፈገግ የሚያሰኝ ግን ደግሞ የቁጭት ትዝታቸው ትውስ አላቸውና እንዲህ ሲሉ ትረካቸውን ቀጠሉ፤
“አመሻሹ ላይ ሰማዩ በወርቃማ የፀሐይ ወጋገን ሲያጌጥ ደመራው ይደመራል። በማግስቱም እያንዳንዱ ችቦ በእጅ ተይዞ “እንጎሮጎባሽ” ሲባል ጭሱ የተስፋና የብርሃን ምልክት ሆኖ አየር ላይ ይንሳፈፋል። እሳት የጥፋት ሳይሆን የፍቅርና የእርቅ መገለጫ ሆኖ የማውቀው በዚያች ቀን ነው።”

“ታዲያ በአንዱ ዓመት እንጎሮጎባሽ ተባብለን በችቦ ስንለኳኮስ አንድ ያልታሰበ ነገር ደረሰብኝ” አሉ ጋሽ ብሩክ እየሳቁ። “ለበዓሉ ተብሎ በጣም የጓጓሁለት አዲስ ልብስ እና ጫማ ተገዝቶልኝ ነበር፤ ከዚያም በደስታ እየሮጥኩ ችቦውን ሳወዛውዝ ከሌላው ልጅ ችቦ ተጎርዶ የወደቀ እሳት አዲሱ ልብሴ ላይ አረፈበት! አዲሱ ልብሴ እና ጫማዬ በእሳቱ ተቃጠሉ። ያኔ የተሰማኝ ሃዘን አይወራም! በዓሉ ሙሉ በሙሉ እንደተበላሸብኝ ተሰምቶኝ፣ ልብሴን አውልቄ እያለቀስኩ አልጋ ውስጥ ገብቼ ተኝቼ ነው የዋልኩት። እናቴ በላይ በላይ እንጀራና ስጋ ባትመግበኝ እስከመቼም ከሃዘኔ የምወጣ አይመስለኝም ነበር!” አሉ ጋሽ ብሩክ በሳቅ ታጅበው፡፡

ጋሽ ብሩክ ይህንን ሲተርኩልኝ እኔም የልጅነት ቁጭታቸውንና ያንን ንፁህ ስሜት እያሰብኩ አብሬያቸው ሳቅሁ። በእርግጥም የመስቀል በዓል እንዲህ ዓይነት ትዝታዎችን አዝሎ የሚያልፍ ድንቅ በዓል ነው።

ጋሽ ብሩክ ወሬያቸውን በመቀጠል፡- “እንጎሮጎባሽ” ተብሎ የጎመን እና የድንች ድስት ወጥቶ የስጋ እና የቅቤ ድስት ሲጣድ እና ሙክት በየቦታው ሲወድቅ፣ የክረምቱን ቅዝቃዜ ደጀን አድርጎ ጀግኖ በየወለሉ እንዳሻው ሰው አላስተኛ አላስቀምጥ ብሎ የከረመ ቁንጫ በችቦ ብርሃን እየተተኮሰ ሲሸሽ …ብቻ የመስቀል በዓል ውበቱ ብዙ ነው” በማለት የመስቀል በዓልን ትዝታ ብዝኃነት ነገሩን።

ከዚያም ውጭ ወደሚጨፈሩት ህፃናት እጃቸውን እየጠቆሙ ጨዋታቸውን ቀጠሉ።

“በኛ ጊዜ ሆያ ሆዬ ሲባል የተለዬ ነበር!

“ሆያ ሆዬ፣ ሆ፣

እዚህ ማዶ፣ ሆ፣

አንድ ጀበና፣ ሆ፣

እዛ ማዶ፣ ሆ፣

አንድ ጀበና፣ ሆ፣

የእኔማ ጋሽዬ ቆራጡ ጀግና! በማለት የቤቱን አባወራ እናሞግሳለን፡፡”

መቼም የባል ገንዘብ ለሚስት፣ የሚስትም ገንዘብ ለባል ነውና ሰጭ ጋሽዬ ብቻ ባለመሆናቸው የቤቱ እማወራም እንደሚከተለው በግጥም ይሞገሳሉ።

“ሆያ ሆዬ፣ ሆ፣

እዚህ ማዶ፣ ሆ፣

አንድ ከልካይ፣ ሆ፣

እዛ ማዶ፣ ሆ፣

አንድ ከልካይ፣ ሆ፣

የእኔማ እሜቴ ቀጭን ፈታይ!“

ከዚያም አቅም በፈቀደ በለጋስነት የሚሰጡንን ስጦታ ተቀብለን፦

“ድንቹ በሰለ፣ ሆ፣

አሁን የት ይገኛል ጋሼን የመሰለ! ብለን መርቀን ወደ ቀጣዩ ቤት እንገሰግሳለን” ሲሉ ነበር ትዝታቸውን ያጋሩን።

ጋሽ ብሩክ ይህን ሐሳብ እንዳጫወቱን ለአፍታ በዝምታ ተዋጡ፤ የአሁኑን እና የጥንቱን የበዓል አከባበር ማወዳደር ጀመሩ። በዚህ ወቅት ነበር በድንገት የፊታቸው ገጽታ ትዝታ ከፈጠረው ደስታ ወደ ቁጭት የተለወጠው።

“አሁን አሁን ዘመን ሲነጉድና ዓመታት በተራቸው ተፈራርቀው ሲተኩ ለውጥ የህይወት ሕግ ነውና አንዳንድ ለውጦችን አስተውላለሁ፤
ይኸው አሁን ህፃናት የሚሉትን አዳምጥ፦

“ሆያ ሆዬ፣ ሆ፣

እዚህ ማዶ፣ ሆ፣

አንድ ሰርዶ ሆ፣

እዛ ማዶ፣ ሆ፣

አንድ ሰርዶ፣ ሆ፣

የእኔማ ጋሽዬ ክርስቲያኖ ሮናልዶ!

“አየህ … ትውልድ እየሸፈተ ነው” በማለት በአሁኑ ወቀት የሚታየውን ከወግ ባሕል የማፈንገጥ ክስተት በሐዘኔታ ነገሩን።

ጋሽ ብሩክ ይህንን ብለው አጠናቀቁና ያወጡትን ባርኔጣቸውን መልሰው በራሳቸው ላይ እያስተካከሉ፣ የቀረበላቸውን ቡና መጠጣት ጀመሩ። ዓይኖቻቸው ግን አሁንም በደስታና በትዝታ ወደሚጨፈሩት ሕፃናት ያተኩሩ ነበር። እኔም ከጋሽ ብሩክ ጋር ያደረግኩትን ይህንን ውብ ጨዋታ በህሊናዬ እያመላለስኩ ወደ ሐሳቤ ተመለስኩ።

(ደረጀ ደርበው)

በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here