መስቀል

0
200

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ምድር ከሃይማኖታዊ ክንዋኔ ባለፈ ሀገራዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው የጎላ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበ ታላቅ በዓል ነው። ይህ በዓል የክርስቶስ ስቅለት የተፈጸመበት እውነተኛው መስቀል የተገኘበትን ታሪካዊ ሁነት የሚያስታውስ ነው፤ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥነ-ጽሑፍ እና ባህል ጋር ያለው ቁርኝት ደግሞ የጎላ  እና ጥልቅ መሠረት ያለው ነው።

የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ

የበዓሉ መሠረተ ታሪክ የሚጀምረው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ326 ዓ.ም) በታሪካዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ ነው። የሮማው ንጉሥ ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ክርስትናን ከመቀበሉ እና የንጉሥነቱ አዋጅ ከመታወጁ በፊት በጦርነት ላይ ሳለ በሰማይ ላይ የበራ የመስቀል ምልክት አይቶ «በዚህ ምልክት ድል ታደርጋለህ» የሚል ድምፅ እንደሰማ እና ጦርነቱንም ድል እንዳደረገ በታሪክ ይነገራል። ይህንን ታሪካዊ ሁነት ተከትሎ የንጉሡ እናት ንግሥት ዕሌኒ የክርስቶስን እውነተኛ መስቀል (ዕፀ መስቀል) ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች።

የአይሁድ መሪዎች፣ ክርስቲያኖች መስቀሉን እንዳያመልኩት እና እንዳያከብሩት በመስጋት ከተማዋን ሲያጸዱ የሚወጣውን ቆሻሻ ሁሉ መስቀሉ በተቀበረበት ስፍራ ላይ ይጥሉበት ስለነበር ቦታው ወደ ትልቅ ኮረብታነት ተቀይሮ ነበር። ንግሥት ዕሌኒ ቦታውን ማግኘት አዳጋች በሆነባት ጊዜ ኪራኮስ (ኪርያኮስ) የተባለ አረጋዊ የአይሁድ ሰው አማካኝነት ተጠቆመች። እርሱም በባህላዊው መንገድ ዕጣን አጥና እንድትጸልይ እና የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ወደ ታች የሚያርፍበት ስፍራ የመስቀሉ መገኛ መሆኑን ነገራት ይላል የዐፄ ዘረአ ያዕቆብ መዋል ያስረዳል።

ንግሥት ዕሌኒም እንደተባለው ዕጣኑን አጥና በፈጠረችው ትልቅ ደመራ ስትጸልይ የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከፍ ካለ በኋላ ቀጥታ አምርቶ መስቀሉ ከተቀበረበት ኮረብታ ላይ አረፈ። ይህንን ታሪካዊ ክስተት ተከትሎ ኮረብታው እንዲቆፈር አዘዘች። ቁፋሮው መስከረም 17 ቀን ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን ተጠናቆ እውነተኛው መስቀል በግራ እና ቀኝ አብረው ከተሰቀሉት ሁለት ወንበዴዎች መስቀል ጋር ተገኘ። በዓሉ መስከረም 17 ቀን የሚከበረው የቁፋሮው መጀመሪያ እና ደመራ የተለኮሰበትን ታሪካዊ ዕለት ለመዘከር ነው።

ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ትስስር

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ ውስጥ እጅግ የጎላ ስፍራ አለው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና የነገሥታቱ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት የጌታ መስቀል ግማሽ (ግማደ መስቀሉ) ወደ ኢትዮጵያ የገባው በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት (ከ1374 – 1405 ዓ.ም) መሆኑን «መጽሐፈ ጤፉት» ያስረዳል፡፡ ሙሉ በሙሉ ሥርዓት ተበጅቶለት ያረፈው ግን በልጃቸው በዐፄ ዘርአ ያዕቆብ (ከ1426 – 1460 ዓ.ም) ዘመን ነው።

በወቅቱ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች እና የግብፅ ኦርቶዶክሳውያን በነገሥታት ግፍ እና መከራ ሲጸናባቸው የኢትዮጵያ ነገሥታት በነበራቸው ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት ጥበቃ ያደርጉላቸው ነበር። የግብፅ እና የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ለዚህ ውለታ ምላሽ ይሆን ዘንድ ታላቅ ስጦታ ለመስጠት በወሰኑ ጊዜ ዐፄ ዳዊት የመረጡት ወርቅ እና አልማዝ ሳይሆን የኢየሱስን ግማደ መስቀል ነበር። ይህ ምርጫ የኢትዮጵያ ነገሥታት ለሃይማኖታዊ ቅርሶች የነበራቸውን የላቀ ፍቅር እና ክብር ያሳያል።

ግማደ መስቀሉ ረጅም ጉዞ ተጉዞ ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ ዐፄ ዘርአ ያዕቆብ «አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል» (መስቀሌን በመስቀል ቅርጽ ባለው ቦታ ላይ አስቀምጥ) የሚል መለኮታዊ ራእይ ስላዩ ቦታውን ፍለጋ ብዙ እንደተጓዙ በመዋላቸው ተጠቅሷል። በመጨረሻም የወሎ (የአሁኑ ደቡብ ወሎ) ምድር ላይ የሚገኘውን ተፈጥሯዊ ቅርጹ የተዘረጋ መስቀል የሚመስለውን የግሸን አምባን አግኝተው ግማደ መስቀሉን እዚያ አሳረፉት።

የግሸን አምባ በደቡብ ወሎ የሚገኝ ታሪካዊ እና በተፈጥሮ የተመሸገ ገደላማ ተራራ ነው። ይህ አምባ ልዩ የሚያደርገው መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጡ የተዘረጋ የመስቀል ቅርጽ ያለው መሆኑ ነው። ከአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን በፊት ንጉሣውያን ወገኖች የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይቀሰቅሱ ተለይተው የሚጠበቁበት ስፍራ ነበር። ዛሬም ድረስ «ግሸን ደብረ ከርቤ» የመስቀሉ ታሪካዊ ማረፊያ በመሆን በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት ቅዱስ ስፍራ ነው።

ባህላዊ እና ማኅበራዊ ትስስር፤ ደመራ እና አዲስ ዓመት

በኢትዮጵያ የመስቀል በዓል ከክረምት ወደ በጋ መሸጋገሪያ፣ ተፈጥሮ አረንጓዴ ለብሳ በቢጫ የመስቀል ወፍ እና የመስቀል አበባ የምታጌጥበት የወቅቶች መለወጫ ማብሰሪያ ነው። በዓሉ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ታላቅ የባህል አውድ ነው።

የበዓሉ ዋዜማ መስከረም 16 ቀን የደመራ ዕለት ይባላል። ረጅም እንጨቶች ተሰብስበው፣ በአደይ አበባ እና በሌሎች ጌጣጌጦች አጊጠው በየአደባባዩ እና በየቤቱ ደመራ ይቆማል። ምሽት ላይ ካህናት፣ ምእመናን እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ደመራው ይበራል። የደመራው መቃጠል እና የእንጨቶቹ መውደቂያ አቅጣጫ (ወደ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ወይም ደቡብ) ለወደፊቱ የሀገር ሰላም፣ ምርት እና መልካም ዘመን ትንበያ የሚደረግበት ባህላዊ መስተጋብር አለው።

ከዚህም በተጨማሪ በመላው ኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገራችን ክፍሎች የመስቀል በዓል ትልቅ ማኅበራዊ ትርጉም አለው። ለምሳሌ በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ «መስቀል» የዓመቱ ታላቅ በዓል ነው፤ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተራራቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ቅሬታዎች እና ቂሞች የሚታረቁበት ታላቅ ዕለት ነው። በዚህ በዓል ላይ ባህላዊ ምግቦች የሆኑት ቆጮ፣ ጎመን፣ ክትፎ እና አይብ በስፋት ተዘጋጅተው በጋራ ይበላሉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ በወላይታ ማኅበረሰብ ዘንድ በዓሉ «ጊፋታ» ተብሎ ይጠራል፤ ትርጉሙም መሻገሪያ ወይም አዲስ ምዕራፍ ማለት ነው። ማኅበረሰቡ አሮጌውን ዓመት በደስታ ሸኝቶ አዲሱን ዓመት በሰላም ለመቀበል በጋራ ይጨፍራል፤ ይደሰታል። በተጨማሪም በሐድያ፣ በከምባታ እና በሌሎችም ማኅበረሰቦች ዘንድ አዲስ የተጋቡ ሙሽሮች የሚጠየቁበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት እና አረጋውያን ወጣቱን መርቀው ወደ ሥራ የሚያሰማሩበት የፍቅር እና የአንድነት በዓል ነው።

የመስቀል በዓል ከኢየሩሳሌም ምድር የተነሳ ታሪካዊ መሠረት ቢኖረውም በኢትዮጵያ ምድር ያገኘው አቀባበል፣ የተገነባለት ሃይማኖታዊ ሥርዓት እና የተዋሃደበት ባህላዊ እሴት በዓሉን ሙሉ በሙሉ «ኢትዮጵያዊ» መልክ አስይዞታል። የመስቀል በዓል የትናንት ታሪክ ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያንን የሕልውና፣ የነፃነት፣ የባህል ጥልቅነት እና የአብሮነት እሴት በየዓመቱ የሚያድስ ሀገራዊ አምድ ነው።

ሳምንቱ በታሪክ

ቃለ-መሐላው

መስከረም 18 ቀን 1909 ዓ.ም የሸዋ መኳንንት ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ካወረዱ ማግስት ታማኝነታቸውን ለንግሥት ዘውዲቱ እና ለአልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ መኮንን ለመግለጽ የታማኝነት ቃለ-መሐላ (የኅብረት ስምምነት) የፈጸሙበት ታሪካዊ ዕለት ነው።

መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን መውረዳቸው በአደባባይ ታውጇል ። በማግስቱ መስከረም 18 ቀን 1909 ዓ.ም ደግሞ የሸዋ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ ጦር መሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ታላቁ ቤተ መንግሥት በይፋ ተሰባሰቡ። ይህ ስብሰባ የተጠራው ኢትዮጵያ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እና ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ ለመከላከል ነበር።

በዕለቱ የተሰበሰቡት መኳንንት በአዲሷ ንግሥተ ነገሥታት ንግሥት ዘውዲቱ አማካኝነት እና በባለሙሉ ሥልጣን አልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ) መሪነት ሥር ሀገሪቱን በታማኝነት ለማገልገል ሕጋዊ የታማኝነት ቃለ-መሐላ ፈጸሙ። ይህ ስምምነት አዲሱ የሥልጣን ጥምረት በሕዝቡ እና በጦር ሠራዊቱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረገ ታሪካዊ እርምጃ ነበር።

ይህ የቃለ-መሐላ ሥነ-ሥርዓት እና የኅብረት ስምምነት ለአዲሱ አስተዳደር መረጋጋት እጅግ ወሳኝ ሚና የነበረው፤ ከልጅ ኢያሱ ወገኖች በተለይም ከወሎው ንጉሥ ሚካኤል ሊሰነዘር የሚችለውን ማንኛውንም ወታደራዊ ጥቃት ለመመከት ቃል የተገባበት በመሆኑ ነው። መኳንንቱ የግል ጥቅማቸውን እና ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው የሀገራችንን አንድነት ለመጠበቅ በአንድ ልብ ለመቆም ተስማሙ። ይህ በታሪክ የተመዘገበው የቁርጠኝነት ውሳኔ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በጥቅምት ወር 1909 ዓ.ም  ለተቀሰቀሰው ታዋቂው የሰጋሌ ጦርነት የሸዋ ጦር ሠራዊት በአንድ ወጥ ዕዝ ሥር እንዲሰለፍ እና የንጉሥ ሚካኤልን ጦር በቁጥጥር ሥር በማዋል ፍጹም ድል እንዲቀናው ጠንካራ መሠረት ጥሏል በማለት «የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ» በሚለው መጽሐፋቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ያስረዳሉ።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም  18  ቀን 2019  ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here