ድንበር ተሻጋሪዉ ሌብነት

0
53

ሙስና ሉዓላዊነትን የሚፈታተን፣ ኢኮኖሚን ከውስጥ የሚበላ እና ድንበር የማያውቅ ዓለም አቀፋዊ ሌብነት ሆኗል፡፡ ሐቀኝነትን በገንዘብ ከመግዛትም አልፎ የዲፕሎማሲ መሣሪያ፣ የፖለቲካ መረብ እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓቱን ክፍተቶች የሚጋልብ ፈተናም ነው፡፡ ይህም ድሆችን በመበዝበብ  “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው የሚያደርግ ድርጊት ነው፡፡

ሙስና የመንግሥት፣ የሕዝብ ወይም የግል ኃላፊነትን እና ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል ሲል ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ሙስና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ተቋም ይተረጉመዋል፤ ይህም የስነ-ምግባር ውድቀትን ብቻ ሳይሆን የሀገራትን ኢኮኖሚ፣ የሕግ የበላይነትን እና ማሕበራዊ ፍትሕን የሚሸረሽር ስውር ወንጀል ነው፡፡ ሙስና ጉቦ መቀበልንና መስጠትን፣ የሕዝብ ሀብት ምዝበራን፣ የዘመድ አዝማድ አሠራርን እና ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን ያጠቃልላል፡፡

የሙስና ታሪካዊ ዳራ

ሙስና የቅርብ ጊዜ ክስተት አይደለም፤ ታሪኩ ከሰው ልጅ የመንግሥት አወቃቀር እና የሥልጣን ሥርዓት ምሥረታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጥንታዊ የጽሑፍ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው ክፍለ ዘመን በሕንድ የተጻፈው አርታሻስትራ(Arthashastra) የተሰኘው የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ መጽሐፍ በወቅቱ የነበሩ የመንግሥት ሠራተኞች የሕዝብ ገንዘብን የሚመዘብሩበትን 40 የተለያዩ የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና መንገዶችን ዘርዝሯል፡፡

የጥንታዊ ሜሶፖታሚያ እና ግሪክ ታሪክ እንደሚያስረዳው ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ18ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የሀሙራቢ ሕግ (Code of Hammurabi) ዳኞች ጉቦ እንዳይቀበሉ የሚከለክሉ እና ጉቦ የተቀበሉ ዳኞች በጽኑ እንደሚቀጡ የሚያዝዙ ድንጋጌዎች ነበሩት፡፡ በጥንታዊ ሮም ግዛት በሮማዊያን ኢምፓየር ዘመን የምርጫ ድምጽን የመግዛት እና የወታደራዊ አዛዦች የሕዝብ ሀብት ምዝበራ የተለመደ የፖለቲካ ውድቀት ምክንያት እንደ ነበርም የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

የሙስና ዓለም አቀፍ ገጽታ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙስና ለምጣኔ ሀብት ዕድገት ትልቅ ማነቆ ሆኗል፡፡ ዓመታዊውን የሙስና ደረጃ ይፋ የሚያደርገው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል መረጃ እንደሚጠቁመው ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት የዓለም ሀገራት ከመቶው ከ50 በታች በማስመዝገብ በከፍተኛ የሙስና ስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ በቅርቡ ያወጡት መረጃ ደግሞ በየዓመቱ ከሁለት ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በጉቦ መልክ እንደሚከፈል እና ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን የሕዝብ ሀብት እንደሚመዘበር አስታውቀዋል፡፡

ሙስና በአፍሪካ

በአፍሪካ አህጉር ሙስና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የድህነት እና የሥራ አጥነት ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት መረጃ እንደሚያመላክተው በአህጉሪቱ በየዓመቱ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት በሕገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰት (Illicit Financial Flows) እና በሙስና ምክንያት ከአህጉሪቱ ይሸሻል፡፡ ይህ ገንዘብ አህጉሪቱ ለትምህርት፣ ሕክምና እና መሠረተ ልማት የምትፈልገውን በጀት ያሳጣል፡፡ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ፍትሕ አካላት እና የምርጫ ቦርዶች በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በመዳከማቸው ሙስናን በብቃት ለመከላከል ሲንገዳገዱ ይስተዋላል፡፡

በአፍሪካ ለጤና ጥበቃ፣ ለንጹህ የመጠጥ ውኃ እና ለትምህርት ዘርፍ መመደብ የነበረበት በጀትም በሙስና ምክንያት ስለሚመዘበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ለከፋ ድህነት እና ለበሽታ ተዳርገዋል፡፡ ሙስና ባለበት ሀገር የሥራ ማስኬጃ ወጪ ስለሚጨምር እና ግልጽነት ስለሚጎድል ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ሀብታቸውን በአፍሪካ ላይ ከማፍሰስ ተቆጥበዋል፡፡

ሙስና ያስከተለው የፍትሕ ማጣት እና ሥራ አጥነት በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሮ ለሥራ ማቆም አድማዎች፣ ለሕዝባዊ አመጾች እና በቅርብ ዓመታት በምዕራብ አፍሪካ ለታዩት ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣዎች (Coup d’état) እንደ ዋነኛ ሰበብ ሆኗል፡፡

በሙስና ሀገራት ያገኙት ደረጃ

በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሚዘጋጀውና 182 ሀገራትን ያካተተው የ2025 እ.አ.አ የዓለም አቀፍ የሙስና አመልካች መረጃ እንደሚያሳየው የዓለም አቀፍ የሙስና አማካይ ውጤት  ከመቶው 42 ሆኗል፡፡ ይህም ባለፉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው ዝቅተኛው አማካይ ነጥብ ነው፡፡

ከ182 ሀገራት መካከል 122 ያህሉ (ከሁለት ሦስተኛ በላይ) ከ50 ነጥብ በታች ያገኙ ሲሆን ይህም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ የሙስና ስጋት እንዳለ አመላካች ነው፡፡ እ.አ.አ በ2025 አነስተኛ ሙስና ያለባቸው ሀገራት ከመቶው  ያገኙትን ውጤት ስንመለከትም ዴንማርክ 89 (89/100) ውጤት በማግኘት ለተከታታይ ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙስናን በመከላከል  በግንባር ቀደምትነት መምራቷን ቀጥላለች፡፡ ፊንላንድ  ደግሞ ከመቶው 88፣ ሲንጋፖር 84 በማምጣት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ ኒውዚላንድ እና ኖርዌይም በ81 ነጥብ ይከተላሉ፡፡

ከፍተኛ ሙስና ወደ ሚፈጸምባቸው ሀገራት ጎራ ስንል በመጀመሪያ ደረጃ ተቀምጠው የምናገኛቸው ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን ነው፡፡

ሁለቱ ሀገራት ከመቶው ዘጠኝ (9/100) በማምጣት በጋራ ዝቅተኛውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ቬኔዙዌላ ከመቶው 10፣ የመን 13፣ ሊቢያ እና ኤርትራ 13 በማምጣት በደረጃው መጨረሻ አካባቢ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከመቶው 38 ነጥብ በማግኘት ከ182 ሀገራት መካከል በ96 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ከሰሀራ በታች ከሚገኙ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የተሻለ ውጤት ብታስመዘግብም አሁንም ከ50 ነጥብ በታች በመሆኑ በመንግሥት አገልግሎትና ግዥዎች ላይ ከፍተኛ የሙስና ማሻሻያ ሥራዎች እንደሚቀሯት ያሳያል፡፡

መፍትሔዎች

የተለያዩ ሀገራት የሙስናን ወንጀል ለመግታት የተለያዩ የሕግ፣ የቴክኖሎጂ እና የቅጣት ርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ ለአብነትም ቻይና በከፍተኛ ባለሥልጣናት እና በታችኛው የሥራ መደብ ላይ ባሉ ሠራተኞች ላይ እየተካሄደ የሚገኝ “ነብሮች” እና “ዝንቦች” የተሰኙ የጸረ-ሙስና ዘመቻን እ.አ.አ በ2012/13 ይፋ ማድረጓ ይታወቃል፡፡ ነብሮች የሚለው ዓላማው ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው አካላት ከሕግ በላይ እንዳልሆኑ ማሳየት እና በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ ያለውን ሥር የሰደደ የሙስና መረብ መስበር ነው፤ በዚህም በከባድ የሙስና እና የምዝበራ ወንጀል የተገኙ ባለሥልጣናት የሞት ቅጣት ወይም የዕድሜ ልክ እስራት ይበየንባቸዋል፡፡

ዝንቦች በሚለው ደግሞ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናት፣ የከተማ ወይም የቀበሌ አስተዳዳሪዎች እና ተራ የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ በዚህ ዘመቻ ተራው ሕዝብ በየቀኑ የሚያጋጥመውን አነስተኛ ሕገወጥ ክፍያዎች፣ ጉቦዎች እና ማጭበርበሮች እንዲቆሙ ተደርገውለታል፡፡

ቻይና በኋላ ላይ “ቀበሮዎችን ማደን” የሚል ተጨማሪ ዘመቻ የጀመረች ሲሆን በዚህ ዘመቻም የሀገርን ሀብት ዘርፈው፣ በሙስና የተገኘን ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገር በማሸሽ በተለይም  ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት የፈረጠጡ ባለሥልጣናትን እና ሀብታሞችን አድኖ ወደ ቻይና በመመለስ ለፍርድ ታቀርባለች፡፡ የቀበሮዎች ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የፓርቲና የመንግሥት አባላት ምርመራ ተደርጎባቸዋል፤ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ የእስራት እና የሀብት መውረስ ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ዴንማርክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ  ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ዝቅተኛ የሙስና ደረጃ ያለባት ሀገር ለመሆን የበቃችው ጠንካራ እና ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዓት ስላላት ነው፡፡ በተጨማሪም ክፍት እና ግልጽ የመንግሥት አሠራር፣ ጠንካራ እና ገለልተኛ የክትትል ተቋማት በመገንባቷ ፣ ግልጽ የሆነ የባለሥልጣናት ሀብት ምዝገባ በማካሄዷ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በተለይም ነጻ እና ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ያለምንም ስጋት የመንግሥት አሠራርን የመመርመር፣ የመከታተል እና የሙስና ጥቆማዎችን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሙሉ ነጻነት ስለተጎናጸፉ ውጤቱ አመርቂ ሆኗል፡፡

ሲንጋፖርም ለመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛ ደመወዝ በመክፈል ገለልተኛ የሙስና ምርመራ ቢሮ በማቋቋም እና የዲጂታል አሠራርን በማስፋፋ ሙስናን ለመከላከል ጥረት አድርጋለች፡፡ ሙስና ሲፈጽም የተገኜ ግለሰብም ከባድ የእስራት ቅጣት፣ የንብረት መወረስ እና ዳግም በማንኛውም የመንግሥት ሥራ የመቀጠር መብትን በዘላቂነት ያጣል፡፡

የአውሮፓ ሕብረትም ሙስናን ለመከላከል በሕገወጥ መንገድ የተገኘ የገንዘብ ዝውውርን መከላከል የሚያስችሉ ሕጎችን አውጥቷል፤ ሙሰኞችን ለሚያጋልጡ ግለሰቦችም የሕግ ከለላ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሙስና ፈጽመው በተገኙ ሰዎች ላይ ከባድ የገንዘብ ቅጣት፣ የንብረት መወረስ እና ለረጅም ዓመታት የእስራት ቅጣቶች ይጠብቋቸዋል፡፡

ሙስና በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ቢስፋፋም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ፣ የዲጂታል አሠራር እና የፖለቲካ ቁርጠኝነትን በማስፈን ሙስናን በመከላከል ረገድ ስኬታማ የሆኑ የአፍሪካ ሀገራትም አሉ፤ ​ሲሼልስ እና ቦትስዋና ደግሞ የዚህ አብነት ናቸው፡፡ ሀገራቱ በአህጉሪቱ አነስተኛ የሙስና ደረጃ ያላቸው እና ግልጽ አሠራርን የገነቡ ናቸው፡፡

ሩዋንዳም ሙስናን ፍጹም በማይታገስ መርህ በመመራት የባለሥልጣናትን ሀብት በማሳወቅ እና የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋፋት ሙስናን ለመከላከል እየሠራች ነው፡፡ ሙስና የፈጸሙ ሰዎች ሲኖሩ  ከባድ የገንዘብ እና የእስራት ቅጣት ይጠብቃቸዋል፤ ጥፋተኛ የተባሉ ባለሥልጣናት ስምም ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል፡፡

በአጠቃላይ ሙስናን ለመከላከል የሕግ አስፈጻሚ ተቋማትን ነፃ ማድረግ፣ የቴክኖሎጂ አሠራሮችን ማስፋፋት እና የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ማረጋገጥ ወሳኝ ርምጃዎች መሆናቸውን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አስነብቧል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here