ጋብቻ እና የንብረት አስተዳደር

0
74

ጋብቻ  ሁለት ሰዎች (ወንድ እና ሴት) ባልና ሚስት ሆነው በአንድነት ለመኖር የሚፈጽሙት ትስስር ነው። ጥንዶች ስሜታዊ፣ አካላዊ እና አዕምሯዊ ሕይወታቸውን የሚጋሩበት፤ በፍቅር፣ በታማኝነት እና በእርስ በርስ መግባባት የሕይወት አጋርነት እና ቤተሰብ የሚመሠረትበት እንዲሁም ትውልድ የሚተካበት ተቋም ነው፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቤተሰብ ሕግ ሁለንተናዊ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተረጋጋ ቤተሰብ እንዲሁም ለሀገር ጠቃሚ ዜጋ መፍጠር የሚቻለው ጤናማ የጋብቻ ሕይወት ሲመሠረት እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ይህም ጋብቻ በሰው ልጆች እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው የተከበረ ማህበራዊ ተቋም መሆኑን ያሳያል።

በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ከአንቀጽ 02 እስከ 04 በተጠቀሱት ድንጋጌዎች ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በሃይማኖት እና በባሕል ሥርዓት መሠረት ሊፈጸም እንደሚችል አመላክቷል፡፡

ለመሆኑ ጥንዶቹ በጋብቻ ውስጥ  ንብረት  ማስተዳደር የሚችሉት እንዴት ነው?

የጋብቻ መመሥረት ከሚፈጥራቸው ሕጋዊ ግንኙነቶች ውስጥ ንብረትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቤተሰብ ሕግ በአንቀፅ 42 ላይ በመርህ ደረጃ ተጋቢዎች ንብረታቸውን ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸው በፊት ወይም እጅግ ቢዘገይ ጋብቻቸውን በሚፈፅሙበት ዕለት በውል መወሰን እንደሚችሉ ደንግጓል።

ሕጉ የጋብቻ ውል በጽሑፍ  ሰፍሮ አራት ምስክሮች (በባል ወገን ሁለት በሚስት ወገን ሁለት)  ሊፈርሙበት  እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

የባልና ሚስት የጋራ ሀብትን በተመለከተም በአንቀፅ 43 እንደሰፈረው ውል ያልተደረገ እንደሆነ ወይም የተደረገው ውል በሕግ ፊት የማይፀና ከሆነ በሕጉ በአንቀጽ 62 (1) ስር በተደነገገው መሠረት ባልና ሚስቱ በግል ወይም በጋራ የሚያገኟቸው ገቢዎች ሁሉ የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ፡፡

በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 62 (2) እንደተጠቀሰው የአንደኛው ተጋቢ የግል ሀብት ነው ካልተባለ በስተቀር ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ የሚያገኙት ንብረት ሁሉ የጋራ ሀብታቸው ይሆናል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 62 (3) በስጦታ ውል ወይም በኑዛዜ ቃል የተገኘ ንብረትም በሌላ አኳኋን ካልተመለከተ በስተቀር ንብረቶች ሁሉ የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አከራካሪ በሆኑ ንብረቶች ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜዎችን ሰጥቷል፡፡

ሀ. ከጋብቻ በፊት የግል ምሪት በነበረ ቦታ ላይ የተሠራ መኖሪያ ቤት

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 14479 በቅጽ 4፣ በመ/ቁ 26130 በቅጽ 6 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ “ቤት የተሠራበት ቦታ አንደኛው ወገን ጋብቻ ከመፈጸሙ በፊት በመንግሥት ተመርቶ ያገኘው ሲሆንና በዚሁ ቦታ ላይ ባልና ሚስት ከጋብቻ በኋላ  ቤት ቢሠሩ ቤቱ በጋብቻ ውስጥ ስለተሠራ የጋራ ሀብት ነው፡፡

ይዞታውም ከጋብቻ በፊት ስለተመራ የግል ነው ሊባል አይገባም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ምክንያቱም  ቤቱ የተሠራበትን ቦታ ለየብቻ ለያይቶ መመልከት ተገቢ ስለማይሆን ቤቱም ሆነ ይዞታው የጋራ ሀብት ነው ይላል፡፡

ለ. የጋራ መኖሪያ (ኮንዶሚኒየም) ቤት

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 74451 በቅጽ 14 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት የኮንዶሚኒየም ቤት የተገኘው በጋብቻ ጊዜ፣ በአንደኛው ተጋቢ ስም እና ለቤቱ  ቅድመ ክፍያ በጋብቻ ወቅት ካፈሩት የጋራ ንብረት የተከፈለ ከሆነ፤ ቤቱን ለማሳመርና በቤቱ የተለያዩ ክፍሎች ለመሥራት በጋብቻ ውስጥ ያፈሩትን ገንዘብ ከተጠቀሙ ቤቱ የባልና ሚስቱ የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡

በመሆኑም የኮንዶሚኒየም ቤቱ እና ያለበት ዕዳ እንደማንኛውም ንብረት የጋራ ስለሚሆን ከተስማሙ በስምምነት መስማማት ካልቻሉ ተሸጦ ዕዳው ተከፍሎ ቀሪውን ባልና ሚስት ሊካፈሉ ይገባል እንጂ አንደኛው ከፍሎ ያስቀር ማለት የተጋቢዎቹን የእኩልነት መብት የሚጥስ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።

በተጨማሪም በመ/ቁ 51893፣ በቅጽ 10 በሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት ለኮንዶሚኒየም ቤት አንደኛው ተጋቢ ከማግባቱ በፊት ተመዝግቦ ዕጣው በጋብቻ ጊዜ የወጣ ከሆነ እና የቤቱ ባለቤት የሚያደርገው የሽያጭ ውል በጋብቻ ውስጥ እያሉ ከተፈጸመ የኮንዶሚኒየም ቤቱ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 62 (2) መሠረት በጋብቻ ጊዜ በግብይት የተገኘ ሊባል የሚችል ስለሆነ የጋራ ሀብት ነው በሚል ወስኗል፡፡

በጋብቻ ውስጥ ስለግል ንብረት

በሕግ የጸና የጋብቻ ግንኙነት የግል ንብረት ከማፍራት አይከለክልም። በዚህም  በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 57 መሠረት ባልና ሚስት ጋብቻ በሚፈጽሙበት ጊዜ በየግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ ያገኟቸው ንብረቶች የግል  ሆነው ይቆጠራሉ በማለት አስፍሯል። በዚህም አንድ ሰው ጋብቻ በሚፈጽምበት ጊዜ በግል የነበረው እንዲሁም ጋብቻ ከፈጸመ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ የሚያገኘው ንብረት በጋብቻ ውስጥ የግል ሆኖ እንደሚቀጥል በመርህ ደረጃ ተደንግጓል፡፡ ይሁንና በጋብቻ ውስጥ በእነዚህ ንብረቶች አማካኝነት የሚገኝ ገቢ በአንቀፅ 62 ስር በተመለከተው አግባብ የጋራ ሀብት ይሆናል።

ሌላው በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 58 (1) መሠረት ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ አንዱ የግል ሀብቱ በሆነ ንብረት ለውጥ ያገኘው ወይም በግል ገንዘቡ የገዛቸው ወይም የግል ንብረቱን ሸጦ የሚያገኘው ገንዘብ የግል ይባልልኝ ብሎ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ያጸደቀው እንደሆነ የግል ሀብቱ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በፍቺ ጊዜ ወይም ጋብቻቸው በሚፈርስበት ጊዜ ባልና ሚስት የግል ሀብት መሆኑን በማስረዳት የግል ንብረታቸውን መልሶ የመውሰድ መብት ይኖራቸዋል።

የንብረት አስተዳደርን በሚመለከት

አንቀፅ 59 (1) እንደሚያስቀምጠው በመርህ ደረጃ እያንዳንዱ ተጋቢ የግል ሀብቱን ራሱ ማስተዳደርና ገቢውንም መሰብሰብ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም በአንቀፅ 59 (2) እንደተመላከተው የግል ሀብቱ ላይ በነፃነት የማዘዝ ስልጣን ተሰጥቶታል።

ነገር ግን ይህ ቢኖርም በአንቀጽ 60 (1) መሠረት ባልና ሚስት አንደኛው የሌላውን ተጋቢ የግል ሀብት በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያስተዳድርለት እና እንደ አስፈላጊነቱ እንዲያዝበት በጋብቻ ውላቸው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ይህም ሕጋዊ የውክልና ስልጣን አሰጣጥ ሂደትን የሚከተል አሠራር ይሆናል።

በአጠቃላይ በጋብቻ ውስጥ ንብረትን በተመለከተ ቀዳሚው ነገር ባልና ሚስት የጋብቻ ውል እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ውል ካልፈጸሙ ወይም የፈጸሙት የጋብቻ ውል በሕግ ፊት የማይጸና ከሆነ ግን በትዳር ውስጥ የሚያፈሯቸው ንብረቶች የግል ወይም የጋራ ናቸው ለማለት የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎችና የሰበር ውሳኔን መሠረት ማድረግን ይጠይቃል።

በተያያዘ አንድ ጊዜ በሕግ ፊት የሚፀና ትዳር ከተፈፀመ በኋላ በትዳር ውስጥ የሚፈራ ንብረት በአንቀፅ 57 የተቀመጠውን ሁኔታ የሚያሟላ ካልሆነ በቀር የጋራ ንብረት ተደርጎ የሕግ ግምት እንደሚወሰድ በሕጉ አንቀፅ 63 በግልፅ  ተቀምጧል፤ በመሆኑም ተጋቢዎች የንብረት አስተዳደርን አስመልክቶ ግልፅ የውል ግንኙነት በማድረግ ወይም የግል ንብረትን ተገቢውን የፍርድ ቤት ሂደት ጠብቆ በግል ባለቤትነት በማስመዝገብ ከአላስፈላጊ የንብረት ክርክር መዳን ይችላሉ።

 

መረጃ

በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ መሠረት ባለትዳሮች ቀድመው ያፈሩትን ንብረት በሕግ ማስዝገባቸው የሚከተሉትን ጥቅሞች ያስገኝላቸዋል፦

  1. የንብረቱን “የግል ንብረትነት” ለማረጋገጥ
  • በሕግ መሠረት ጋብቻ ከመመሥረቱ በፊት የአንደኛው ወገን የነበሩ ንብረቶች የዚያኛው ወገን የግል ንብረት ሆነው ይቀጥላሉ። ነገር ግን ንብረቶቹ አስቀድመው በሕግ ካልተመዘገቡ፣ ውል ከሌለ ወይም ማስረጃ ከጠፋ ከጊዜ ብዛት ንብረቱ በጋራ ጥረት እንደተፈራ ተቆጥሮ “የባልና ሚስት የጋራ ንብረት” ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። በመሆኑም ማስመዝገብ ይህንን ስጋት ያስቀራል።
  1. ውዝግብንና የፍርድ ቤት መጉላላትን ለመቀነስ
  • ትዳር ፈርሶ ፍቺ በሚከተልበት ጊዜ ወይም አንደኛው ወገን በሚያርፍበት ጊዜ የንብረት ክፍፍል ትልቅ ችግር ይሆናል። አስቀድሞ የተመዘገበ ሰነድ ካለ ግን የትኛው የግል፣ የትኛው ደግሞ በጋራ ትዳር ውስጥ የተፈራ ንብረት እንደሆነ በግልጽ ስለሚታወቅ አላስፈላጊ ክርክርን፣ የገንዘብን እና ጊዜን ብክነት ያስቀራል።
  1. ከዕዳ ተጠያቂነት ለመዳን
  • አንደኛው ወገን በትዳር ውስጥ ወይም ከትዳር በፊት የገባው የግል ዕዳ ቢኖር ዕዳ አስከፋዮች የሌላኛውን ወገን የግል ንብረት እንዳይነኩ ለመከላከል ንብረቱ አስቀድሞ በግል ስም የተመዘገበ መሆኑ ማረጋገጫ ይሆናል።
  1. በንብረት ላይ ሙሉ መብት እንዲኖር
  • አንዱ ወገን የራሱን የግል ንብረት ለመሸጥ፣ ለመለወጥ ወይም በስጦታ ለማስተላለፍ የትዳር አጋሩን ፈቃድ መጠየቅ አይኖርበትም። ንብረቱ በሕግ መመዝገቡ ይህንን የባለቤትነት ነፃነት ያረጋግጣል።
  1. የወራሾችን መብት ለማስጠበቅ
  • በተለይ ሁለተኛ ጋብቻ ለሚመሠርቱ እና ከመጀመሪያ ትዳራቸው ልጆች ላሏቸው ሰዎች የቀድሞ ንብረታቸውን ለይተው ማስመዝገባቸው የልጆቻቸውን የውርስ መብት ያረጋግጣል።

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

 

 

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here